መቐለ ከተማ ከገብረመድህን ኃይሌ ጋር በይፋ ተፈራረመ

ሰኔ 30 ከአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጋር በይፋ ከተለያዩ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በቃል ደረጃ ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር የተስማሙት መቐለ ከተማዎች ዛሬ ከአሰልጣኙ ጋር ይፋዊ የፊርማ ስነ-ስርዓት አከናውነዋል።

ዛሬ 5 ሰዓት ላይ አሰልጣኙ ጨምሮ የቡድኑ አመራሮች በተገኙበት በደስታ ሆቴል በነበረው ይፋዊ ስነ-ስርዓት ላይ በርካታ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን በቀጣይ ዓመታት ቡድኑ የራሱ የሚለይበት አጨዋወት እንደሚኖረው እና ለቡድኑ ውጤታማት የሚፈለገው መስዋዕትነትን ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የመቐለ ከተማ ስራ አስከያጅ አቶ ሽፈራው ተ/ሃይማኖት ገልፀዋል።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በበኩላቸው ወደ መቐለ ከተማ መምጣታቸው እንዳስደሰታቸው እና ውስጣቸው የሚፈልገውን ነገር ማሳካታቸው ደስ እንዳሰኛቸው ገልፀው በቀጣይ በወጣቶች ላይ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ጨምረው ገልፀዋል።

ገብረመድህን ኃይሌ በ1994 በትራንስ ኢትዮጵያ የጀመረው የፕሪምየር ሊግ ቆይታቸው በባንክ፣ መድን፣ ቡና፣ ደደቢት፣ መከላከያ፣ ጅማ አባ ቡና እና ጅማ አባጅፋር አድርጎ መቐለ ከተማ ደርሷል።