የ2008 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ተጠናቆ ሁለተኛው ዙር ሲጀምር ከትላንት በስትያ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተደረገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ የዙሩ መጀመሪያ ፍልሚያ ነበር፡፡ በ90+5ኛው ደቂቃ ላይ በተገኘችው የያቤውን ዊልያም የፍፁም ቅጣት ምት ጎል በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የዚህን ጨዋታ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሶከር ኢትዮጵያ እንደሚከተለው አቅርባላችኋለች፡፡
የጨዋታ አቀራረብ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፡ – በተለይም በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ለመረዳት አስቸጋሪ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጨዋወት በአመዛኙ ወደ 4-1-4-1 የቀረበ ነበር፡፡ በቡድኑ የፊት አጥቂ ቢኒያም አሰፋና በተከላካይ አማካዩ ጋብርኤል አህመድ መካከል በአብዛኛው ይታይ የነበረው የአራቱ አማካዮች እንቅስቃሴ የቡድኑ ቅርፅ 4-1-4-1 እንደነበር ማሳያ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና፡ – የቅዳሜው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን በ4-4-2 ቅርፅ ያሳየን ነበር፡፡ ከመጀመሪያው ዙር በተለየ ሁኔታ ቡድኑ አንድ የአጥቂ አማካይ በመቀነስ በቲ ካፑ ሲጠቀም እንደነበረው በሁለት አጥቂዎች ሲጠቀም ተስተውሏል፡፡ በአማካይ ስፍራ ላይ በሁለቱ መስመሮች እያሱ ታምሩን እና ኤልያስ ማሞን ሲጠቀም ከመሀል አማካዮች ጋቶች ፓኖምና አማኑኤል ዩሀንስ መካከል አማኑኤል ወደፊት ጠጋ ብሎ የአማካዩን መስመር ከአጥቂው ጋር የማገናኘቱን ሀላፊነት እንዲሁም ጋቶች እንደተለመደው የተከላካይ አማካይነቱን ሚና ሲወጡ ተስተውሏል፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ
የጨዋታው የመጀመሪያ ጥቂት ደቂቃዎች በፈጣን እንቅስቃሴ የታጀቡ ነበሩ፡፡ ሁለቱም ፡ ቡድኖች በቶሎ ወደግብ በመድረስ የጎል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ሲታይ ጨዋታው በቅርብ ደቂቃዎች ጎሎቹን ሊያስተናግድ እንደሚችል የሚያስገምት ነበር፡፡ ነገር ግን በጨዋታው ጎሎችን ለመመልከት አልተቻለም፡፡ ይህም የሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት እቅድ ስኬታማ እንዳልነበር የሚናገር ነው፡፡ የሁለቱን ቡድኖች ያልተሳካ የማጥቃት አቀራረቦች እንደሚከተለው እንመልከታቸው፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፡ – በብዙ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች እንደተዋቀረ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎል የማስቆጠር ችግሩ በመጀመሪያውም ዙር አብሮት የነበረ ነው፡፡ በትናንትናውም ጨዋታም ይኋው ችግሩ አብሮት ነበር፡፡ የቡድኑ የመጀመሪያ ምርጫ የማጥቃት መስመር በግራ በኩል ወይም በኤፍሬም አሻሞ በኩል ነው፡፡ ቡድኑ በተደጋጋሚ በዚህ መስመር ጥቃቶችን ለመሰንዘር ቢሞክርም ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በኃላ ይህ አካሄድ ለተጋጣሚው ተጫዋቾች ተገማች አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾችም ወደ መከላከል በሚያደርጉት ሽግግር ላይ ይህን መስመር ፈጥነው እየዘጉ ተጋጣሚያቸው አደጋ ክልል ውስጥ ከመጋባቱ በፊት ኳሶችን ያቋርጡ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በእጅጉ ወደግራ ያዘነበለ ማጥቃት የቀኙን መስመር ያዘናጋው አስመስሎታል፡ በዚህም የተነሳ የቀኝ አማካዩ ፍቅረየሱስ ተክለብርሀን ቡድኑ ኳስን በግራ መስመር ላይ ይዞ በሚቆይባቸው ጊዜያት በተደጋጋሚ ያለኳስ በሚያረገው እንቅስቃሴ በተጋጣሚው የሜዳ ክልል ላይ ሲገኝ የሁለተኛ አጥቂ ሚና ያለው ይመስል ነበር፡፡ ቡድኑ በዚህ በኩል በተመጣጠነ ሁኔታ ሁለቱን መስመሮች በመጠቀም ተጋጣሚውን በሜዳው ስፋት በማጥቃት ክፍተቶችን ለማግኘት በመሞከር በኩል ደካማ ነበር፡፡ የቡድኑ ወደግራ ማዘንበል የተጋጣሚውንም ሃሳብ ወደ አንድ አቅጣጫ መሳቡ በቀኝ በኩል በተደጋሚ ክፍተቶችን እየፈጠረለት ነበር፡፡ ነገር ግን ከጥቂት አጋጣሚዎች በቀር ይህን ክፍተት ለመጠቀም አልተሞከረም፡፡ በዚህ በኩል በ8ኛው ደቂቃ በግራ በኩል በኤፍሬም አሻሞ ተጀምሮ በፍቅረየሱስ አማካይነት በቀኝ ክንፍ በነበረው ክፈተት በመጠቀም ለአብዱልከሪም የደረሰውና አብዱልከሪም የሞከረው የመጀመሪያው የቡድኑ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም በቀኝ መስመር ወደ ተጋጣሚው ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ አሻግሮት ከአጥቂው ቢኒያም ቀድሞ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ደርሶ ከተፋው በኋላ መልሶ የያዘው ኳስ የቀኝ መስመሩ የተሻለ ክፍተት የነበረውና ተደጋጋሚ ጥቃት በዚያው አቅጣጫ ቢደረግ ጎል ሊያስገኝ ይችል የነበረ መሆኑን የሚያሳዩ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ ቡድን በተጋጣሚው ላይ የነበረው የመሀል ሜዳ የቁጥር ብልጫ ከኃላም ሆነ ከግራ በኩል ተመስርተው የሚጀመሩ ኳሶችን ወደቀኝ ለማሻገር ወሳኝ ጥቅም የነበረው ቢሆንም አማካይ መስመሩ ይህንን ማሳካት አለመቻሉ አጥቂው ቢኒያም አሰፋ ከአማካይ ክፍሉ ግልፅ የጎል ዕድል ሳያገኝ እንዲቀር አድርጎታል፡፡
አትዮጵያ ቡና፡ – በመጀመሪያው ዙር ላይ እንደተመለከትነው ኢትዮጵያ ቡና በአብዛኛው አንድ አጥቂ በመጠቀምና በመሀል ሜዳው ላይ ከተከላካዩ ጋቶች ፓኖም ፊት ፈጣሪ አማካዮችን እና የመስመር አማካዮች በመጠቀም ለ4-1-4-1 በቀረበ አጨዋወት የመሀል ሜዳውን የበላይነት ለመውሰድ በመሞከር የግብ እድሎችንም ከነዚህ አማካዮች ለማግኘት ይሞክር ነበር፡፡
ነገር ግን ይህ አካሄድ እንደታሰበው ከፊት ለሚገኘው አጥቂ ብዙ የማግባት እድሎች በመፍጠር በኩል ስኬታማ አልነበረም፡፡ ቡድኑ የሚይዘውን የመሀል ሜዳ የበላይነትም ያህል የጎል ፍሬ ለማግኘት ተቸግሮ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል አትዮጵያ ቡና በዚህ ጨዋታ ላይ ሁለት አጥቂዎችን በመጠቀም ጎሎችን ለማግኘት በማሰብ ወደ 4-4-2 አጨዋወት የመጣው፡፡ ነገር ግን በጨዋታ እንቅስቃሴ በተፈጠሩ አጋጣሚዎች ጎል ሳያስገባ እንዲሁም እንደ ሌላው ጊዜ የመሀለ ሜዳ የበላይነቱ በጉልህ ሳይታይ ነበር የዋለው፡፡
ከሁለቱ የፊት አጥቂዎች መካከል የቡን ዊልያም ወደኃላ እየተሳበ እንዲሁም ወደቀኝ እየወጣ ኳስን በመቀበል የቡድኑን የመሀል ሜዳ የበላይነት ለማስገኘት ሲጥር ተስተውሏል፡፡ ይህ አጨዋወቱ በተለይም በአብዛኛው በቀኝ በኩል ወይም በኤልያስ ማሞ በኩል ያጋደለው የቡድኑን አጠቃቅ የበለጠ ጉልበት የሚጨምርለት የነበረ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ያለቀለት የግብ ሙከራ ለመፍጠር አላገዘውም፡፡ ሌላኛው አጥቂ ንዳዬ ፋያስም በቂ እድሎች ማግኘት አልቻለም፡፡ በግራ መስመር በእያሱ ታምሩ እንዲሁም በመሀል ሜዳው አማካይ አማኑኤልም በኩል የነበረው የማጥቃት አካሄድም የመጨረሻ ኳሶችን ለአጥቂዎቹ በማድረስ የተዋጣለት አልነበም፡፡ ባጠቃላይ ቡድኑ አሁንም ጨዋታዎችን አሸንፎ ለመውጣት በተለይም በማጥቃቱ በኩል በቋሚነት ሊጠቀምበት የሚችለውን ትክክለኛ የጨዋታ ዕቅድ ያገኘ አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያ ቡና የጎል እድሎችን ለመፍጠር እና ጎሎችን በብዛት ለማግኘት የሚረዳውን አማራጮች ሲፈልግ የመሀል ሜዳ የበላይነቱን የሚያስገኙለትን የፈጣሪ አማካዮቹን ሚና ሳይቀንስ ቢሆን ይመረጣል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተደረጉ ለውጦች
በሁለተኛው አጋማሽ አብዛኛው ክፍል የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ ብዙ ሳይቀየር የቀጠለ ነበር፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ ለውጦችን ለመመልከት ችለናል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሁለቱን የመሀል አማካዮች ቦታ በመቀየር አብዱልከሪምን ከኤፍሬም አጠገብ በማድረግ እና ሰለሞንን ከፍቅረየሱስ ጎን በማድረግ ለመጫወት ሞክሯል፡፡ ይህ ቅያሪ በተለይ በግራ በኩል ቡድኑ ማጥቃት ይሰነዝርበት የነበረውን አግባብ በመጠኑ ቀይሮት ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የኤፍሬም አሻሞን የቴክኒክ ብቃት ከግራ መስመር ኳስን ይዞ ወደውስጥ በመግባት እንዲጠቀምበት በማድረግና አብዱልከሪም በኤፍሬም ወደውስጥ መግባት የሚፈጠረውን ክፍተት ለመጠቀም መስመሩን ይዞ ወደፊት ይሄድበት የነበረው እንቅስቃሴ በተለየ መልኩ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
በተጨሪም በ78ኛው ደቂቃ ታዲዮስ በለዲን በሰለሞን ገ/መድህን በመተካት የተደረገው ቅያሪ የቡድኑን ቅርፅ ወደ 4-2-3-1 የቀየረ ነበር በዚህም ቡድኑ በሁለት የተከላካይ አማካዮች በመጠቀም ውጤት አስጠብቆ ለመወጣት ማሰቡን ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በሁለተኛው ግማሽ የሁለቱን አጥቂዎች ሚና አለዋውጦ ገብቷል፡፡ ያቤውን ዊሊያምን የመጨረሻ አጥቂ አድርጎ በምትኩ ወደኋላ የመሳቡን ሀላፊነት ለንዳዬ ፋደስ ሰቶት ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ ሁለቱንም መስመሮች በተመጣጠነ ሁኔታ ለመጠቀምም ሞክሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በ69ኛው ደቂቃ ንዳዬ ፋደስን በሳዲቅ ሴቾ (7) እንዲሁም በ75ኛው ደቂቃ አክሊሉ ዋለልኝን (12) በኤሊያስ ማሞ በመቀየር እያሱ ታምሩን በቀኝ በኩል በመመለስ እና የኤልያስን ቦታ እንዲያዝ በማድረግ ለአክሊሉ የግራ መስመር አማካይነቱን ሰጥቶታል፡፡
ነገር ግን በእለቱ ከኤልያስ ማሞ ሁዋላ ሆኖ በቀኝ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈውና በዚሁ መስመር ላይ ወደፊትም እያለፈ በማጥቃቱ በኩል የተዋጣ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረውን አህመድ ረሻድን በጉዳት ያጣው ኢትዮጵያ ቡና አጥቂው ፓትሪክ ቤናውን (21) በማስገባት በሜዳው ላይ ያሉትን የአጥቂዎች ብዛት ሶስት አድርሶታል፡፡ ይህ አጋጣሚ እያሱን በጨዋታው ለሶስተኛ ጊዜ ቦታ አስቀይሮት አህመድ ረሻድን በመተካት የቀኝ መስመር ተከላካይ ሲያረገው የቀኝ መስመር አማካይነቱን ቦታ ሳዲቅ እንዲሸፍን ሆኗል፡፡
በሁለት የማጥቃት ባህሪ ባላቸው ተጫዋቾች እንዲዋቀር የተገደደው የኢትዮጵያ ቡና የቀኝ መስመር ( ምስል3) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠንካራ የግራ መስመር ጫና ውስጥ ሊገባ የሚችልበት እድል የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ንግድ ባንኮች ይህን አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት በተቃራኒው የኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻ ሰአት በዚህ መስመር በኩል በተፈጠሩ ተፅዕኖ አማካይነት የተሻገረው ኳስ በመሀል ተከላካዩ ቶክ ጀምስ በእጅ ተነክቶ በያቡን ዊሊያም አማካይነት ለተቆጠረችው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ምክንያት ሆኗል፡፡ ከጎሏ መቆጠር በኋላም ጨዋታው በመገባደዱ ንግድ ባንኮች የኢትዮጵያ ቡናን ተጋለጠ የቀኝ መስመር መፈተን ሳይችሉ በብቸኛዋ ጎል ተሸንፈው ለመውጣት ተገደዋል፡፡
ባጠቃላይ ሁለቱም ቡድኖች ይዘውት የገቡት የጨዋታ እቅድ በቀጥታ በጨዋታው ላይ የበላይነትን ሊያቀዳጃቸው አለመቻሉ እና ጨዋታውም በጥቂት የጎል ሙከራዎች ብቻ መታጀቡ ቡድኖቹ በመጪዎቹ ጊዜያት የጨዋታ አቀራረባቸውን ቀይረው ወይም አሻሽለው ሊመጡ እንደሚገባ ያሳየ ሆኖ አልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቀጥለው ሲካሄዱ ሀሙስ 9 ሰዐት ላይ ኢትዮጵያ ቡና በ አዲስ አበባ ስታድየም መከላከያን ሲገጥም አርብ ደግሞ 11፡30 ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደደቢት ይፋለማል፡፡