ሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ተጫዋቹን አስፈርሟል

በዝውውር መስኮቱ ተጫዋች ሳያስፈርሙ ከቆዩ ጥቂት ክለቦች አንዱ የነበረው ሀዋሳ ከተማ የመጀመርያ ተጫዋቹን በማስፈረም ምንተስኖት አበራን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል። 

አዲሴ ካሳን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው ሀዋሳ ከተማ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ምንተስኖት አበራን በአንድ ዓመት ውል የግላቸው አድርገዋል።  በአርባምንጭ ከተማ ለረጅም ዓመታት የተጫወተው ምንተስኖት ክለቡ እስከወረደበትና ውሉ እስከተጠናቀቀበት የዘንድሮው የውድድር ዓመት ድረስ የቆየ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ በክረምቱ የለቀቀው ጋብሬል አህመድን ቦታ ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሀዋሳ ከተማ ከምንተስኖት ፊርማ በተጨማሪ የሶስት ተጫዋቾቹን ውል ማራዘሙ ታውቋል። አማካዩ አስጨናቂ ሉቃስ፣ ቶጓዊው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ እና ጋናዊው ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ ውላቸውን በአንድ ዓመት ለማራዘም የተስማሙ ተጫዋቾች ናቸው።