ሩሲያ 2018፡ ግብፅ ከ27 ዓመታት በኃላ ወደ ዓለም ዋንጫ አልፋለች

እሁድ በተደረገ ብቸኛ የፊፋ ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ብቸኛ የማጣሪያ ጨዋታ ግብፅ ወደ ሩሲያ ያመራችበትን ውጤት ኮንጎ ብራዛቪልን 2-1 በማሸነፍ ማግኘት ችላለች፡፡

በቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የግብፅ መንግስት ፍቃድ መስጠቱን ተከትሎ በርካታ የባለሜዳው ደጋፊዎች ጨዋታውን በስታዲየሙ የተከታተሉ ሲሆን በመጀመሪያው 45 ተመጣጣኝ ፉክክር ከሁለቱም ቡድኖችን ታይቷል፡፡ በተለይ ኮንጎዎች በጠንካራ መከላከል እና አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ባለሜዳዎቹን መፈተን ችለዋል፡፡ አምበሉ ፕሪንስ ኦኒያንጉ ከረጅም ርቀት የመታው ኳስ ኢላማውን መጠበቅ ሳይችል ሲወጣ ግብ ጠባቂው ባሬል ሞኩ የአህመድ ሄጋዚን ሙከራ ማምከን ችሏል፡፡ ድዞን ንዲንጋ ኳስ እና መረብን ማገናኘት የሚችልበትን ሙከራ ኳስ በሄጋዚ ተጨርፋ በግቡ አናት ወጥታለች፡፡

በሁለተኛው 45 ፈርኦኖቹ በመሃመድ ሳላህ የ63ኛ ደቂቃ ግብ መሪ መሆን ሲችሉ ከግቡ መቆጠር በኃላ ኮንጎ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዳለች፡፡ ቢሆንም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ለማድረግ ግን አልቻሉም ነበር፡፡ በመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ ሳላህ ሞክሮ ሞኩ ሲያድንበት በ88ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገለትን ኳስ አርኖልድ ቦካ ሞቱ አስቆጥሮ በስታዲየሙ የተገኘውን ደጋፊ ዝም አስብሏል፡፡ ሆኖም በጨዋታው መገባደጃ ላይ ጋምቢያዊው ሁለት ግዜ የካፍ የዓመቱ ምርጥ አርቢት ክብርን ያገኙት ባካሪ ፓፓ ጋሳማ የሰጡትን አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምት ልማደኛው ሳላህ አስቆጥሮ ግብፅ የሩሲያ ትኬቷን ቆርጣለች፡፡

ውጤቱን ተክተሎ የምድብ አምስት ሳትጠበቅ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረችው ዩጋንዳ ከማጣሪያው ውጪ ሆናለች፡፡ ምድቡን ግብፅ በ12 ነጥብ ስትመራ ዩጋንዳ በ8፣ ጋና በ6 እንደሁም ኮንጎ በ1 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

እስካሁን በተደረጉ የምድብ ጨዋታዎች ናይጄሪያ እና ግብፅ ብቻ ወደ ዓለም ዋንጫው ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሃገራት ናቸው፡፡ ቱኒዚያ ለማለፍ ከጫፍ የደረሰች ሲሆን ሞሮኮ እና ኮትዲቯር በምድብ ሶስት ተፋጠዋል እንዲሁም የምድብ አራት አላፊ እስካሁን አልታወቀም፡፡ ለማለፍ ሴኔጋል የተሻለ እድልን የያዘች ሲሆን ደቡብ አፍሪካ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቨርድም የማለፍ ተስፋቸውን አሁንመ አለ፡፡

የአርብ ውጤት

ማሊ 0-0 ኮትዲቯር

የቅዳሜ ውጤቶች

ደቡብ አፍሪካ 3-1 ቡርኪና ፋሶ

ዩጋንዳ 0-0 ጋና

ናይጄሪያ 1-0 ዛምቢያ

ካሜሮን 2-0 አልጄሪያ

ጊኒ 1-4 ቱኒዚያ

ሊቢያ 1-2 ዲ.ሪ. ኮንጎ

ኬፕ ቨርድ 0-2 ሴኔጋል

ሞሮኮ 3-0 ጋቦን

የእሁድ ውጤት

ግብፅ 2-1 ኮንጎ ሪፐብሊክ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *