ኢትዮጵያ ቡና ካሳዬ አራጌን ቀጣዩ አሰልጣኝ አድርጎ መረጠ

ኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ለቀጣዩ የውድድር ዘመን አሰልጣኝ አድርጎ መምረጡን በይፋዊ ገፁ አስታውቋል።

የውድድር ዓመቱን በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ መሪነት ጀምሮ በገዛኸኝ ከተማ ጊዜያዊ አሰልጣኝነት ሊያገባድድ የተቃረበው ኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ኦፕሬሽንና ቴክኒክ ኮሚቴን በአዲስ መልክ ማዋቀሩ የሚታወስ ሲሆን የአሰልጣኝ ምርጫ እንዲያከናውን በተሰጠው መመሪያ መሰረት አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ምርጫው ማድረጉን ገልጿል። “ኢትዮጵያ ቡና የሚታወቅበትን የጨዋታ ዘይቤ በጥልቀት ይረዳል.” በሚል መነሻነት እንደተመረጠም ክለቡ ጨምሮ ገልጿል።

አሰልጣኝ ካሳዬ ከሚኖርበት ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከስምምነት ላይ ከደረሰ ቀጣዩ የቡና አሰልጣኝ ሆኖ የሚሾም ይሆናል ተብሏል።

ከ1979 ጀምሮ ለኢትዮጵያ ቡና የተጫወተው ካሳዬ አራጌ በ1994 መጨረሻ ከእግርኳስ ዓለም ከተገለለ በኋላ የክለቡ አሰልጣኝ ሆኖ የሰራ ሲሆን እስከ 1996 አጋማሽ በነበረው ቆይታ የጥሎ ማለፍ ድል ሲያስመዘግብ ኢትዮጵያ ቡናን በጂኬ አጨዋወት ፍልስፍናው የወቅቱ መነጋገርያ ቡድን አድርጎት ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡