ሪፖርት | ምዓም አናብስት ከተከታያቸው የነበራቸውን የነጥብ ልዩነት መልሰው አስፍተዋል

በ23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትግራይ ስታድየም ላይ ስሑል ሽረን ያስተናገደው መቐለ 70 እንደርታ 3-1 ሶስት በማሸነፍ ከተከታዩ ፋሲል ከነማ የነበረውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት መልሶታል።

ባለፈው ሳምንት ህይወቱን ላጣው የዋልታ ፖሊስ ትግራይ ተጫዋች አማኑኤል ብርሃነ በተደረገው የህሊና ፀሎት የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ጥሩ የጨዋታ ፍሰት ያሳዩበት እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ነበር። ገና ከጅማሮው ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር የታየበት ጨዋታው ግብ ያስተናገደው ገና በአራተኛው ደቂቃ ነበር፤ ያሬድ ከበደ ከግራ መስመር የተሻገረለት ኳስ የስሑል ሽረው ግብጠባዊ ሰንደይ ሮትሚ ስህተት ታክሎበት ግብ በማስቆጥር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ በሁለቱም የመስመር ተከላካዮች አማካኝነት አጥቅቶ ለመጫወት ድፍረት የነበራቸው ስሑል ሽረዎች ከተጠቀሱት መስመሮች በተነሱ ሁለት ኳሶች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። ረመዳን የሱፍ ከመስመር በጥሩ ሁኔታ አሻግሮት ከግቡ ቅርብ ርቀት ይገኝ የነበረው ሳሊፉ ፎፋና ያልተጠቀመበት ኳስ እና ፎፋና ከአብዱሰላም አማን የተሻገረለትን ኳስ ከጠበበ አቅጣጫ መትቶ ፍሊፕ ኦቮኖ በጥሩ ሁኔታ ያዳነው ኳስ ስሑል ሽረዎች ከፈጠሯቸው ዕድሎች ለግብ የቀረቡት ነበሩ።

በጨዋታው ከሁለቱ የመሃል ተከላካዮች በተጨማሪ ናይጀርያዊው አንጋፋ ግብጠባቂው ሰንደይ ሮቲሚም በተደጋጋሚ ጊዜ ለስህተቶች ሲዳረግ ታይቷል። በዚህም አማኑኤል ገብረሚካኤል በስሑል ሽረ የመከላከል ስህተት የተገኘችው ኳስ ይዞ ሲገባ ሳጥን ውስጥ በዲሜጥሮስ ወልደሥላሴ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አማኑኤል ገብረ ሚካኤል ቢመታም ኳሷ በሰንደይ ሮትሚ መመለስ ችላለች። በጨዋታው ፍፁም ቅጣት ምት ያመከነው አማኑኤል ገብረ ሚካኤል ከአስር ደቂቃዎች በኃላ ከሳጥን ውጭ ግሩም ግብ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በአጋማሹ ከሐብታሙ ሽዋለም እና በጨዋታው ጥሩ በተንቀሳቀሱት ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ረመዳን የሱፍ እና አብዱሰላም አማን አማካኝነት ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የታዩት ስሑል ሽረዎች በሃያ ስምንተኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል፤ ቢስማርክ አፒያ ከአብዱሰላም አማን የተላከለትን ኳስ የመቐለ ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ያለመናበባቸውን ተጠቅሞ ነበር ግቧን ያስቆጠራት።

ከሌሎች ደቂቃዎች በተሻለ በርካታ ዕድል የተፈጠሩባቸው የመጀመርያ አጋማሽ የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተስተውለዋል። በመቐለ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል ከያሬድ ከበደ የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም ስሑል ሽረዎች በሐብታሙ ሽዋለም አማካኝነት ከርቀት ያደረገው ግሩም ሙከራ በተጠቀሱት የመጨረሻ ደቂቃዎች ከታዩት ሙከራዎች የተሻለ ነበሩ።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ሲያይ በጣም የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ እና በጣም ጥቂት ሙከራዎች በታየበት አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል የተሳካ የማጥቃት አጨዋወት ያልታየበት ነበር። በሙከራ ረገድ ከሽረዎች የተሻሉ የነበሩት መቐለዎች ምንም እንኳ ለግብ የቀረቡ ባይሆኖም ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይ ኦሴይ ማውሊ ከመስመር አሻምቶት ሃይደር ሸረፋ በግንባር ያደረገው ሙከራ፣ ከተመሳሳይ ቦታ ኦሴይ ማውሊ አሻምቶት አማኑኤል ገብረሚካኤል የሞከረው እና ሚካኤል ደስታ ከርቀት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ አቀራረብ ከአማካዮች በሚነሱ ቀጥተኛ ኳሶች ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የታዩት እና በአጋማሹ በአማካይ ላይ የፈጠራ አቅም እጥረት የተስተዋለባቸው ሽረዎች ምንም እንኳ የአጨዋወት ለውጥ አድርገው ቢመለሱም የማጥቃት አጨዋወታቸው ፍሬያማ አልነበረም። ሆኖም በሁለት አጋጣሚዎች አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር፤ ቢስማርክ አፖንግ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መትቶ ፊሊፕ ኦቮኖ እንደምንም ያወጣት ኳስ እና ሳሊፉ ፎፋና ከረመዳን የሱፍ የተሻገረችለት መትቶ በተመሳሳይ ፊሊፕ ኦቮኖ በጥሩ ብቃት ያዳናት ኳስ ስሑል ሽረዎችን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሁለት ድንቅ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎቹ ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ ራሳቸው ሳጥን አስጠግተው በመከላከል በረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የታዩት ምዓም አናብስት በሰማንያ ስምንተኛው የኦሴይ ማውሊ ድንቅ የረጅም ርቀት ግብ የጎል ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል፤ አጥቂው ከጋብርኤል አህመድ የተላከለት ኳስ ተጠቅሞ ነበር በግምት ከ25 ሜትር ግሩም ግብ ያስቆጠረው።

ውጤቱ በዚህ መልኩ መጠናቀቁን ተከትሎ ምዓም አናብስት ከተከታያቸው የነበራቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ ማድረግ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡