” ዲዲዬ ጎሜስ አቅም የላቸውም የሚል እምነት የለንም ” መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ

ኢትዮጵያ ቡና በ2011 የውድድር ዘመን እስካሁን ካደረጋቸው በዘጠኝ ጨዋታ 18 ነጥቦች በመሰብሰብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ከባለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ በውጤት ረገድ እያዝመዘገበ ባለው ጉዞ መልካም የሚባል ቢሆንም በየጨዋታዎቹ የቡድኑ እንቅስቃሴ አሳማኝ አለመሆኑን ተከትሎ ደጋፊው በተለያዩ መንገዶች ደስተኛ አለመሆኑን እና የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ የጨዋታ እንቅስቃሴ አለመመቸቱን በቅሬታ መልክ እያሰማ ይገኛል። 

ይህን ተከትሎ የክለቡን የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞን ደጋፊው እየገለፀው ስላለው ቅሬታ አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ክለቡ በአሰልጣኙ ላይ እምነት እንዳለው ገልጸዋል። “የአሰልጣኙ ቡድን ጥሩ አይጫወትም የሚል አቋም የለንም። ዲዲዬ አቅም እንዳለው ባለፈው ዓመትም ሆነ ዘንድሮ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ላይ ተመልክተናል። አሁን በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ በመሪነት ላይ እንገኛለን። ይህ ተደማምሮ ክለቡ በአሰልጣኙ ላይ እምነት አለው። የሚወስደው ምንም አይነት ነገርም የለም። ሆኖም የሚስተካከሉ ነገሮች በመኖራቸው ከአሰልጣኙ ጋር እየተነጋገርን ነው። ” ብለዋል። 

መቶ አለቃ ፈቃደ ጨምረው የቡድኑ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ምክንያት ያሏቸውን ሀሳቦች ገልጸዋል። “እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ቡና ከማንኛቸውም ክለቦች በተለየ የበርካታ ተጫዋቾች ጉዳት ሰለባ ነው። ዳኞች ለተጫዋቾቻችን ከለላ እየሰጡ ባለመሆኑ ተጫዋቾቻችን እየተጎዱብን ነው። ጎንደር ላይ አስራት ቱንጆ፤ ባለፈው በሸገር ደርቢ አማኑኤል ዮሐንስ ላይ የተሰሩ ግልፅ ጥፋቶችን ዳኞቹ በዝምታ እያለፉ መሆናቸው በቂ ማሳያ ነው። የህክምና ክፍላችን ተጫዋቾችን ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ ጥረት እያደረጉ ነው። ስለዚህ ችግሩን ገምግመን እናስተካክላለን እንጂ አሰልጣኙን አይችልም የሚል አቋም የለንም።”

ኢትዮጵያ ቡና በአስረኛው ሳምንት ወደ ሀዋሳ ተጉዞ በመጪው እሁድ ከሲዳማ ቡና ጋር ይጫወታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *