ሶከር ሜዲካል | የቅድመ ዝውውር ህክምና አስፈላጊነት

እግርኳስ ተጫዋቾች ከአንድ ክለብ ወደ ሌላው የሚያደርጉት ዝውውር እውን ከመሆኑ በፊት ረጅም ሂደት ሊኖረው ይችላል። ተጫዋቹ ክለቡን እንዲቀላቀል ማግባባት፣ ከቀድሞ ክለቡ ጋር የዝውውር ሂሳብ ላይ በመደራደር መስማማት፣ ከተጫዋቹ ወኪል ጋርም በደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ከስምምነት መድረስ ዝውውሩ እንዲሳካ መደረግ ያለባቸው ነገሮች ናቸው። ነገርግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ መልክ ቢይዙም በመጨረሻ ተጫዋቹ የጤና እና አካላዊ ብቃት ምርመራውን ማለፍ ካልቻለ ዝውውሩ የመሳካቱ ዕድል የጠበበ ነው። በዛሬው የሶከር ሜዲካል አምዳችን በተለይ በምዕራቡ ዓለም የተጫዋቾች ዝውውር ሂደት እጅግ ወሳኝ አካል የሆነውን የተጫዋቾች የቅድመ-ዝውውር ህክምና ምርመራ የምንመለከት ይሆናል።
 

በቀደሙት ዓመታት ተጫዋቾች ከዝውውር በፊት የሚያደርጉት የጤና ምርመራ በአውሮፓ ሃገራት እንኳን ትልቅ ስፍራ ሳይሰጠው እንደልምድ የሚደረግ እና ግፋ ቢል ከሁለት ሰዓታት በላይ የማይፈጅ ነበር። በዝውውር ሂሳብ እና በደመወዝ በርካታ ሚሊዮን ፓውንዶች በሚወጡበት የወቅቱ የዓለም እግርኳስ ገፅታ ግን የተጫዋቾች ሜዲካል ምርመራ የማይተካ ሚና አለው።  ይህንን ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ተጫዋቹን የሚገዛው ክለብ ገንዘቡን ያፈሰሰበት ንብረቱ በጥሩ ጤንነት እና የአካል ብቃት እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ፍላጎቱ ቢኖረው አይደንቅም። ፊዚዮሩም የተባለው ዌብሳይት ባደረገው ጥናት በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ2016/17 የውድድር ዘመን ብቻ በጉዳት ምክኒያት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ላልቻሉ ተጫዋቾች ክለቦች ያወጡት የደመወዝ ክፍያ ወጪ ከ180 ሚልዮን ፓውንድ በላይ መሆኑን ስንመለከትም የምርመራውን አስፈላጊነት እንረዳለን።

 

በዝውውር ወቅት የሚደረግ የጤና ምርመራ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ ጠቀሜታው ከተጫዋቾች ይልቅ ለክለቦች ነው። ተጫዋቾች የጤና ሁኔታቸውን በምርመራው ወቅት ማረጋገጥ የሚችሉ ቢሆንም ይህንን መረጃ በፊፋ የህክምና መመሪያ መሠረት በዝውውር ውስጥ ያለፉም ሆነ በአንድ ክለብ የቀጠሉ ተጫዋቾች በሚያደርጉት ዓመታዊ የጤና ምርመራ ወቅት ሊያገኙት ይችላሉ። በአንፃሩ ክለቦች ገንዘብ ያወጡበትን ተጫዋች ጤንነት እና የአካል ብቃት በማረጋገጥ ዝውውሩን እንዲያጠናቅቁ፤ ከሚያወጡበት ገንዘብ አንፃር የሚጠበቅበትን ያህል ግልጋሎት ላይሰጥ ይቻላል ብለው ካመኑም የዝውውር ሂደቱን የሚያቋርጡበት እድል ያገኛሉ። ተጫዋቹ ከተደበቀ እና ሙሉ በሙሉ ካልዳነ ጉዳት አንስቶ እስከተለያዩ የውስጥ ህመሞች እና የልብ ችግር ድረስ የሚገኝበት ከሆነም ለክለቡ እንዳይፈርም ሊደረግ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ባልተለመደ መልኩ ክለቦች ተጫዋቾችን የኤች አይ ቪ ምርመራ እንዲያደርጉ ሲያስገድዱም ታይቷል፤ በ2016 የግብፁ ክለብ አል ኢቲሃድ አሌክሳንድሪያ ካሜሩናዊው አጥቂ ሳሙኤል ንሌንድ ኤች አይ ቪ በደሙ ውስጥ እንደሚገኝ በማረጋገጡ ምክኒያት ዝውውሩን ማቋረጡ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

 

 

ምርመራው ምን ያካታትታል?

 

ምርመራው የክለቡ ሃኪም፣ ፊዚዮቴራፒስት እና የአካል ብቃት አሠልጣኞችን ባቀፈ ቡድን የሚደረግ ሲሆን ይህ የምርመራ ቡድን ለተጫዋቹ የማለፍ ወይም የመውደቅ ውጤት አይሰጥም። ይልቁንም የክለቡ አሠልጣኝ እና አስተዳደር የተጫዋቹ ዝውውር ላይ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ለማገዝ በተጫዋቹ ጤና ዙርያ አስፈላጊውን መረጃ መስጠት የምርመራው ቡድን ሃላፊነት ነው። ይህም ማለት የምርመራው ውጤት ተጫዋቹ ‘ጤነኛ ነው’ ወይም ‘ጉዳት ላይ ነው’ የሚል ሳይሆን ያለውን የጤና ሁኔታ በማስቀመጥ አሠልጣኙ እና የክለቡ አስተዳደር የተጫዋቹ መፈረምን ጉዳት እና ጥቅም አመዛዝነው ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ የሚረዳ ነው ማለት ነው።

 

እያንዳንዱ ተጫዋች ይለያያል፤ የእያንዳንዱ ተጫዋች ጤና እና የህክምና ታሪክ የተለያየ እንደመሆኑ የሚደረገውም የጤና ምርመራ ይለያያል። የክለቡ ፍላጎት፣ የአሠልጣኙ መመሪያ፣ የተጫዋቹ ዕድሜ፣ የጨዋታ ስፍራ እና በፊት ያጋጠሙት ጉዳቶች ምርመራው እንዲለያይ የሚያደርጉ variables ናቸው። ምርመራው አብዛኛውን ጊዜ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ያጠቃልላል።

 

  1. የጤና ታሪክ ግምገማ እና አካላዊ ምርመራ

የጤና ምርመራው የመጀመሪያ step የተጫዋቹን የጤንነት እና ህመም ታሪክ መገምገም ነው። የቡድኑ ሃኪም ተጫዋቹ ከዚህ በፊት ያጋጠመውን ህመም፣ ያደረገውን ቀዶ ጥገና እና የደረሰበትን ስፖርታዊ ጉዳት ከመመዝገብ በተጨማሪ ከቀድሞ ክለቡ የተላከውን የተጫዋቹ የጤና መዝገብ በመከለስ አጠቃላይ የጤንነት ታሪኩን ያዋቅራል።

 

ከዚህም በመቀጠል ተጫዋቹ አጠቃላይ አካላዊ ምርመራ ይደረግለታል። የተጫዋቹ ቁመት፣ ክብደት፣ የሰውነት ስብ መጠን፣ የሳምባ አቅም፣ የልብ ምት እና የደም ግፊት ምርመራዎች የዚህ አካል ናቸው። የተጫዋቾች የዕይታ፣ የማዳመጥ ችሎታ እና የጥርስ ጤና ምርመራዎችም በበርካታ ክለቦች የቅድመ ዝውውር ምርመራ የሚካተቱ ናቸው። እንደ ተጫዋቹ የጤና ታሪክ እና አካላዊ ምርመራ ውጤትም ተጨማሪ የላብራቶሪ እና radiologic ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ። የደም እና ሽንት ምርመራ፣ ከወገብ በታች ያሉ የሰውነት አካላት ኤም አር አይ (MRI) ምርመራ እና የልብ ምርመራዎች በተለያዩ ምክኒያቶች ይታዘዛሉ።

 

በልብ ችግር ምክንያት በጨዋታ መሃል የሚያጋጥሙ እስከ ሞት ድረስ የሚያደርሱ አደጋዎች በዓለም እግርኳስ በተደጋጋሚ በመታየታቸው ምክኒያት የኤሌክትሪክ የልብ ምት ምርመራ (ECG) እና የልብ አልትራሳውንድ (Echocardiography) ምርመራዎች በአሁኑ ሰዓት የቅድመ ዝውውር ጤና ምርመራዎች ቋሚ አካል ሆነዋል።

 

  1. የጡንቻ እና አጥንት (Musculoskeletal) ብቃት ምርመራ

የቡድኑ ሃኪም እና ፊዚዮቴራፒስት የተጫዋቹን እያንዳንዱ መገጣጠሚያ እንቅስቃሴ በመመርመር ጉዳት አለመኖሩን ያረጋግጣሉ። የተጫዋቹን እንቅስቃሴ በመመልከትም ጡንቻዎቹ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመኖሩን ይመረምራሉ። ሀኪሞቹ በዚህ ምርመራ ወቅት ለተጫዋቹ እንቅስቃሴ ተቃራኒ የሆነ ሃይል በመፍጠር የሰውነት ጡንቻዎቹን ጥንካሬ የሚለኩ መሳሪያዎችን (Isokinetic Devices) ይጠቀማሉ።

 

  1. የሰውነት ስብ መጠን ምርመራ

አንዳንድ ክለቦች በተጫዋቹ ሰውነት ውስጥ የኤሌክትሪክ signal በመላክ የሰውነቱን የስብ መጠን የሚለካ ቴክኖሎጂ (Bioelectrical Impendance Technology) ይጠቀማሉ። አብዛኞቹ ፕሮፌሽናል የእግርኳስ ተጫዋቾችም የሰውነታቸው የስብ መጠን ከ10% መብለጥ እንደሌለበት ይመከራል።

 

  1. ፍጥነት (Ergometric sprint test)

ተጫዋቾች በተወሰነ ርቀት ላይ ሲሮጡ የሚኖራቸውን ፍጥነት ይመዘግባል። ይህም ተጫዋቾቹ ሰውነታቸው በቂ ኦክስጂን በማያገኝበት ጊዜ ያላቸውን ከፍተኛ የእንቅስቃሴ አቅም (Anaerobic Capacity) ይመዝናል። ለምሳሌ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች 20 ሜትር ርቀት ያለውን ሩጫ ከ3 ሰከንድ ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቁ ይጠበቅባቸዋል (ምንም እንኳን ይህን ማድረግ አለመቻል በሊጉ እንዳይጫወቱ ባያስገድድም)።

 

በሃገራችን እግርኳስ በተጫዋቾች ዝውውር ላይ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከፍተኛ ገንዘብ እየፈሰሰ ይገኛል። ክለቦቻችም ከሚያስፈርሟቸው ተጫዋቾች ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት ይችሉ ዘንድ ከዝውውር በፊት በቂ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ በማድረግ ራሳቸውን ካላስፈላጊ ወጪ ሊጠብቁ እንደሚገባ ልንጠቁም እንወዳለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *