ሪፖርት | ወልዋሎ እና አዳማ በጭማሪ ደቂቃ ጎሎች አቻ ተለያይተዋል

ሁለት የመጨረሻ ሰዓት ጎሎች በታዩበት የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ ወልዋሎ እና አዳማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት ከባህር ዳር አቻ ከተለያየው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ አዳማዎች በበኩላቸው ደደቢትን ካሸነፈው ስብስባቸው በምኞት ደበበ ምትክ ተስፋዬ በቀለ፣ በአዲስ ህንፃ ምትክ ከነዓን ማርክነህን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሁለቱም ቡድኖች በመሃል ሜዳ በሚያደርጓቸው ጥሩ እንቅስቃሴዎች የጀመረው ጨዋታውን ምንም እንኳ ጥሩ ጅማሮ ቢኖረውም በዛው ቅኝት አልቀጠለም። እንየው ካሳሁን በራሱ ጥረት ገብቶ ባደረገው ሙከራ ጥቃታችቸው የጀመሩት ወልዋሎዎች በተለይም ከአስር ደቂቃ በኃላ በነበረው የጨዋታ ክፍለ ግዜ በሁሉም ረገድ ብልጫ የነበራቸው ሲሆን በርካታ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም አፈወርቅ ኃይሉ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መትቶ ጃኮ ፔንዜ እንደምንም ያወጣው እንዲሁም እንየው ካሳሁን እና ሬችሞንድ አዶንጎ በጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን ገብተው አዶንጎ መትቶ ጃኮ ፔንዜ በድንቅ ብቃት ያወጣው ሙከራ ቢጫ ለባሾቹ ካደረጓቸው ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ። አብዱራህማን ፉሴይኒ በግል ጥረቱ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም ድንቅ ብቃት ላይ የነበረው ጃኮ ፔንዜ ወደ ውጭ አውጥቶታል።

በጨዋታው በመከላከል ላይ ካሳዩት ጥንካሬ ውጭ ይህ ነው የሚባል ጥሩ የማጥቃት አጨዋወት ያልነበራቸው አዳማዎች አልፎ አልፎ የመሃል ሜዳ ብልጫ ቢወስዱም በርካታ ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም። በዚህም ቡልቻ ሹራ ከቅጣት ምት መቶት ዓብዱልዓዚዝ ኬታ ካዳነው እና ከነዓን ማርክነህ በራሱ ጥረት ገብቶ ካደረገው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ሆኖም ቡድኑ ከነዓን ማርክነህን በሃሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ባሰለፈባቸው የመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል የተሻለ መንቀሳቀስ ችሎ ነበር።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ተመጣጣኝ ፉክክር እና ጥቂት ሙከራዎች በታየበት አጋማሽ ይህ ነው የሚባል ማራኪ እንቅስቃሴ አልታየበትም። ቡልቻ ሹራ ከርቀት አክርሮ መቶ ኬይታ በቀላሉ ባዳነው ሙከራ የጀመረው ጨዋታው እስከ ሰባ አምስተኛው ደቂቃ ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ አልታየበትም። በባለሜዳዎቹ በኩል በአንፃራዊነት ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች ታይተዋል። በተለይም ደስታ ደሙ ቢኒያም ሲራጅ ከመስመር ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራ እና ኤፍሬም አሻሞ ከርቀት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

እጅግ ድንቅ እንቅስቃሴ በታየበት የተጨማሪ ሰዓት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለት ግብና ሦስት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የታየበት ነበር። በሙከራ ረገድ ከነዓን ማርክነህ በራሱ ጥረት ተጫዋቾች አታሎ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝንቶ ያመከነው ኳስ ከታዩት ሙከራዎች ለግብ የቀረበ ነበር። ከሙከራው ብዙም ሳይቆይ በተመሳሳይ ቦታ ከነዓን ማርክነህ ተጫዋቾች አልፎ ከጠባብ አቋቋም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል እጅግ ተጠግተው ያጠቁት ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ብዙም ሳይቆዩ አቻ የሚያደርጋቸው ኳስ በዚህ ዓመት ወደ ዋናው ቡድን ባደገው ተስፈኛው ሰመረ ሃፍታይ ማስቆጠር ችለዋል። ተጫዋቹ ከሌላው አዲስ አዳጊ ስምዖን ማሩ የተላከለትን ግሩም ኳስ በአግባቡ ተጠቅሞ ከጠባብ አቅጣጫ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን አቻ ማድረግ የቻለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: