ሶከር ሜዲካል | የአዕምሮ ጤና በእግርኳስ 

የህክምና ጉዳዮችን ከእግር ኳስ ጋር በማቆራኘት በምንመለከትበት በዚህ አምድ የዚህ ሳምተት መሰናዶ የአዕምሮ ጤና ምንነት፣ ጠቀሜታ እንደዚሁም ከእግር ኳስ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳስሳለን። 

የዓለም አቀፍ የጤና ተቋም (WHO) ጤንነትን በአራት መሰረታዊ ክፍሎች ይመለከታል። አንድ ሰው ጤነኛ ለመባል አካላዊ ፣ አዕምሯዊ ፣ መንፈሳዊ እና መስተጋብራዊ ብቁነት ያስፈልገዋል። በሽታ አልያዘኝም ብሎ ስላሰበ ብቻ ጤነኛ ነው ልንለውም አንችልም። የአዕምሮ ጤና እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ያለ አዕምሮ ጤና ሙሉ ጤነኝነት ሊኖር አይችልም። ነገር ግን ስለዚህ ወሳኝ የሆነ የጤና ዘርፍ ብዙም ግንዛቤ የለም። የአዕምሮ ጤና ማለት ውስጣዊ ሰላምን እና የዕለት ተዕለት ተግባራትን ያለምንም ተፅዕኖ ማከናወን መቻልን ያጠቃልላል። 

በቅርቡ የዓለም አቀፍ የአእምሮ ጤና ቀን በሚከበርበት ወቅት ወደ 27% በመቶ የሚደርሱ የኢትዮጵያ ዜጎች የአዕምሮ ህመም ተጠቂ ናቸው የሚል መረጃ ወጥቶ ነበር። በማህበራዊ ድረገፆች ይህን አሃዝ ተከትሎ ያልተገቡ ፅሁፎች ሲወጡ ነበር። የአዕምሮ ህመም በውስጡ ብዙ በሽታዎችን ያቀፈ ነው። አብዛኛው ሰው የአዕምሮ ህመም ሲባል የሚመጣለት ሰውን የሚጎዳ አልያም አዕምሮውን የሳተና ማንነቱን የማያውቅ ህመምተኛ ነው። ይህ ግን እጅጉን የተሳሳተ አመለካከት ነው።  

የአዕምሮ ህመም አብዛኛውን ሰው የሚያስቸግሩ እንደ ጭንቀት ፣ ድብርት አልያም ሱስን በውስጡ አቅፏል። አንድ ሰው DSM-5 የተባሉትን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ የሚገኝ ሲሆን የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል ማለት ነው። ለምሳሌ:- ድብርት በአንድም በሌላም ወቅት ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ የሚችል ስሜት ነው። በሆነ ምክንያት ይህ ስሜት ሲያጋጥመን የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ስሜታችን እንዲሻሻል እናደርጋለን። ከሰው ጋር ማውራት አልያም ሙዚቃን ማዳመጥ በራሳችን ከምናከናውናቸው የመዝናኛ (መረጋጊያ) መፍትሄዎች መሃል ሊጠቀሱ ይችላሉ። እነዚህም  በተወሰኑ መልኩ የአእምሮ ሰላማችንን ለመቆጣጠር በራሳችን የምናደርጋቸው የመጀመሪያ ደረጃ መፍትሄዎች ናቸው።


ከአቅም በላይ ሲሆንስ? አንድ ሰው ድብርቱ ከ2 ሳምንት በላይ ከቆየበት፣ የምግብ ፍላጎቱ በጣም ከጨመረ አልያም ከቀነሰ፣ ስራውን ማከናወን ካልቻለ እና የመሳሰሉት ነገሮች ሲያጋጣሙ የባለሙያ እርዳታ ያስፈልገዋል።


እግር ኳስ ተጫዋቾች በተለያዩ ምክንያቶች ለአእምሮ ህመም በተለይም ለድብርት ተጋላጭ ናቸው። ውጤት ማጣት፣ በሚዲያ እና በደጋፊዎች መተቸት፣ ለብዙ ጊዜ በጉዳት ከሜዳ መራቅ ለዚህ መንስዔዎች ሊሆኑ ይችላል። የእግር ኳስ ተጫዋቾች ታዋቂ በመሆናቸው እና በርከት ያለ ገንዘብ ስለሚያገኙ ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ናቸው የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ። እንደኛ ሰዎች ስሜትን በግልፅ አውጥተው ማውራትን በማያበረታታ ማህበረሰብ ደግሞ እንደዚህ አይነት ችግሮች ያይላሉ። “አንተ ወንድ አይደለህ እንዴ? ጠንከር በል” የሚሉ ኋላ ቀር እና የተዛቡ አመለካከቶች ሰዎች የውስጥ ችግራቸውን ይዘው እንዲብሰለሰሉ እና መፍትሄ እንዳይፈልጉ እንቅፋት ይሆናሉ። 

በውጭ ሀገር  አሁን እየተለመደ በመጣ መልኩ ተጫዋቾች በግልፅ ስለ አዕምሮ ጤንነት ችግሮቻቸው እያወሩ ነው ። በቅርቡ እንኳን እንግሊዛዊው የቶተንሃም ሆትስፐር የግራ መስመር ተከላካይ ዳኒ ሮዝ ከድብርት ጋር የነበረበትን ችግር ተናግሯል። አሁን ወደ ማሰልጠኑ ዓለም የተቀላቀለው ማይክል ካሪክም ክለቡ ማንችስተር ዩናይትድ ሮም ላይ በባርሴሎና 2-0 ተሸንፎ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ካጣ በኋላ ከባድ ድብርት ውስጥ ገብቶ እንደነበር በቃለ መጠይቅ ወቅት ገልፇል። ተወዳጁ የቀድሞ ጣልያናዊ አማካይ አንድሬያ ፒርሎ 2005 ላይ በድራማዊ መልኩ ኤሲ ሚላን በሊቨርፑል ከተሸነፈ በኋላ ለአመታት የቆየ ድብርት እንዳጋጠመው በህይወት ታሪክ መፅሃፉ ላይ አስፍሯል። የቀድሞው የባየር ሙኒክ ኮከብ ሴባስቲየን ዳይስለር ገና በ27 ዓመቱ ከእግርኳስ ራሱን ያገለለው በድብርት ምክንያት ነበር። ባለፈው የውድድር ዓመት በይፋ ከእግር ኳስ ዓለም የተገለለውና ከሳምንት በፊት የእግር ኳስ ህይወቱን በጀመረበት ሃኖቨር ደማቅ አሸኛኘት የተደረገለት ግዙፉ ጀርመናዊ አጥቂ ፔር ሜተሳከር ሁልጊዜ ከጨዋታ በፊት ከፍተኛ ጭንቀት እንደሚያስቸግረው መናገሩ የሚታወስ ነው። ጭንቀቱ ከጨዋታ በፊት ምግብ መብላት እንደሚከለክለው የተናገረው የቀድሞው የአርሰናል እና ቨርደር ብሬመን ተከላካይ በእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ ላቅ ያለ ተፅዕኖ እንዳለውና ለጭንቀቱም ዋናው ምክንያቱ ይሄ እንደሆነ ተናግሯል።  በእኛ ሀገርስ? ስንት ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና በስፖርቱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች እንደዚህ አይነት ስሜቶች ይገጥሟቸዋል? መፍትሄዎችንስ አግኝተዋል? ክለቦች ድጋፍ አድርገውላቸዋል? 

የመፍትሄ ሀሳቦች 

እንደ ማኅበረሰብ 

1) የአዕምሮ ህመም ምንነትን መረዳት 

2) ሁኔታውን ከማጣጣል መቆጠብ 

3) ከማሾፍ እና ከማግለል መታቀብ 

4) የሰዎችን ችግር ለማዳመጥ እና አቅም በፈቀደ መልኩ ለመርዳት መጣር 

ተጫዋቾች 

1) የሚሰማቸውን ስሜት ቅርብ ላለ ሰው ማስረዳት 

2) በተቻለ መጠን ሁሌ የሚያወያዩት ሰው ቢኖር 

3) ከአቅም በላይ ሲሆን ባለሙያን ማማከር 

4) መድሃኒት የሚያስፈልግ ከሆነ (ለምሳሌ:- የእንቅልፍ መድሃኒት፣ ጭንቀት እንዲቀንስ የሚረዱ ) ያለምንም ፍርሃት መውሰድ 

በአጠቃላይ 

1) በሀገር አቀፍ ደረጃ የባለሙያዎች ቁጥር መጨመር 

2) በተለያዩ የሚዲያ አካላት ስለ አዕምሮ ጤና ግንዛቤን የሚፈጥሩ አስተማሪ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት 

3) የተሳሳቱ እና ጎጂ የሆኑ አመለካከቶችን እና ንግግሮችን ለማስወገድ መጣር 

በዚህ ርዕስ ላይ በወደፊት አዳዲስ ሃሳቦችን በጥልቀት ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።

error: