በውጪ የሚጫወቱ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ባሳለፍነው ሳምንት በተደረጉ የሊግ እና የቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ ተሰልፈው መጫወት ችለዋል፡፡
ግብፅ
ፔትሮጀት እና ኢኤንፒፒአይ ጋር በሳምንቱ መጨረሻ በተደረጉ የግብፅ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሽንፈትን ቀምሰዋል፡፡
ፔትሮጀት ከሜዳው ውጪ በአዲስ አዳጊው አስዋን 2-1 ሲሸነፍ የኡመድ ክለብ የሆነው ኢኤንፒፒአይ በመሪው አል አሃሊ 2-0 ተሸንፏል፡፡ ሽመልስ ሙሉ 90 ደቂቃ መጫወት የቻለ ሲሆን ክለቡ ለአብዛኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ መሪ መሆን የቻለበትን ግብ እንዲቆጠር በማድረግ ሚናው የላቀ ነበር፡፡ በ11ኛው ደቂቃ ሞታሳም ሳሊም ከሽመልስ የተቀበለው ኳስ ተጠቅሞ ፔትሮጀትን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ በ61ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ናይጄሪያዊው ጄምስ ኦቦስኪኒ በ68ኛው ደቂቃ በቀጥታ ቀይ ካርድ መውጣቱ ፔትሮጄትን ዋጋ አስከፍሏል፡፡ የቁጥር ብልጫ የነበራቸው አስዋኖች በጨዋታው መገባደጃ ላይ በኤሃብ ኤል ማስሪ እና ኢብራሂም ኤል ሻኢብ ግቦች አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡ ፔትሮጀት በግብፅ ዋንጫ ላይም ከሩብ ፍፃሜው በኢቲሃድ አሌክሳንድሪያ ተሸንፎ የቀረ ሲሆን ወደ አፍሪካ መድረክ ለመመለስ መንገዶች ሁሉ የጠበቡበት ይመስላል፡፡
ኢኤንፒፒአይ በቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም በሊግ መሪው አል አሃሊ 2-0 ሲሸነፍ ኡመድ በ66ኛው ደቂቃ ሃምዲ ፋቲን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ ኡመድ በጨዋታው ላይ መልካም እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡ አሃሊ በአብደላ ኤል ሰዒድ የፍፁም ቅጣት ምት እና በጨዋታው ኮከብ በነበረው ሞሜን ካዛሪያ ግብ ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከአውሮፖ ክለቦች ከፍተኛ ትኩረትን ያገኘው የአሃሊው መስመር አማካይ ረመዳን ሶብሂ በመጀመሪያው አጋማሽ በቀይ ካርድ ወጥቷል፡፡
ሽንፈቱን ተከትሎ ኢኤንፒፒአይ አሰልጣኝ ሃምዳ ሰድኪን አሰናብቷል፡፡ ረቡዕ በካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የጋቦኑን ሲኤፍ ሞናናን የሚያስተናግደው ኢኤንፒፒአይ በግዜያዊ አሰልጣኙ ካሊድ ሜትዋሊ እየተመራ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ራሱን ከአሰልጣኝነት መንበሩ በገዛ ፍቃዱ ያነሳውን ሃኒ ራምዚን ተክተው ወደ ነዳጅ አምራቹ የመጡት ሰድኪ ኢኤንፒፒአይ በውጤት ማጣት ውስጥ መገኘቱ ለስንብታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡
በደረጃ ሰንጠረዡ ፔትሮጀት 10ኛ ሲሆን ኢኤንፒፒአይ 12ኛ ነው፡፡ ሊጉን አል አሃሊ ይመራል፡፡ የአምና ሻምፒዮኑ ዛማሌክ ደግሞ በ2ኛነት ይከተላል፡፡
ደቡብ አፍሪካ
የፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ ከብሎምፎንቶን ሴልቲክ ጋር 1-1 በተለያየበት ጨዋታ ጌታነህ ወደ ቋሚ አሰላለፉ ተመልሷል፡፡ ላለመውረድ በትግል ላይ ለሚገኘው የፕሪቶሪያው ክለብ ደቡብ አፍሪካዊው ኢነሰንት ኔሙኮንደኒ ከጌታነሀ የተላከትን ኳስ ተጠቅሞ ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ጌታነህ በውድድር ዓመቱ ሶስት ግብ የሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል፡፡ ሴልቲክ ነጥብ ይዞ የወጣበትን ግብ ቩያኒ ናታንጋ በ85ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡
በአብሳ ፕሪምየርሺፕ ደረጃ ሰንጠረዥ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ 21 ነጥብ 14ኛ ሲሆን ሊጉን ማሜሌዲ ሰንዳውንስ በ58 ነጥብ ይመራል፡፡
ስዊድን
በስዊድን ሊግ ኦስተርሰድስ ሁለት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ በያምክራፍት አሬና ላይ ቢኬ ሃከንን ያስተናገደው ኦስተርሰንድስ 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ዋሊድ ከቀድሞ ክለቡ ጋር በተደረገ ጨዋታ የኋላ መስመሩን የመራ ሲሆን ለኦስተርሰንድስ የድል ግቦቹን ሮናልድ ሙኪቢ እና ኢራናዊው ብርዋ ኑሪ (በፍፁም ቅጣት ምት) አስገኝተዋል፡፡ ለሃከን ሳይመን ሳንድበርግ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ዋሊድ ኦስተርሰንድስ ለፋልከብርግስ ጋር ባደረገው የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ ከቡድኑ ውጪ የነበረ ሲሆን ከሃከኑ ጨዋታ ወደ ቋሚ አሰላለፉ ተመልሷል፡፡ ኦስተርሰንድስ በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ በሰባት ነጥብ ስድስተኛ ሲሆን አንድ ቀሪ ጨዋታ የሚቀረው ዩርጋርደንስ ሊጉን በ9 ነጥብ ይመራል፡፡
ባንግላዴሽ
ወደ ባንግላዴሽ ሊግ ያቀናው ፍቅሩ ተፈራ ለሼክ ሩሰል መሰለፉን ቀጥሏል፡፡ በቅድመ ውድድር ዋንጫ ኢንዲፐንደንስ ካፕ ጨዋታ በምደብ ሁለት ፊኒን ያሰተናገደው ሼክ ሩሰል ያለግብ አቻ ወጥቷል፡፡ ፍቅሩ በመጀመሪያ ጨዋታው ግብ ያስቆጠረ ሲሆን በሁለተኛው ጨዋታም የአጥቂ መስመሩን መምራት ችሏል፡፡
ፎቶ ፡ ዋሊድ አታ እና ተሰናባቹ አሰልጣኝ ሀምዳ ሰድኪ (ከኦስተርሰንድስ እና ኢኤንፒፒአይ የፌስቡክ ገፆቸ ችየተወሰዱ)