​ቻምፒየንስ ሊግ፡ ዩኤስኤም አልጀር ከዋይዳድ ካዛብላንካ በግማሽ ፍፃሜው ይገናኛሉ

አራት የሰሜን አፍሪካ ሃገራት ክለቦች ብቻ በቀሩበት የ2017 የካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ፡፡ የአልጄሪያው ዩኤስኤም አልጀር የሞሮኮውን ዋይዳድ ካዛብላንካን በሜዳው የሚያስተናግድበት ጨዋታ ዛሬ ይጠበቃል፡፡
የ2015 የቻምፒየንስ ሊጉ የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረው ዩኤስኤም ከሁለት ዓመት ቆይታ በኃላ ለግማሽ ፍጻሜው አልፏል፡፡ በሙሉ ስሙ ዩኒየን ስፖርቲቭ ደ ላ መዲና ደ አልጀር ተብሎ የሚጠበቀው የአልጄሪያ መዲና ክለብ የአፍሪካ ክለብ ውድድሮች አሸንፎ የማያውቅ ሲሆን በአልጄሪያ የክለቦች ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ እና ከስኬታማ ክለቦች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ የዩኤስኤም ተጋጣሚ ዋይዳድ በበኩል ቻምፒየንስ ሊጉ በ1992 ካነሳ በኃላ በ2016 ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰበት ውጤት ትልቁ ውጤት ነው፡፡

ሁለቱም ክለቦች ወጥ ባልሆነ አቋም የውድድር አመቱን የጀመሩ ሲሆን በሩብ ፍፃሜው ዩኤስኤም የሞዛምቢኩን ፎሬቫያሪዮ ደ ቤይራ እንዲሁም ዋይዳድ የአምናው ቻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከውድድር ውጪ አድርገዋል፡፡ ዩኤስኤም አልጀር በሁሉም ውድድሮች ያደረጋቸውን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲፈፅም ዋይዳድ በበኩሉ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በሁለት ተሸንፎ አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ችሏል፡፡ በቤልጅየማዊው የቀድሞ የቡርኪና ፋሶ አሰልጣኝ ፖል ፑት የሚመራው ዩኤስኤም ከኤንኤ ሁሴን ዴይ፣ ዲአርቢ ታጅናት እና ፎሬቫያሪዮ ቤይራ ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ነው ማጠናቀቅ የቻለው፡፡ ዋይዳድ ካዛብላንካ በቡሉ በፉስ ራባት 3-1 በሞሮኮ ሊግ መክፈቻ ሲሸነፍ፣ ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ፕሪቶሪያ ላይ ተሸንፎ በመልሱ ጨዋታ ራባት ላይ አሸንፏል፡፡

ከዩኤስኤም አልጀር በኩል ስድስት የቻምፒየንስ ሊግ ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው ኦሳማ ዳርፎሎ ሲጠበቅ የዋይዳዱ መሃመድ ኦንዠም በጨዋታው ለውጥ ይፈጥራል ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡

የዛሬ ጨዋታ (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር)

2፡00 – ዩኤስኤም አልጀር ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ስታደ ጁላይ 5 1962)

እሁድ

2፡30 – ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል ከ አል አሃሊ (ስታደ ኦሎምፒክ ደ ሶስ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *