​ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት የቅዳሜ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ድሬደዋ ከተማን እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ ደደቢት ሲዳማ ቡናን የሚያስተናግዱባቸው ጨዋታዎች የሉጉ ሰባተኛ ሳምንት መክፈቻዎች ናቸው። ሁለቱን ጨዋታዎች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።


ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬደዋ ከተማ

ድሬደዋ እና ሀዋሳ በዕኩል ሰባት ነጥቦች በሰባተኛ እና ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። አስገራሚው ነገር እስካሁን ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠር የቻለው ድሬደዋ በግብ ክፍያ የተሻለ መሆኑ ነው። ድሬደዋዎች ያስተናገዱት አንድ ግብ ብቻ መሆኑ አንድ ንፁህ ግብ እንዲኖራቸው አርጓል። በአንፃሩ ሰባት ግቦችን በማስቆጠር በሊጉ በርካታ ግብ ካስቆጠሩ ሁለት ቡድኖች መሀል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማ በተመሳሳይ ሰባት ግቦች በመረቡ ላይ ማረፋቸው የግብ ልዩነቱን ዜሮ አድርጎታል። ይህ ነጥብ ጨዋታው በሊጉ በማጥቃት ረገድ ግምባር ቀደም የሆነውን እና ከመከላከል አጨዋወት ጋር ስሙ የማይለየውን  ክለብ የምይንገናኝ ያደርገዋል። በፌ/ዳኛ አሰፋ ደቦጭ የመሀል ዳኝነት የዛሬውን ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ቡድኖቹ በስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀዋሳ አዲስ አበባ ላይ ከመከላከያ እንዲሁም ድሬደዋ ከተማ በሜዳው ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ የተለያዩ ሲሆን  አምና 13ኛው ሳምንት ላይ በሀዋሳ ሲገናኙም ያለግብ መለያየታቸውም የሚታወስ ነው።               

በሀዋሳ ከተማ በኩል አዳማ ላይ ጉዳት ያስተናገደው የመሀል ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ እና ሳዲቅ ሴቾ በጉዳት ሳቢያ ጨዋታው እንደሚያልፋቸው ሰምተናል። ጂብሪል አህመድ እና ተክለማርያም ሻንቆም የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ከጉዳት እንዳገገመ እየተነገረ የሚገኘው ዳንኤል ደርቤም ለጨዋታው ብቁ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። በአንፃሩ በድሬደዋ በኩል ጅማል ጣሰው እና ዘነበ ከበደ ብቻ በጉዳት ለጨዋታው የማይደርሱ ተጨዋቾች ናቸው።

የሁለቱ ቡድኖች አቀራረብ በግልፅ የሚታወቅ መሆኑ እና አሰልጣኝ ውበት አባተም ሆኑ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የአጨዋወት እምነታቸውን በተመሳሳይ መልኩ በየጨዋታው ሲተገብሩ መታየታቸው የዛሬውን የቡድኖቹን የእርስ በእርስ ግንኙነት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለመሳል ቀላል ያደርገዋል። በዚህም የጨዋታው አብዛኛው ሂደት በድሬደዋ የሜዳ ክፍል ላይ የሚያመዝን እና በሀዋሳዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የሚደረግ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ፍሬው ሰለሞንን ከቤሔራዊ ቡድን ቆይታ በኃላ የምያገኙት ሀዋሳዎች የማጥቃት ጉልበታቸው ይበልጥ እንደሚሻሻል እርግጥ ነው። ፊት ላይ ፍሬው ከዳዊት እና ያቡን ዊልያም ጋር የሚኖረው ጥምረት በታፈሰ ሰለሞን ከሚመራው የአማካይ ክፍል ጋር በመሆን እስካሁን አንድ ጊዜ ብቻ መረቡን ካስደፈረው የድሬደዋ ከተማ አጠቃላይ የቡድን የመከላከል እንቅስቃሴ ጋር የሚፋለም ይሆናል። ድሬደዋ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው የማጥቃት ጥንካሬ አንፃር በቀላሉ ክፍተት ከማይሰጠው የተከላካይ ክፍላቸው በተጨማሪ እንደ አናጋው ባድግ ፣ ሳውሪል ኦርሊሽ ፣ ኢማኑኤል ላርያ እና ወሰኑ ማዛ አይነት የመከላከል ባህሪ ባላቸው አማካዮች እንደሚጠቀሙ ይገመታል። ሆኖም ደካማው የሀዋሳ የተከላካይ መስመር ያለፉት ጨዋታዎች ላይ እንደታየው ስህተቶች የሚሰራ ከሆነ የድሬደዋዎች መልሶ ማጥቃት ሰለባ ሊሆን ሚችልበት ዕድል አለ። በጥቅሉ ከተጋጣሚያቸው አንፃር ጨዋታው ሀዋሳ ከተማ ያለውን የማጥቃት ሀይል እንዲሁም ድሬደዋ ከተማም የሚታወቅበትን የመከላከል ጥንካሬ ጥግ በትክክል የሚፈትሹበት ይሆናል።



ደደቢት ከ ሲዳማ ቡና 

በፌ/ዳኛ አሸብር ሰቦቃ የመሀል ዳኝነት ከሚደገረገው ከዚህ ጨዋታ በፊት ደደቢት በንፅፅር ጥሩ ሊባል የሚችል የሊግ ጉዞ ላይ ቢገኝም በሜዳው ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች መሰብሰብ የቻለው አምስት ነጥቦች ብቻ መሆኑ እና በሁለቱ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አለመቻሉ እንደ ድክመት ይነሳበታል። ሆኖም በስድስተኛው ሳምንት ከሜዳው ውጪ በሁለት ግቦች ልዩነት አሸንፎ መመለሱ ከሁለት ያለግብ ከተጠናቀቁ ጨዋታዎች በኃላ የተገኘ ድል እንደመሆኑ መጠን ቡድኑ የአሸናፊነት መንፈሱን መልሶ ለማግኘት እንደምረዳው ይታመናል። ሲዳማዎች እስካሁን የሰበሰቧቸው አምስት ነጥቦች በሙሉ በአቻ የተገኙ ናቸው። አምና እስከ ስድስተኛው ሳምንት ሶስት ጨዋታዎችን አሸንፎ ለነበረው ሲዳማ ቡና ይህ ውጤት አሳሳቢ ሊባል የሚችል ነው። ምናልባት ቡድኑ ወደዚህ ጨዋታ ይዞት የሚመጣው ጥሩ ነገር ካለ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገዱ ነው።                    

ደደቢት ጉዳት ላይ የሚገኙትን የአምበሉን ብርሀኑ ቦጋለን እና የፋሲካ አስፋውን አገልግሎት የማያገኝ ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩል መሳይ አያኖ ፣ ትርታዬ ደመቀ እና ባዬ ገዛሀኝ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል። ጉዳት ላይ የነበሩት ፈቱዲን ጀማል እና መሀመድ ኮናቴ ደግሞ ከሲዳማ ቡና በኩል ከጉዳት ያገገሙ ተጨዋቾች ናቸው።

የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታው ደደቢት በተጨዋቾች ስብስብ ደረጃ ዘንድሮ ደካማ የሚባል ቢሆንም እንደነ የአብስራ ተስፋዬ ፣ አቤል እንዳለ ፣ አቤል ያለው እና ሰለሞን ሀብቴ ያሉ ተጨዋቾች ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻሉ መምጣት ክፍተቱን እንዲሞላ እየረዳው ይገኛል። አቤል ያለውን በሴካፋ ምክንያት ሳይዝ ወደ መቐለ አቅንቶ የነበረው ቡድኑ ጌታነህን ብቻ ከፊት አድርጎ አምስት አማካዮችን በመጠቀም በተጋጣሚው ላይ የተሻለ ብልጫን መውሰድ ከመቻሉም በላይ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። የአማካይ ክፍሉ የኳስ ቁጥጥር እና የመስመር ተከላካዩ ሰለሞን ሐብቴ የማጥቃት ተሳትፎም በጨዋታው ከደደቢት በኩል የሚነሳ ጠንካራ ጎን ነበር። በፋሲሉ ጨዋታም ከአክዌር ቻሞ መቀየር በኃላ በተመሳሳይ አጨዋወት ደደቢት መሻሻል ሲታይበት ታዝበናል። ዛሬ የአቤል ያለውን መመለስ ተከትሎ አሰልጣኝ ንጉሴ ወደ ቀድሞው የቡድናቸው ቅርፅ ተመልሰው ጌታነህን እና አቤልን ከፊት ያጣምራሉ ወይስ በአሸናፊ ቡድናቸው ይቀጥላሉ የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ሆኗል። ብሔራዊ ቡድኑ ከሴካፋ ውድድር መመለሱ ከማንም በላይ ሲዳማን ተጠቃሚ ያደርገዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። የአበበ ጥላሁን ወደ ቡድኑ መመለስ ሲዳማዎች የደደቢትን ጥቃት እንዲቋቋሙ ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሰጣቸው ይታመናል። በማጥቃቱ ረገድ የአዲስ ግዳይ መኖር ደግሞ ይበልጥ ቡድኑን ተጠቃሚ ያደርገዋል። አዲስ በማጥቃት ላይ የተሻለ ተሳትፎ ካለው መስመር ተከላካይ ሰለሞን ሀብቴ ጋር የሚገናኝ መሆኑ ክፍተት ለማግኘት ዕድል የሚሰጠው ሲሆን የደደቢትን የግራ መስመር ማጥቃት የማፈን ሚናም እንዲወጣ ያደርገዋል። ሲዳማ ቡና ከአዲስ ግደይ የቀኝ መስመር በተጨማሪም የፈጣኑን የግራ መስመር አጥቂ አብዱለጢፍ መሀመድን ብቃት በሁለቱም አቅጣጫዎች የተመጣጠነ እና ተገማች ያልሆነ ጥቃት ለመሰንዘር ተጠቃሚ ያደርገዋል። የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ሲፈጠሩም የነዚህ ሁለት የመስመር አጥቂዎች ኃላፊነት ከፍ ያለ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *