ከፍተኛ ሊግ | ወልቂጤ እና መድን ተጋጣሚያቸውን ሲያሸንፉ ኢኮስኮ ተሸንፏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 19ኛ ሳምንት እንዲሁም የምድብ ሀ እና ሐ ተስተካካይ ጨዋታዎች ሲደረጉ ወልቂጤ ከተማ እና መድን ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

ወልቂጤ ላይ ወልቄጤ ከተማ ከ ድሬዳዋ ፖሊስ ያደረጉትን ጨዋታ ወልቂጤ 3-0 አሸንፎ በመሪነቱ መቀጠል ችሏል። ፌዴራል ዳኛ ቢንያም ወርቅአገኘሁ በጥሩ ብቃት በመሩት ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ በብዙ መለኪያዎች የባለሜዳው ወልቂጤ ብልጫ የታየበት ነበር። እንግዶቹ ድሬዳዋ ፖሊሶች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፈጣን እንቅስቅሴ በማድረግ ንፁህ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ባይሳካም ዘርዓይ ገብረስላሴ በ6ኛው ደቂቃ ከርቀት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነበት የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ነበር። የተወሰደባቸውን የኳስ እንቅስቃሴ ብልጫ ማስመለስ የቻሉት ወልቂጤዎች በ5ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ታደሰ የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ከርቀት አክርሮ መትቶ በግቡ አናት ወደላይ ወጥቶበታል።

ግብ ለማግባት ጥረት ሲያደርጉት የነበሩት ክትፎዎቹ በተደጋጋሚ የግብ እድል ቢፈጥሩም የድሬዳዋ ግብ ጠባቂ ቀድሞ በመውጣት ሲያድንባቸው ውሏል። በተለይም በ15ኛው ደቂቃ የአህመድ ሁሴን እና በ29ኛ ደቂቃ ሐብታሙ ታደሰ እጅጉን ለግብ የቀረበ ሙከራ ግብ ጠባቂው ያከሸፈበት መንገድ የሚደነቅ ነበር። አልፎ አልፎ ኳስ መሰረት አድርገው አብዛኛውን ጌዜ በመልሶ ማጥቃት መጫወት የቻሉት ድሬዳዎች ፈርአን ሰይድ እንዲሁም ከድር እዮብ ያደረጉት የግብ ሙከራ ተጠቃሽ ነው።

የመስመር ጨዋታ ምርጫቸው ያደረጉት ወልቄጤዎች በ41ኛው ደቂቃ ላይ ብስራት ገበየሁ ያሻማውን ቅጣት ምት አህመድ ሁሴን በግሩም ሆኔታ በግንባሩ በመግጨት ወደግብነት ለውጦ መሪ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር ባኋላ በድጋሚ ሐብታሙ ታደሰ በግንባር የገጫት ኳስ በግቡ የግራ አግዳሚ የወጣችበት እድል አስቆጭ ነበረች።

በርካታ የሜዳ ላይ ጥፋቶች እንዲሁም ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ እና የጠራ የግብ እድል በሁለቱም ቡድን መታየት በቻለበት ሁለተኛው የጨዋታው ምዕራፍ ድሬዳዋ ፖሊሶች ጫና ፈጥረው ወልቂጤዎች ደግሞ ጥንቃቄ በመምረጥ የተንቀሳቀሱበት ነበር። በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ድሬዳዋ ፖሊሶች በ49ኛው ደቂቃ ፋርዓን ሠይድ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በ51ኛው ደቂቃ አቤል ብርሃኑ ከርቀት የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች። በጨዋታው እንቅስቃሴ አማካይ ክፍላቸው ተቀዛቅዞ የነበረው ወልቂጤዎች ከመስመር በሚሻገሩ ኳሱች እንግዳውን ቡድን ሲፈትኑ ታይተዋል። በተለይም በ54ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ያሳለፈለትና ተመስገን ደረሰ ከሳጥን ውስጥ ሆኖ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አናት የወጣችበት አጋጣሚ የግብ ብዛቱን ከፍ ማድረግ የምትችልበት አጋጣሚ ነበር። 

በ60ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን እድል ተመስገን ደረሰ አሻምቶ ሐብታሙ ታደሰ ወደ ግብነት ለውጦ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። በ74ኛው ደቂቃ ቢንያም ጌታቸው የመታው ኳስ የግቡን የግራ አግዳሚ ጨርፎ ሲወጣበት በ82ኛው ደቂቃ የድሬዳዎ ፖሊስ ግብ ጠባቂ እና ተከላካይ ስህተት ታክሎበት ቢንያም ያሻማውን ኳስ አህመድ ሁሴን በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት በመለወጥ ለቡድኑን ሶስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በወልቂጤ አሸናፊነት 3-0 ውጤት ተጠናቋል።

መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድን ከ ናሽናል ሲሚንት ያደረጉት ጨዋታ በመድን 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለኢትዮጵያ መድን በ27ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት አብዱልለጢፍ ሙራድ ቀዳሚዋን ግብ ሲያስቆጥር ከዕረፍት መልስ ምስጋናው ወልደዮሐንስ በ67ኛው ደቂቃ ላይ የመድንን ሁለተኛ ጎል አክሏል። መድን ማሸነፉን ተከትሎም የቻምፒዮናነት ትንቅንቁ ለቀጣይ ሳምንት እንዲሻገር አስችሎታል።

በኦሜድላ ሜዳ የካ ክፍለ ከተማ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢኮስኮን 1-0 አሸንፏል። በ28ኛው ደቂቃ ላይ ንጉሱ ጌታቸው ብቸኛዋን የማሸነፍያ ጎል ሲያስቆጥር በውጤቱ መሠረት የካ ላለመውረድ በሚያደርገው ጥረት ተስፋ ዘርቷል። ኢኮስኮ ደግሞ ለማደግ የነበረውን ተስፋ ይበልጥ አጨልሟል።

ነገሌ አርሲ ዲላ ከተማን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል። አርሲ ምትኩ ጌታቸው በ32ኛው ደቂቃ በጨዋታ፣ በ84ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥር ለዲላ ከተማ በ70ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል አለማየሁ ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ በ10:00 አዲስ አበባ ከሀላባ ያደረጉት ጨዋታ ያለምንም ግብ ሲጠናቀቅ ቅዳሜ በተደረገ ጨዋታ ሶዶ ላይ ሀምበሪቾ ሶዶ ከተማን 3-1 ረቷል። በ4ኛው ደቂቃ መሳይ አገኘው ሶዶዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ብርሀኑ አዳሙ በ46ኛው እና በ75ኛው ደቂቃ፣ ዘካርያስ ፍቅሬ በ62ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሀምሪቾ አሸንፎ ወጥቷል።

በሌሎች ምድቦች ጨዋታዎች በምድብ ሀ የ16ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ወልዲያ ላይ ወሎ ኮምቦልቻ ከ ደሴ ከተማ 0-0 ሲለያዩ ደሴ ከተማም ለማደግ ከሚደረገው ፉክክር ውጪ ሆኗል። በምድብ ሐ 12ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ካፋ ቡና ከ ሻሸመኔ ያደረጉት ጨዋታም በተመሳሳይ 1-1 ተጠናቋል።

የሁሉንም ቡድኖች የደረጃ ሠንጠረዥ ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ | LINK


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡