የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው በደረጃ ሰንጠረዡ አናት የሚገኙት ክለቦች ነጥብ ጥለዋል፡፡ ድሬዳዋ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ መከላከያ እና ወላይታ ድቻ ደግሞ ድል ቀንቷቸዋል፡፡
ድሬዳዋ ላይ ዳሽን ቢራን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ 3-1 በማሸነፍ ሁለተኛውን ዙር በድል ጀምሯል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ካለግብ በተጠናቀቀበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዮርዳኖስ አባይ በ57ኛው ደቂቃ በግንባሩ በመግጨት ድሬዳዋን ቀዳሚ ሲያደርግ በ65ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ የድሬዳዋን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡ ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ኤዶም ሆሶውሮቪ ዳሽን ቢራን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ ቢያስቆጥርም ዳዊት እስጢፋኖስ በ74ኛው ደቂቃ ድሬዳዋ ከተማ ድሉን ያረጋገጠበትን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ዮርዳኖስ አባይ ለድሬዳዋ ከተማ በተጫወተበት የመጀመርያ ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ቦዲቲ ላይ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደደቢትን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 1-0 አሸንፏል፡፡ የድቻን ወሳኝ የማሸነፍ ግብ ከመረብ ያሳረፈው ፀጋዬ ብርሃኑ ነው፡፡
በሲዳማ ደርቢ ሀዋሳ ከተማ ሲማ ቡናን አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ይርጋለም ላይ በተደረገው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች ፍርዳወቅ ሲሳይ ባስቆጠረው ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ከ5 ደቂቃዎች በኋላ የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ አጥቂ አንዱአለም ንጉሴ ሲዳማን አቻ አድርጓል፡፡ በ61ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ግርማ በቀለ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን ወደ ድል መርቷል፡፡
ሆሳዕና ላይ ሁለቱ የመውረድ ስጋት ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ሀዲያ ሆሳዕና በቢንያም ገመቹ የቅጣት ምት ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ተሸመ ታደሰ በ86ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ አርባምንጭ ከተማን ታድጓል፡፡
አዲስ አበባ ስታድየም ላ መከላከያ ኤሌክትሪክን 2-0 አሸንፏል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ካለግብ በተጠናቀቀበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የተሸለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት መከላከያዎች በፍሬው ሰለሞን እና ማራኪ ወርቁ ግቦች ድል አድረገው ወጥተዋል፡፡
በእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን አስተናግዶ በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ መሪነቱን የሚሰፋበትን እድል አምክኗል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያው የያዙት አዳማ ከተማዎች ሲሆኑ በ37ኛው ደቂቃ ጫላ ድሪባ እንግዶቹን መሪ ሲያደርግ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ራምኬል ሎክ ፈረሰኞቹን አቻ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ከተጠናቀቀበት ሰአት የጀመረው በደጋፊዎች መካከል የተነሳ ግርግር ለ40 ደቂቃዎች ዘልቆ ለሰዎች እና ንብረት ጉዳት ዳርጓል፡፡
ከ40 ደቂቃ ግርግር በኋላ የተጀመረው ጨዋታ እንደመጀመርያው አጋማሽ ፈጣን እንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራዎች ሳይታይበት ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ከፍተኛ ግብ አግቢዎች
በተፈጠረው ግርግር ዙርያ ያጠናቀርነውን ዘገባ ይዘን እንመለሳለን