የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ማረፍያ ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ሶከር ኢትዮዽያ አረጋግጣለች፡፡
ለአንድ አመት ያህል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በውጤት መራቅና ተያያዥ ጉዳዮች መነሻነት ባሳለፍነው ሳምንት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት ባደረጉት ስብሰባ ረዳቶቻቸው እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ከሃላፊነት እንዲነሱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ፌዴሬሽኑ የስንብት ዜናውን ይፋ ያላደረገ ሲሆን በመጪው ሳምንት ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አሰልጣኝ ዮሃንስ የስንብታቸው ዜና ከተሰማበት ማግስት አንስቶ ስማቸው ከተለያዩ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር መያያዙን ቀጥሏል፡፡
ለአሰልጣኙ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ዮሃንስ በአሁኑ ሰአት በፕሪሚየር ሊጉ በወቅታዊ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ደደቢት ፣ መከላከያ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ አሰልጣኞች ታሪክ ከፍተኛ ክፍያ በማቅረብ የቅጥር ጥያቄ እንዳቀረቡ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አሰልጣኝ ዮሃንስ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየታቸውን ወደ ክለብ እግርኳስ ለመመለስ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸውና ከፌዴሬሽኑ ጋር ያላቸውን ጉዳይ መልክ እስኪያሲዙ ድረስ ጊዜ እንዲሰጧቸው ምላሽ እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከኢትዮያ ውጭ በተለይ ከኬንያ ብሔራዊ ቡድን የቀረበላቸውን ጥያቄ እንዳልተቀበሉና በሀገራቸው ኢትዮጵያ ሊሰሯቸው የሚያስቧቸው በርካታ ስራዎች እንዳሉ በመጠቆም ማረፊያቸው ኢትዮዽያ ውስጥ ከሚገኙ የፕሪሚር ሊግ ክለቦች አንዳቸው እንደሚሆኑ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ አንድ ቀን በኬንያ የማሰልጠን ፍላጎት እንዳላቸው ከወራት በፊት ለሃገሪቱ የእግርኳስ ድረገፅ ሶካ ኬንያ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡