​የኢትዮዽያ አንደኛ ሊግ በሀምበሪቾ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ከሐምሌ 8-16 ድረስ በድሬደዋ ከተማ አስተናጅነት በስድስት ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የቆየው የአንደኛ ሊግ የማጠቃልያ ውድድር ዛሬ በደማቅ ሁኔታ ፍፃሜውን አግኝቷል።

አቶ አስራት ጫላ የከንቲባ ፅህፈት ቤት ተወካይ ፣ አቶ ከድር ጁሀር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ፣ አቶ አበበ ገላጋይ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ፍፃሜ ውድድር አስቀድሞ በተደረገ የደረጃ ጨዋታ መቂ ከተማ የካ ክፍለከተማን በመለያ ምቶች አሸንፎ 3ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡

ጨዋታው እምብዛም ጠንካራ ፉክክር ያልተደረገበት ሲሆን የጎል ሙከራ በማድረግ የካዎች የተሻሉ ነበር። ጨዋታው በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ግብ አለመሰተናገዱን ተከትሎ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡ የመለያ ምቶች መቂ ከተማ 5-4 ማሸነፍ ችሏል።

10:00 ላይ ሀምበሪቾን ከ ደሴ ከተማ ባገናኘው የፍጻሜ ጨዋታ ሀምበሪቾ 2-0 በማሸነፍ የውድድሩ አጨቃላይ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በዚህ የማጠቃለያ ውድድር ላይ በምድብ ጨዋታ ተገናኝተው ሀምበሪቾ 5-2 ማሸነፉ ይታወሳል።

የፍፃሜ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን ጠንካራ ፉክክር ባስተናገደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ሀምበሪቾዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በውድድሩ ጠንካራ አጥቂ መሆኑን ያሳየው ቢንያም ጌታቸው በተደጋጋሚ ያገኘውን አጋጣሚ ባይጠቀምም 24ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረው ኳስ ተሞክሮ የግቡ አግዳሚ ሲመልሰው በመመታት ሀምበሪቾን ቀዳሚ አድርጓል፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላም ጫና ፈጥረው የተንቀሰቀሱት ሀንበሪቾዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ጎል የሚያስቆጥሩበትን አጋጣሚ በፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ሚሊዮን ሰለሞን መትቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የመጀመርያው አጋማሽም በሀምበሪቾ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ደሴዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የጎል አጋጣሚ እሱባለው አንለይ እና ዳዊት ክፍሌ አማካኝነት ቢያገኙም ያልተጠቀሙባቸው ኳሶች የሚያስቆጩ ነበር። 71ኛው ደቂቃ ላይ የሀምበሪቾ ግዙፉ አንበል እና ተከላካይ እንዳለ ዮሀንስ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት የሀምበሪቾን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።

ጨዋታው በቀሩት 19 ደቂቃዎች ከዝቀዝ ብሎ ቀጥሎ ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በሀምበሪቾ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የዱራሜው ክለብም የ2009 የአንደኛ ሊግ የማጠቀለያ ውድድር አሸናፊ ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ የሽልማት ስነስርአት ቀጥሎ የተደረገ ሲሆን መቂ ከተማ ሦስተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ የነሐስ ሜዳልያ ፣ ደሴ ከተማ ሁለተኛ በመውጣቱ የብር ሜዳልያ እንዲሁም ሀምበሪቾ አንደኛ ሆኖ በማጠናቀቁ የወርቅ ሜዳልያ እና የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል። በየምድባቸው አንደኛ በመሆን ያጠናቀቁት ሚዛን አማን ፣ ቡታጅራ ከተማ ፣ ደሴ ከተማ ፣ መቂ ከተማ እና የካ ክፍለከተማም የተዘጋጀላቸውን ዋንጫ አንስተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *