ናኖል ተስፋዬ – በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች እይታ ውስጥ የገባው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ታዳጊ

በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነው እና ኑሮውን በስዊድን ያደረገው የ14 አመቱ ናኖል ተስፋዬ (በቅጽል ስሙ ናኒ) በተለያዩ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ራዳር ውስጥ እንደገባ ኦ-ፖስትስ የተሰኘው የእግር ኳስ ድረ ገጽ አስነብቧል። 

እንደ ድረ-ገፁ መረጃ ታዳጊውን የቀኝ መስመር ተከላካይ ለማዘዋወር ፍላጎት ካሳዩ ክለቦች መካከል የእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ መሪ የሆነው ማንችስተር ሲቲ አንዱ ሲሆን የቀድሞው ሃያል ክለብ ሊድስ ዩናይትድ ተጫዋቹ ላይ ፍላጎት ያሳደረ ሌላኛው ክለብ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የእግርኳስ ህይወቱን በስዊድን በሚገኘው ቫሳሉድ አካዳሚ የጀመረው ናኖል በ2016 ወደ አይኤፍ ስቶክሆልም አካዳሚ በማቅናት የአንድ ዓመት ቆይታ የነበረው ሲሆን ያለፉትን ወራት ወደ ቫሳሉድ ተመልሶ ለ15 አመት በታች ቡድኑ ተጫውቷል። በአሁኑ ወቅትም ቀጣይ ማረፊያውን ለመወሰን ከበርካታ ክለቦች ጋር በድርድር ላይ ይገኛል።

ናኖል ትውልድ እና ዕድገቱ በስዊድን ሲሆን ከኢትዮጵያውያን ወላጆች መገኘቱ ከሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ምርጫው ላደረገው የመጫወት አጋጣሚን ፈጥሮለታል። ኦ-ፖስትስ ድረገፅ እንዳስነበበው ከሆነ የ14 ዓመቱ ታዳጊ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አባል ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለው።

ተስፈኛው ታዳጊ በእግርኳስ ህይወቱ ዙሪያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ስለ እግር ኳስ ጅማሬህ ጥቂት ንገረን

ያው ተወልጄ ያደኩት ስዊድን ነው፡፡ እዛም ባሉ የ9 እና 10 አመት በታች አካዳሚዎች ውስጥ በመግባት ነው የጀመርኩት፡፡

ወደ ኢትዮጵያ መጥተህ ታውቃለህ?

አዎ። ምንም እንኳን ኑሮዬ ስዊድን ቢሆንም ወደተለያዩ ሀገራት በእረፍት ወቅት እሄዳለሁ፤ ወደ ኢትዮጵያም የመሄድ ዕድሉን አግኝቻለሁ።

በልጅነትህስ እንደ አርአያ ትመለከታቸው የነበሩ ተጫዋቾች አሉ? አጨዋወትህስ ከማን ጋር ይመሳሰላል?

አጨዋወቴን ማመሳሰል ካስፈለገ እንደ ማርሴሎ ወይም ሄክተር ቤለሪን አይነት ነው፡፡ እንደ አርአያ እየተመለከትኳቸው ያደኩት ግን ዲዲዬ ድሮግባ እና ፈርናንዶ ቶሬስን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአንተ ላይ ፍላጎት አሳድሯል የሚባለው ምን ያህል እውነት ነው? ከፌደሬሽኑ ጋርስ በዚህ ጉዳይ አውርተሃል?

ከኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳለ ሰምቻለው ነገር ግን እስካሁን በቀጥታ ቀርቦ ያናገረኝ ሰው የለም።

ወደፊት በእግርኳስ ህይወትህ ምን ለማሳካት አቅደሀል?
ወደፊት በአውሮፓ ባሉ ታላላቅ ክለቦች ለመጫወት ነው አላማዬ፡፡ ከእንግሊዝ የዝውውር ጥያቄዎች ቀርበውልኛል፤ ነገር ግን በአሁን ሰዓት በድርድር ላይ ስለምገኝ ቀጣይ ክለቤን ማሳወቅ አልችልም።

ጊዜ ወስደህ ለጥያቄዎቻችን መልስ ስለሰጠህ እናመሰግናለን፡፡
እኔም አመሰግናለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *