ኡመድ ለስሞሀ ባደረገው የመጀመርያ ጨዋታ የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ አስቆጥሯል

የ2017/18 የግብፅ ፕሪምየር ሊግ አርብ ሲጀመር በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሰኞ ምሽት ከሜዳው ውጪ ኤንፒን የገጠመው ስሞሃ በኡመድ ኡኩሪ ግብ ነጥብ ተጋርቷል፡፡ ኡመድ ኡኩሪም በቅርቡ ለተዛወረበት ስሞሀ ባደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ጎል አስቆጥሯል፡፡

ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ስሞሃ በመጀመሪያው አጋማሽ ቀዳሚ ቢሆንም ባለሜዳዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡

በፔትሮስፖርት ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በፈጣን እንቅስቃሴ እንግዶቹ ወደ ግብ በመድረስ ተሽለው የታዩ ሲሆን በ33ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል የመጣውን ኳስ በፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ የግራ መስመር ላይ የነበረው ራጋብ ባክር አግኝቶ ወደ ግብ ሲልክ ከግቡ በቅርብ ርቀት የነበረው ኡመድ አስቆጥሮ ስሞሃን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ኡመድ ለስሞሃ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢን ለቆ የተቀላቀለ ሲሆን ለክለቡ ባደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በሁለተኛው 45 ኤንፒዎች በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን ግብ እንዲያስቀጥሩ አስችሏቸዋል፡፡ በ50ኛው ደቂቃ አምር ኤል-ሃላዋኒ የሞከረውን ኳስ የስሞሃው ግብ ጠባቂ መሃመድ አቡ ጋባል ሲተፋው ለግቡ ቅርብ የነበረው ሃምዲ ፋቲ አስቆጥሮ ቡድኖቹ አቻ ሁነዋል፡፡ በ57ኛው እና 70ኛው ደቂቃዎች ኡመድ ያገኛቸውን እድሎች ሲያመክን ኤንፒን በጨዋታው መገባደጃ ላይ አሸናፊ ልታደርግ የምትችል እድል መሃመድ ባሶኒ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ኡመድ በ70ኛው ደቂቃ ላይም ከግብ ጠባቂው አሊ ሎትፊ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ሎትፊ ሙከራውን አምክኖበታል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ኡመድ በቀኝ መስመር አማካይ ሆኖ ሲሰለፍ በ49ኛው ደቂቃ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል፡፡

ኡመድ በ2015/16 ለአንድ የውድድር ዘመን በኤንፒ ያሳለፈ ሲሆን ቆይታው መልካም የሚባል አለመሆኑን ተከትሎ ወደ ኤንታግ ኤል ሀርቢ ተዛውሮ ድንቅ አመት ማሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡

አርብ እለት ሽመልስ በቀለ ሙሉ ደቂቃውን በተሰለፈበት ጨዋታ ፔትሮጀት ከሜዳው ውጪ ከኤል ዳክልያ ጋር 1-1 ተለያይቷል፡፡ ቻምፒዮኑ አል አሃሊ በታላል ኤል ጋይሽ በሜዳው ነጥብ ሲጥል ዛማሌክ ከሜዳው ውጪ ከኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ጋር አቻ ተለያይቷል፡፡ በመጀመሪያው ሳምንት ኢስማኤሊ፣ አል መስሪ እና አረብ ኮንትራክተርስ ድል የቀናቸው ብቸኞቹ ክለቦች ናቸው፡፡

በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሐሙስ ሲጀምሩ ፔትሮጀት አል መስሪን ፤ እሁድ ስሞሃ ታንታን ይገጥማሉ፡፡

የኡመድን ጎል ይመልከቱ | You Tube Link

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *