ደደቢት በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ከተሰማራው ትራንስ ኢትዮጵያ ጋር ወደፊት የሚታስ የአጭር ጊዜ የስፖንሰርሺፕ ውል ዛሬ በካፒታል ሆቴል ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የደደቢት እርኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ ወልዳይ በርሄ እና የትራንስ ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ ዘውዱ ሲሆኑ ለ6 ወር በሚቆየው የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ትራንስ ለደደቢት 4 ሚልዮን ብር ይከፍላል፡፡ በስምምነቱ ላይ ትራንስ ኢትዮጵያ በቀጣዩ አመት ወደ ክለቡ የኮርፖሬት አባልነት የሚያድግ ሲሆን ክለቡን በቀጣዮቹ አመታት በተለያዩ ተቋማት ባለበትነት ስር እንዲተዳደር የማድረግ አላማ ያለው ነው ተብሏል፡፡
በጋዤጣዊ መግለጫዎች ላይ ፣ ደደቢት በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች እና በክለቡ ኦፊሴላዊ ፎቶዎች ላይ የትራንስ ኢትዮጵያ አርማ የያዘ ባነር እንደሚኖር ከደደቢት በኩል ተገልጧል፡፡ በትራንስ በኩል የስፖርት ልማትን ለመደገፍ እና ኩባንያውን የማስተዋወቅ አላማ በመያዝ ደደቢትን ስፖንሰር እንዳደረገ ታውቋል፡፡
ደደቢት ይህን መሰል ስምምነት ሲፈራረም 2008 ከገባ በኋላ ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡ መሰቦ ሲሚንቶ የማልያ ስፖንሰር በመሆን በ4 ሚልዮን ብር ለአንድ አመት ስፖንሰር የሆነ ሲሆን ከሳምንታት በፊት ሱር ኮንስትራክሽን 2.3 ሚልዮን ብር የሚያወጣ የተጫዋቾች ማጓጓዣ አውቶብስ በስፖንሰር መልክ አበርክቷል፡፡
በፕሮግራሙ መጨረሻ የደደቢት ሴቶች ቡድን አባላት በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዙር ላስመዘገቡት ውጤት የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት እንደየአስተዋፅኦዋቸው ከ7-4 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡