አሰልጣኝ ዘማርያም ቡድናቸውን መቼ መምራት ይጀምራሉ?

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ.ማ የሦስት ወር ዕግድ የተላለፈባቸው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ መቼ ቡድናቸውን መምራት እንደሚጀምሩ ታውቋል።


የአስረኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከተጠናቀቁ በኋላ የሊግ ኮሚቴው ጥር 10 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የሻሸመኔ ከተማው ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ክለቡ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበረው ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት “አሠራርን የሚተች እና የጨዋታ አመራሮችን ክብር የሚነካ አስተያየት ስለመስጠታቸው ሪፖርት ቀርቦባቸዋል።” በማለት በውድድር እና ሥነስርዓት ኮሚቴ አሰልጣኙ የሦስት ወር ዕግድ እና ተጨማሪ የ10ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸው መቆየቱ ይታወሳል።

በዚህ መነሻነት ያለፉትን ሦስት ወራት(የ11 ሳምንታት ጨዋታዎች) ቡድናቸውን ሳይመሩ ቆይተዋል። ሆኖም ዛሬ ሚያዚያ 10 ቅጣታቸውን የሚያጠናቀቅቁበት ሦስተኛ ወራቸው መሆኑን ተከትሎ አሰልጣኝ ዘማርያም የፊታችን ቅዳሜ አስር ሰዓት ሻሸመኔ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ቡድናቸውን እንደሚመሩ እርግጥ ሆኗል።