የኢምፓክት ሶከር አካዳሚ በጎ ጅምር

በሀገራችን እግርኳስ ስር ከሰደዱ ችግሮች መካከል የተደራጀ የታዳጊዎች እና ወጣቶች ስልጠና አለመኖር በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ ይህንን ለመቅረፍም በግለሰቦች እና ተቋማት አነሳሽነት በሀገሪቱ የታዳጊ ማሰልጠኛዎች መቋቋም ጀምረዋል፡፡ በድሬዳዋ የሚገኘው ኢምፓክት ሶከር አካዳሚም በጎ ጅምር ላይ ከሚገኙት መካከል ነው፡፡

ጥቅምት 2009 ላይ የተመሰረተው ኢምፓክት ሶከር አካዳሚ የአስር ወራት ጊዜ ያስቆጠረ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ ላይ ታዳጊዎችን በሁለቱም ጾታ ታዳጊዎችን እያሰለጠነ ይገኛል። በአጠቃላይ ከ70 በላይ ታዳጊዎች ካለምንም ክፍያ ስልጠናውን እየወሰዱ ሲገኙ በሴቶች ከ15 እና ከ20 አመት በታች ፣ በወንዶቹ ደግሞ ከ15 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን አቅፏል፡፡

በአካዳሚው በድሬዳዋ እግር ኳስ ታሪክ ላይ ስማቸው በጉልህ የሚጠሩ ግለሰቦች እያሰለጠኑ የሚገኙ ሲሆን የቀድሞ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ እና ምድር ባቡር ድንቅ ተጨዋቾች የነበሩት ፍስሀ ጥኡመልሳን ፣ ማሙሽ አለምሰገድ ፣ ተንሳይ ግርማ ፣ አለምሰገድ ኃ/ማርያም ፣ ግርማ ተሾመ እና ቀኝነህ ጥላሁን በስራ ላይ ከሚገኙት መካከል ናቸው፡፡

ዛሬ ማለዳ ላይ ታዳጊዎቹ ልምምድ በሚሰሩበት ሜዳ ሶከር ኢትዮዽያ ባደረገችው ቅኝት ትኩረት ተሰቶት ተገቢ የሆነ እና ተከታታይነት ያለው ስልጠና ካገኙ መጎልበት የሚችሉ እና በክህሎታቸው የተሻሉ ታዳጊ ተጨዋቾችን ለመመልከት ችላለች።

የኢምፓክት ሶከር አካዳሚ መስራች የሆነችው አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ስለ አካዳሚው አጠቃላይ ሁኔታ ከሶከር ጋር ባደረገችው ቆይታ ለመመስረት ያነሳሳትን ምክንያት ትገልጻለች፡፡

” ከዚህ ቀደም ይሰራ የነበረው የታዳጊዎች ፕሮጀክት በመቋረጡ እና ተተኪ ወጣቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠፉ ስለሆነ ቢያንስ ይህን ችግር በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ ነው የተቋቋመው፡፡

“በኢትዮዽያ እግር ኳስ ውስጥ ታዳጊዎች በአካዳሚ በመግባት ሳይንሳዊ የሆነ ስልጠና እያገኙ የሚያድጉ ውስን በመሆናቸው በአሁን ሰአት በተለያዩ ቦታዎች አካዳሚዎች በመከፈት ታዳጊዎች ወደ ዘመናዊ አሰለጣጠን እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህ መሆኑ የጎላ ጠቀሜታ ስላለው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

“በአካዳሚው የሚገኙ ታዳጊዎች ከስልጠና ባሻገር አቅማቸውን ለማሳደግ ስራዎችን እየሰሩ እንደሆነ መሰረት ትናገራለች፡፡ ” ድሬዳዋ ላይ በሚዘጋጁ ውድድሮችም ሆነ ከሌሎች መሰል አካዳሚዎች ጋር ግኑኝነት በመፈጠር ተዟዙሮ የመጫወት እቅድ አለን፡፡ ወደ ፊት ከሜዳ ላይ ስልጠና በተጨማሪ ምድር ባቡር በሚገኘው ሁለት ክፍሎች ውስጥ ተጨማሪ በቂ የሆነ ዕውቀት ይዘው እንዲወጡ የቀለም ትምህርት እንዲሁም ከእግር ኳሱ በተያያዘ የስነ ልቦና ትምህርት እንዲያገኙም እናደርጋለን፡፡ ”

በኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በርካታ የታዳጊዎች ማሰልጠኛዎች እየተጀመሩ በአቅም ማነስ ሲቋረጡ ይታያል፡፡ የኢምፓክት አካዳሚም የሌሎቹ እጣ እንዳይደርሰው ከተለያዩ አካላት ድጋፍ እየተደረገለት እንደሚገኝ አሰልጣኝ መሰረት ትገልጻለች፡፡
” እስካሁን ባለው ሁኔታ የከተማው ከንቲባ ፅህፈት ቤት እና የሌሎች ቢሮ ኃላፊዎች ፣ ባላሀብቶች ፣ የድሬደዋ እግር ኳስ ክለብ ለታዳጊዎቹ ትጥቆች በመስጠት ድጋፍ እያደረጉልን በመሆኑ ምስጋናዬን አቀርባለው፡፡ ወደ ፊት ከድሬደዋ ከተማ ስፖርት ክለብ ጋር በመነጋገር ክለቡ ለሚያቋቁመው ከ17 አመት በታች ቡድን በዚህ አካዳሚ የሚገኙት ታዳጊዎች በግብአትነት ለመጠቀም እቅድ አለ፡፡ አካዳሚያችን የራሱ ሜዳ እንዲኖረው ፣ በሌሎች የእድሜ እርከኖች ስልጠናውን የማስፋት ሀሳብም አለን፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *