የ20 ዓመት በታች ቡድኑ ዝግጅት ሲቀጥል የሠላምና የወዳጅነት ውድድር በተባለበት ጊዜ ላይካሄድ ይችላል 

በአራት ሀገሮች ተሳታፊነት በኤርትራ አዘጋጅነት ከሚያዚያ ሦስት ጀምሮ ይካሄዳል ተብሎ ቀጠሮ የተያዘለት “የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ” በተባለበት ጊዜ ላይጀምር እንደሚችል ቢገመትም የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን አጠናክሮ እየሰራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ፣ ጁቡቲ ፣ ሱማሊያ እና አዘጋጇ ሀገር ኤርትራ ይካፈሉበታል ተብሎ የታሰበው ” የሠላም እና የወዳጅነት ” ጨዋታ ከሚያዚያ ሦስት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በአስመራ ከተማ ውድድሩ እንደሚካሄድ ከዚህ ቀደም መገለፁ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ከ20 አዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም የመጨረሻ 25 ተመራጭ ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን በተጠናከረ ሁኔታ እያካሄደ ይገኛል። ዛሬ 04:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ከመከላከያ የ20 ዓመት በታች ቡድን ጋር ባደረገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሸ እዮብ ዓለማየሁ ባስቆጠረው ብቸኛ ጎል 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ይሁን እንጂ ከተሳታፊ ሀገራት መካከል በተለይ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ተጫዋቾችን በመምረጥ ሆነ ለውድድሩ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ቢገኙም የተቀሩት ሁለት ሀገራት ሶማሊያ እና ጁቡቲ እስካሁን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ አለመሆኑ እና በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ እስካሁን ማረጋገጫ የሰጡ ባለመሆኑ ውድድሩ አስቀድሞ በወጣለት መርሐግብር መሠረት ላይካሄድ እንደሚችል ተገምቷል።


በቀጣዩ ሁለት ቀናት የሚለወጥ አዳዲስ ነገሮች ካሉ እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡