ድሬዳዋ ከተማ የፕሪሚየር 2ኛ ዙር ጨዋታውን ዛሬ ዳሽን ቢራን በማስተናገድ ይጀምራል፡፡ ቡድኑን በቅርቡ የተቀላቀለው ዮርዳኖስ አባይም ታሪክ ወደሰራበት ፕሪሚየር ሊግ ተመልሷል፡፡
ዮርዳኖስ በዝውውሩ እና በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ኮንትራትህ ለምን ያህል ጊዜ ነው?
ለድሬዳዋ ከተማ የፈረምኩት የ3 ወር ውል ማለትም እስከ ሁለተኛው ዙር መጠናቀቅ ድረስ ነው፡፡
በሊጉ መጫወት የጀመርከው በድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ነው፡፡ አሁን ወደ ድሬዳዋ የመጣኸው በክለቡ የጨዋታ ዘመንህን ለማጠናቀቅ ነው?
ለድሬደዋ ከተማ በመፈረሜ እና በትውልድ ከተማዬ ላይ ሆኜ መጫወት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ድሬደዋ ከተማ ወደ ፕሪሚየር ሊግ መግባቱ ለእግር ኳሱ ትልቅ መነቃቃት ነው የፈጥረው፡፡ አሁን በግማሽ የውድድር ዘመን ላይ በመግባቴ ከዚህ በኋላ ባለኝ ጊዜ ከተጨዋቾቹ እና ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ለድሬዳዋ እግር ኳስ የምችለውን ለማድረግ ነው የማስበው፡፡ የመጨረሻህ ጊዜ ይሆናል ላልከው ግን ፈጥሪ ነው የሚያቀው፡፡
አብረውህ የተጫወቱ ተጫዋቾች በአመዛኙ ጫማ ሰቅለዋል፡፡ አንተ ለረጅም ጊዜ የመጫወትህ ሚስጢር ምንድነው?
ምንም የተለየ ሚስጥር የለውም ዋናው ስራህ የሚፈልገውን ነገር ማድረግ አለብህ፡፡ ይህ ማለት እግር ኳሱ የሚፈልገውን ነገሮች ካደረግክ ለምሳሌ ልምምድ በአግባቡ መስራት ፣ እረፍት ማድረግ ፣ ራስን በዲሲፒሊን መጠበቅ. . . በቃ በነዚህ ነገሮች ረጅም ጊዜ ለመቆት ችያለው፡፡
ስለዚህ እስከ መቼ መጫወትህን ትቀጥላለህ?
ሀሳቤ እስከምችለው ድረስ ያለኝን አቅም ሙሉ ለሙሉ አውጥቼ ለመጫወት ነው፡፡ የጉዳትና ምናልባት የተለያየ ምክንያት ካልመጣ በጥሩ ብቃት እግር ኳስ ማቆም ነው የማስበው፡፡
ስለ ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሲነሳ ሁሌም ስምህ ይነሳል፡፡ ይህ ምን ይፈጥርብሃል?
ደስ ይላል፡፡ ይበልጥ አሁን ባለሁበት ሰአት መሆኑ ደግሞ ደስ ይለኛል፡፡ እስካሁን ይህ ነገር እኔ ጋር በመሆኑ ይበልጥ እንድሰራ ነው የሚያደርገኝ ጥሩ ሆኜ እንድቆይ ያደርገኛል፡፡
ከየመን 10 አመት ቆይታ ተመልሰህ ለመድን ፣ ለኤሌትሪክ እና ለድሬዳዋ ፖሊስ ተጫውተሀል፡፡ ከተመለስክ በኋላ ያለህን ቆይታ እንዴት ትገልፀዋለህ?
ጥሩ ነበር፡፡ ትንሽ ችግር የገጠመኝ በኤሌክትሪክ የመጫወት እድል አልሰጡኝም፡፡ በኢትዮጵያ መድን ደግሞ ከቦርዱ ጋር ጥሩ ግኑኝነት ነበረኝ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ አባይነህን የመሰለ አሰልጣኝ ማግኘቴ በህይወቴ ላይ ትልቅ ትምህርት እንዳገኝ አድርጎኛል፡፡ ከዛም በኃላ በድሬደዋ ፖሊስ ከተጨዋቾቹ ጋር በፍቅር ጥሩ ጉዞ አድርጌያለው፡፡
የድሬደዋ ልጅ ብትሆንም ብዙዎች የሚያውቁህ በኤሌትሪክ ፣ በቡና እና በብሄራዊ ቡድን በሰራኸው ነው ። የድሬደዋ ስፖርት አፍቃሪ የሚያስታውስህን ስራ ለመስራት አሁን እድል አግኝተሃል፡፡ በዚህ ዙርያ ምን አስበሀል?
በአዲሱ ክለቤ ድሬዳዋ ከቡድን አጋሮቼ ጋር ተባብረን ጥሩ ነገር ለማምጣት እንጥራለን፡፡ ድሬዳዋ ከተማ በመጀመርያው ዙር ጥሩ ነበር፡፡ አሁንም በግሌ ድሬዳዋን ወደ ጥሩ ደረጃ ለማምጣት ዝግጅት እያደረግኩ ነው፡፡
ድሬዳዋ በ1ኛው ዙር ድክመቱ የአጥቂ መስመሩ ነበር፡፡ ይህን ችግር እቀርፈዋለህ ብለህ ታስባለህ?
አሁን አሁን የሚነሱ የአጥቂ ችግሮች ስሰማቸው ይገርሙኛል፡፡ በተለይ አጥቂ የለም ሲባል ስሰማ ይገርመኛል እንዴት 80 እና 90 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ አንድ አጥቂ ማግኘት ያቅተናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አንድን አጥቂ የሚያስተካክለው አሰልጣኝ ነው የሚሰጠው ስልጠና ጥሩ ከሆነ አጥቂውም ጥሩ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡
በምችለው አቅም ጎሎችን ማስቆጠር እና መስዋአት መሆን አለብኝ፡፡ የአጥቂ ስራ ጎል ማግባት ብቻ አይደለም፡፡ ባለኝ ሰፊ የተጨዋችነት ልምድና በአገኘሁት አጋጣሚ ለቡድኑ ጥሩ ነገር ለማድረግ መስዋአት በመሆን የምችለውን አደርጋለው፡፡
ቀጣይ የእግር ኳስ ዘመንህ ምን መልክ ይኖረዋል?
ወደ ድሬደዋ ስመለስ ፖሊስ ስገባ ያደረጉልኝ አቀባበል በጣም ጥሩ ነበር እኔም የምችለውን ያክል ማድረግ ችያለው ድሬደዋ ከነማም አሁንም ከዚህ በፊት በሌሎቹ ክለቦች የሰራዉኋቸውን ስራዎች ለመስራት በደንብ ተዘጋጅቼአለው ከህዝቡ ከተጨዋቾቹ ጋር በመሆን የምችለውን አደርጋለው