የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የብሄራዊ ቡድኑን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እና ረዳቶቻቸውን ለማሰናበት ከውሳኔ መድረሱ ከፌዴሬሽኑ አካባቢ ተሰምቷል፡፡
በጉዳዩ ዙርያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ይፋዊ ማረጋገጫ ያልሰጠ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ከፌዴሬሽኑ ሃላፊዎች እና አሰልጣኝ ዮሃንስ ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም፡፡
ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አሊሚራ መሃመድ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉና ፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ይፋ እስኪያደርግ መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ከሚድያ ከመስማታቸው በቀር መረጃው እንደሌላቸው የጠቀሱ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ ስብሰባው ላይ ባለመገኘታቸው ስለ ጉዳዩ ምንም እንደማያውቁ ገልፀዋል፡፡
ከአንድ አመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣነት መንበር የመጡት ዮሃንስ ሳህሌ በአንድ አመት ቆይታቸው በቻን ፣ ሴካፋ ፣ የአለም እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች ያስመዘገቧቸው ደካማ ውጤቶች ፣ በጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ያላቸው አቀራረብ እና ወጥ ባልሆነው የተጫዋቾች አመራረጥ ልምዳቸው በብዙዎች የተወቀሱ ሲሆን በመጨረሻም ከአሰልጣኝነት መንበራቸው መሰናበታቸው ተሰምቷል፡፡