የሶከር ኢትዮጵያ “የአመቱ የእግርኳስ ሰዎች/ተቋማት ሽልማት” – 2009

ሶከር ኢትዮጵያ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለአዲሱ አመት 2010 በሰላም አደረሳችሁ እያለች ለሶስተኛ ጊዜ ያዘጋጀችው የአመቱ የእግርኳስ ሰዎች/ተቋማት ሽልማትን አሰናድታለች፡፡ በዚህ ፅሁፍም ስለ ሽልማቱ ፣ የምርጫ መስፈርት ፣ እጩዎች እና ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ታቀርባለች፡፡

ስለ ሽልማቱ

ይህ ሽልማት በአንድ አመት ውስጥ በእግርኳሱ ተፅእኖ ለፈጠሩ ግለሰቦች የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡ በሜዳ ውስጥ ውጤታማነታቸውን ካሳዩ ባሻገር በአጠቃላይ እግርኳሱ ላይ የሚገኙ ማናቸውም ግለሰቦች በዚህ ሽልማት ውስጥ ይካተታሉ፡፡

ከነዚህም መካከል
ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች ፣ ዳኞች ፣ የህከምና
ባለሙያዎች ፣ የአስተዳደር ሰዎች ፣ የሚድያ ባለሙያዎች ፣ ደጋፊዎች ፣ በጎ ፍቃደኞች እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

በሜዳ ላይ ድንቅ አቋም የሳየ ተጫዋች ፣ ውጤታማ አመት ያሳለፉ አሰልጣኞች እና ባለሙያዎች ፣ እግርኳሱን አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ አስተዋጽኦ ያደረጉ ፣ ከዚህ ቀደም ያልታየ አዲስ ነገር ያሳዩ ወይም ግኝት ያገኙ ፣ ለችግሮች መፍትሄ የሰጡ እና የመሳሰሉት ለሽልማቱ እንደ መስፈርትነት ያገለግላሉ፡፡

የውድድሮች ደረጃ እና የሀገሪቱ የእግርኳስ እርከኖች ለሽልማቱ አንድ መስፈርት ናቸው፡፡ ለምሳሌ በኢንተርናሽናል ውድድር እና ከኢትዮጵያ በደረጃቸው ከፍ ባሉ የሊግ ውድድሮች ውጤታማ መሆን ፣ የብሔራዊ ቡድን ስኬት እና የሀገር ውሰጥ የሊግ እርከኖች እንደየደረጃቸው የየራሳቸው ክብደት ይኖራቸዋል፡፡

ያለፉ አሸናፊዎች

በ2007 በተደረገው ምርጫ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ የመጀመርያዋ ሴት አሰልጣኝ ለመሆን የበቃችው መሰረት ማኒ አሸናፊ ሆናለች፡፡ ቀጥሎ በተካሄደው የ2008 ምርጫ ደግሞ በወንዶች እግርኳስ ዘርፍ ጌታነህ ከበደ ፤ በሴቶች እግርኳስ ደግሞ ሎዛ አበራ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ዘርፍ

ይህ ሽልማት በ2007 ሲጀመር ዘርፉ አንድ የነበረ ሲሆን በሁለቱም ፆታ የሚገኙ ግለሰቦች አንድ ላይ ተወዳድረዋል፡፡ በ2008 የሽልማት አመት ዘርፉ ወደ ሁለት ከፍ ብሎ በወንዶች እግርኳስ አና ሴቶች እግርኳስ በሚል ተከፍሏል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ዘርፉ ወደ 4 ከፍ ብሎ የወጣቶች እግርኳስ እና ተቋማት/ክለቦች ዘርፍ ለብቻቸው ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

የወንዶች እግርኳስ

በዚህ ዘርፍ በወንዶች እግርኳስ ተፅእኖ የፈጠሩ ግለሰቦች ይሸለማሉ፡፡ በሁለቱም ጾታ ያሉ ግለሰቦች በወንዶች እግርኳስ ላይ እስካሉ ድረስ አሸናፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

-ለምሳሌ የወንድ ቡድንን የምትመራ ሴት አሰልጣኝ በዚህ ዘርፍ ትወዳደራለች፡፡

የሴቶች እግርኳስ

በዚህ ዘርፍ በሴቶች እግርኳስ ተፅእኖ የፈጠሩ ግለሰቦች ይሸለማሉ፡፡ በሁለቱም ጾታ ያሉ ግለሰቦች በሴቶች እግርኳስ ላይ እስካሉ ድረስ አሸናፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

-ለምሳሌ የሴቶች ቡድንን የሚመራ ወንድ አሰልጣኝ በዚህ ዘርፍ ይወዳደራል፡፡

የወጣቶች እግርኳስ

በዚህ ዘርፍ ውስጥ በወጣቶች ውድድሮች ላይ ውጤታማ የሆኑ ግለሰቦች ፣ ለወጣቶች እና ለታዳጊዎች እግርኳስ እድገት መልካም ስራ የሰሩ ፣ በእግርኳስ መጀመርያ ወቅታቸው ላይ ረጅም ርቀት መጓዝ የቻሉ ወጣቶች በዚህ ዘርፍ ይካተታሉ፡፡

ክለቦች / ተቋማት ዘርፍ

በዚህ ዘርፍ በአመቱ ስኬታማ ጊዜ ያሳለፉ እና በእግርኳሱ የተለየ በጎ ተፅዕኖ የፈጠሩ ክለቦች ፣ በእግርኳሱ ውስጥ የጎላ ተፅእኖ የፈጠሩ ተቋማት እውቅና የሚሰጥበት ዘርፍ ነው፡፡

ድምፅ አሰጣጥ

በዚህ ሽልማት 70% ድምጽ የሚሰጡት የሶከር ኢትዮጵያ ኤዲቶርያል አባላት ሲሆኑ የድረ ገፃችን አንባቢያን ድምፅ 30% ይይዛል፡፡

ስለ እጩዎች

የወንዶች እግርኳስ ዘርፍ

ሳላዲን ሰኢድ

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ለክለቡ ስኬታማ የውድድር አመት ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ በተለይም በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምድብ ድልድል ውሰጥ እንዲገባ እና በምድቡም ተፎካካሪ እንዲሆን የሳላዲን 7 ጎሎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ፈረሰኞቹ ለ4ኛ ተከታታይ አመታት የሊጉን ዋንጫ ከፍ ሲያደርጉም ወደ ቻምፒዮንነት ለማንደርደር እጅግ ወሳኝ የሆኑትን ጎሎች ጨምሮ 15 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

ጌታነህ ከበደ

የአምናው የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ ሰዎች/ተቋማት አሸናፊ የሆነው ጌታነህ በግሉ ግሩም አመት አሳልፏል፡፡ 25 የሊግ ግቦችን በማስቆጠርም የሊጉን በአንድ የውድድር አመት በርካታ ግብ የማስቆጠር ሪኮርድ ከ16 አመታት በኋላ ሰብሯል፡፡

ኡመድ ኡኩሪ

ከ2007 ጀምሮ በግብጽ ሊግ እየተጫወተ የሚገኘው ኡመድ እንደዘንድሮው ስኬታማ ጊዜን አላሳለፈም፡፡ ወደ ስሞሀ ክለብ የተዛወረው ኡመድ በኤንታግ ኤል ሀርቢ የውድድር አመት ቆይታው የክለቡ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል፡፡

ሴቶች እግርኳስ ዘርፍ

ሰናይት ቦጋለ

በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ብዙዎችን ያሳመነ ምርጥ የውድድር አመት አሳልፋለች፡፡ ደደቢት ለተከታታይ አመታት የሊጉ ቻምፒዮን እና የጥሎ ማለፉ የፍጻሜ ተፋላሚ እንዲሆን የአጥቂ አማካይዋ ሰናይት ሚና የጎላ ነበር፡፡

ሎዛ አበራ

የ2008 ” የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ የእግርኳስ ሰዎች/ተቋማት” ተሸላሚ የሆነችው ሎዛ ለተከታታይ 3ኛ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ደደቢትን ለቻምፒዮንነት አብቅታለች፡፡ በሴካፋ የሴቶች ዋንጫ መልካም ጊዜ ያሳለፈችው ሎዛ ወደ ቱርክ በማቅናትም የሙከራ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ትገኛለች፡፡

ዮሴፍ ገብረወልድ

የሀዋሳ ከተማ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ዮሴፍ ገብረወልድ በወጣቶች የተገነባ ቡድን በመስራት በሊጉ ተፎካካሪ መሎን ችሏል፡፡ በምድቡ ኢትዮጵየያ ንግድ ባንክን መፈተን የቻለው ሀዋሳ ጠንካራውና አመቱን ሙሉ ሽንፈት ያልቀመሰው ደደቢትን በመርታት የጥሎ ማለፍ ባለ ድል እንዲሆን የአሰልጣኝ ዮሴፍ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡

ወጣቶች እግርኳስ ዘርፍ

ተመስገን ዳና

በወጣቶች እግርኳስ ላይ ተደጋጋሚ የበላይነት እየያሳየ ከሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ጀርባ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ይገኛል፡፡ በ2008 ከ17 አመት በታች ጥምር ድል ከሀዋሳ ጋር ያሳካው ተመስገን ሙሉውን ቡድን ይዞ ወደ 20 አመት በታች በመሻገር ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገውን የ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ እነና ጥሎ ማለፍ አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል፡፡ ባለፉት አመታት ለዋናው ቡድን በርካታ ተጫዋቾችን ያበረከተው አሰልጣኝ ተመስገን ዘንድሮም በዚህ ተግባሩ ቀጥሏል፡፡

ቢንያም በላይ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቁ መድረክ ላይ ሁለተኛ የውድድር አመቱን ያሳለፈው ቢንያም ፈጣን እድገቱን ቀጥሎ ወደ አውሮፓ ተሻግሯል፡፡ በትጋት በርካታ የሙከራ ጊዜያት በማሳለፍ በመጨረሻም ወደ አልባንያ አምርቶ በዩሮፓ ሊግ ተሳታፊ ለሆነው ስኬለንደብሩ ክለብ ፈርሟል፡፡

አቡበከር ነስሩ

በ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጎልቶ የወጣው አቡበከር በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ለኢትዮጵያ ቡና ዋናው ቡድን በተሰለፈበት የመጀመርያ ጨዋታ ግብ አስቆጥሮ የመወያያ ርዕስ መሆን ችሏል፡፡ የወደፊቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ኮከብ የመሆን እምቅ አቅም እንዳለውም በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች አሳይቷል፡፡

በተቋማት / ክለቦች ዘርፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ

2009 ቅዱስ ጊዮርጊስ በ81 አመት ታሪኩ ከሚጠቀሱ ስኬታማ አመታት መካከል ያሳለፈበት ሆኖ አልፏል፡፡ በክለቡ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ 4ኛ ተከታታይ አመታት የሊግ ቻምፒዮን ሲሆን በሀገራችን ክለቦች የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ምድብ ድልድል ገብቷል፡፡ ከሁሉም በላይ በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስም የተሰየመውና በክለቦቻችን ታሪክ የመጀመርያ የሆነው የታዳጊዎች አካዳሚን አጠናቆ ያስመረቀው በ2009 አመት ነው፡፡

ኮካ ኮላ

በሀገሪቱ እግርኳስ ላይ እንደችግር የሚጠቀሰው ለታዳጊዎች የመጫወት እድል የሚሰጥ የውድድር እጥረትን ለመቅረፍ እየሰሩ ከሚገኙ ተቋማት መካከል ኮካ ኮላ ይጠቀሳል፡፡ እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን በሁለቱም ጾታ የሚያሳትፈውና በመላ ሀገሪቱ ከ1500 በላይ ትምህርት ቤቶች 27 ሺህ ታዳጊዎችን እግርኳስ የመጫወት ህልማቸውን እንዲያሳኩ የረዳው ኮፓ ኮካ ኮላን በማዘጋጀት ኮካ ኮላ ለኢትዮጵያ እግርኳስ የበኩሉን እየወጣ ይገኛል፡፡

ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ

ባለፉት 10 አመታት በርካታ ቁጥር ያለው ግዙፍ ስታድየሞች እየተገነቡ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የወልድያው መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም ብቻ ነው፡፡ ይህን ዘመናዊ ስታድየም በ2009 ሙሉ ለሙሉ አጠናቆ ያስረከበውና ወጪውን ሙሉ ለሙሉ የሸፈነውም የሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ድርጅት በሆነው ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *