ሪፖርት | ስሑል ሽረ ባህር ዳርን በሜዳው በመርታት ወሳኝ ሶስት ነጥቦች አሳካ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛው ሳምንት ጨዋታ ሽረ ላይ ስሑል ሽረ በሜዳው ባህርዳር ከተማን ጋብዞ በሳሊፍ ፎፋና ብቸኛ ግብ 1-0 በመርታት ድልን አሰመዝግቧል፡፡

ስሑል ሽረ ወደ ሶዶ አምርቶ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ከተጋራባት ስብስቡ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥን በማድረግ አርዓዶም ገብረህይወት እና ዮናስ ግርማይን በቢስማርክ አፖንግ እና ያስር ሙገርዋ ሲተኩ ቅዱስ ጊዮርጊስን በ16ኛ ሳምንት የረቱት የጣና ሞገዶቹ አስናቀ ሞገስ እና ኤልያስ አህመድን በጃኮ አራፋት እና ደረጀ መንግስቱ ለውጠው ገብተዋል፡፡

ጨዋታው ልክ እንደተጀመረ ባለሜዳዎቹ ስሑል ሽረዎች በቁጥር በርከት ብለው ወደ ባህርዳር የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመቅረብ የግብ አጋጣሚ ሲፈጥሩ የባህርዳር ከተማ ተጫዋቾች የስሑል ሽረ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴን ከማምከን በተረፈ ይህ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በጨዋታው ጥሩ በመንቀሳቀስ ላይ በነበረው ሳሊፉ ፎፋና ላይ በተሰራው ጥፋት ስሑል ሽረዎች ፍፁም ቅጣት ቢያገኙም ቢስማርክ ኦቦንግ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የመጀመርያው አጋማሽም ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ብልጫ ወስዶ ቢጫወትም ጫና ፈጥሮ መጫወት የቻለው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ብቻ ነበር። የስሑል ሽረ ተጫዋቾች ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም በሳሊፉ ፎፎና አስቆጪ የሚባሉ የግብ ሙከራዎች መፍጠር ችለዋል። 76ኛው ደቂቃ ላይም ያስር ሙገርዋ በግሩም ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ አዲስ ፈራሚው ሳሊፉ ፎፋና ከባህርዳር ከተማ ተከላካዮች ሾልኮ በመውጣት ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ጨዋታው በሽረ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቢጫ ለባሾቹ ከወራጅነት ሰረጋት ለማምለጥ በሚያደርጉት ጥረት ላይ ወሳኝ ነጥቦች አሳክተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *