የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ዙር ዛሬ ሲጀመር ኢትዮጵያ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ ባገኘው የፍፁም ቅጣት ምት ታግዞ ንግድ ባንክን 1-0 አሸንፎ ወጥቷል፡፡
ፈጣን በሆነ እንቅስቃሴ ተጀምሮ አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተደራጀ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት በዘለቀው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል እጅግ ጥቂት የግብ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ከቡና በኩል በ41ኛው ደቂቃ ያቤውን ዊልያም ከመስመር የተሸገረለትን ኳስ ሞክሮ ፌቮ እንደምንም ያወጣበት ከባንክ በኩል ደግሞ ዳንኤል አድሀኖም ከርቀት ሞክሮ ሀሪሰን ያወጣበት ኳስ በጨዋታው የታዩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ፡፡
ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰአት በመጨረሻዎቹ ደቂዎች ጫና ሲፈጥሩ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ችለዋል፡፡ በ90+3ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ያቤውን ሲጨርፈው ቶክ ጀምስ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ያቤውን ዊልያም ወደ ግብነት ቀይሮ ለኢትዮጵያ ቡና ወሳኝ 3 ነጥብ አስገኝቷል፡፡
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ እስከ ጨዋታው መጠናቀቅያ ድረስ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በክለቡ አመራሮች ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ አምሽተዋል፡፡
ውጤቱ ኢትዮጵያ ቡና 5 ደረጃዎችን አሻሽሎ 6ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ሲያደርገው ንግድ ባንክ አንድ ደረጃ እንዲወርድ አድርጎታል፡፡
የደረጃ ሰንጠረዥ
የፕሪሚየር ሊጉ 14ኛ ሳምንት ነገ ሲቀጥል አዲስ አበባ ላይ መከላከያ ከ ኤሌክትሪክ ፣ ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ከ አርባምንጭ ከተማ ፣ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ከ ደደቢት በተመሳሳይ ሰአት ሲጫወቱ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ዳሽን ቢራን 10፡00 ላይ ያስተናግዳል፡፡ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን 11፡30 ላይ የሚያስተናግድበት ጨዋታ የ14ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ይሆናል፡፡