ከፍተኛ ሊግ ሐ | ጅማ አባ ቡና እና አርባምንጭ ነጥብ ተጋርተዋል

በከፍተኛ ሊግ 14ኛ ሳምንት ምድብ ሐ ቅዳሜ በተካሄደ ብቸኛ ጨዋታ ጅማ ስታድየም ላይ ጅማ አባ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡

በዝናብ ታጅቦ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እምብዛም ፉክክር ያልነበረበትና እንደ አየር ንብረቱ ሁሉ በእቅስቃሴ ረገድ ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ነበር፡፡ በሁለተኛው ዙር የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግ የተወሰኑ አዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ከመጀመሪያው ዙር አንፃር ጥሩ መሻሻል ያሳዩት ጅማ አባ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ጥቅጥቅ ብለው የሚከላከሉት የአርባምንጭ ተከላካዮችን አልፈው የግብ እድሎችን መፍጠር እኛ ሙከራዎችን ለማድረግ ተቸግረዋል። አርባምንጭች በመከላከሉ ላይ ትኩረት በማድረጋቸው ወደ ፊት በመሄድና ሙከራዎችን በማድረጉ በኩል ረገድ ደካማ የነበሩ ሲሆን አልፎ አልፎ ከመስመር ወደ ሳጥን ለስንታየሁ መንግስቱ የሚሻገሩ ኳሶች እና ከርቀት ወደ ግብ የሚሞከሩት ሙከራዎችም ውጤታማ አልነበሩም።

አባቡናዎች በመሀል ሜዳ ላይ የአቤል አምበሴና የካሚል ረሺድ ጥምረት እንዲሁም ምስጋናው መኮንን የግል ጥረቶች ጠንካራውን የአርባምንጭን የተከላካይ ለማለፍ ተቸግረዋል። በ37ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ አቤል አምበሴ ለምስጋናው በተከላካዩች መሀል ለመሀል አሳልፎ የሰጠውን ኳስ ምስጋናው የግቡ ቋሚ የውጠኛውን ክፍል ለትማ የወጣችበት አጋጣሚ አባቡናዎች የፈጠሯት ወርቃማ አጋጣሚ ነበረች።

ከእረፍት መልስ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በተመሳሳይ አባቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም የአርባምንጮችን ጠንካራና የተደራጀ መከላከል አጨዋወትን በመስበር ተስኗቸው ወደ ግብ የቀረቡ ሙከራዎች እድሎችን መፍጠር አልቻሉም። በዚህም ሁለቱም ቡድኖች ከእረፍት መልስ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ያለ ግብ 0-0 አቻ ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡