የግብፁ ኢኤንፒፒአይ እና የሱዳኑ አሃሊ ሸንዲ ከካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ ሲሰናበቱ ምስር ኤል ማቃሳ፣ ሚዲአማ፣ ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት፣ ሲኤፍ ሞናና እና ካውካብ ማራካሽ ቀጣዩን ዙር የተቀላቀሉ ክለቦች ናቸው፡፡
ፔትሮ ስፖርት ስታዲየም ላይ በተደረገ ጨዋታ ኢኤንፒፒአይ ሞናናን በዋኤል ፋራጅ እና በሆንዱራሳዊው አጥቂ ማርዩ ማርቲኔዝ 2-0 ቢያሸንፍም በመለያ ምት 5-4 ተሸንፈው ከውድድሩ ተሰናብተዋል፡፡ ኡምድ ኡኩሪ ከብድኑ ውጪ በመደረጉ በጨዋታው ላይ መሰለፍ አልቻለም፡፡ በተጫዋቾች አያያዝ እና ለአሰልጣኞች ምቹ ባለመሆን የሚተቸው ክለቡ መጥፎ የውድድር ዘመንን እያሳለፈ ይገኛል፡፡
የአዲስ ህንፃው አሃሊ ሸንዲ በጋናው ሚዲአማ 2-0 ሲሸነፍ ኩዋሜ ቦሂን እና አባስ መሃመድ ግቦቹን በመጀመሪያው ግማሽ አስገኝተዋል፡፡
ካውካብ ማራካሽ በፋኪር የመጀመሪያ ግማሽ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ታግዞ ሞሊዲያ ክለብ ደ ኦራንን ሲረታ የኢትዮጵያውን መከላከያ በቅድመ ማጣሪያው ማሸነፍ የቻለው ምስር ኤል ማቃሳ ፋዩም ስታዲየም ላይ ኮንስታንታይንን 3-1 በማሸበፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ሶስተኛው የማጣሪያ ዙር አልፏል፡፡ የማለፍ ተስፋው ከመጀመሪያው ተሟጦ የነበረው የዩጋንዳው ቪላ ካምፓላ ላይ ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባትን 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ራባት ላይ የግብ ናዳ የወረደባቸው ቪላዎች በኡመር ካሱምባ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ወደ ሶስተኛው እና የመጨረሻው የማጣሪያ ዙር ያለፉት ክለቦች ከካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር ከወደቁት ክለቦች ጋር ተደልድለው ወደ ምድብ ለመግባት የሚጫወቱ ይሆናል፡፡፡ የመጨረሻው ዙር ድልድል ዛሬ አመሻሽ ላይ ካፍ ይፋ ያደረጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የረቡዕ ውጤቶች፡
ስፖርት ክለብ ቪላ (ዩጋንዳ) 1-0 ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ) (1-7)
ኢኤንፒፒአይ (ግብፅ) 2-0 ሲኤፍ ሞናና (ጋቦን) (2-2 በመለያ ምት ሞናና 5-4 አሸንፏል)
ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ) 1-0 ሞሊዲያ ክለብ ደ ኦራን (አልጄሪያ) (1-0)
ሚዲአማ (ጋና) 2-0 አሃሊ ሸንዲ (ሱዳን) (2-0)
ምስር ኤል ማቃሳ (ግብፅ) 3-1 ክለብ ስፖርቲፍ ኮንስታንታይን (አልሪጄያ) (3-2)
ወደ ተከታዩ ዙር ያለፉ ክለቦች፡
ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ፣ ሳግራዳ ኤስፔራንሳ፣ ሚዲአማ፣ ካውካብ ማራካሽ፣ ሲኤፍ ሞናና፣ ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት፣ ምስር ኤል ማቃሳ እና ስታደ ጋብሲየን ከቻምፒየንስ ሊጉ የወረዱ ክለቦች፡ ኤቷል ደ ሳህል፣ ቲፒ ማዜምቤ፣ ኤል-ሜሪክ፣ ያንግ አፍሪካንስ፣ ሞሎዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ፣ ስታደ ማሊያን፣ አሃሊ ትሪፖሊ እና ማሜሎዲ ሰንዳውንስ