አፍሪካ ዋንጫ | ሑሴን ሻባኒ እና ሮበርት ኦዶንካራ ወደ ግብፅ ያመራሉ

የኢትዮጵያ ቡናው ብሩንዳዊ አጥቂ ሑሴን ሻባኒ እና የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማምራታቸውን በማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ ውድድሩ የሚያመሩ ተጫዋቾችን ቁጥር አራት አድርሰዋል።

በኢትዮጵያ ቡና የስድስት ወር ቆይታው ጥሩ ብቃት ያሳየው የ28 ዓመቱ የቀድሞ የባሮካ ተጫዋች በአፍሪካ ዋንጫው ለመጀመርያ ተሰላፊነት ከጂኤስ ካቤሌው ምርጥ አጥቂ ፊስቶን ዓብዱልረዛቅ እና የስቶክ ሲቲው ሰይዶ ቤራሂኖ ጋር ጠንካራ ፉክክር ይጠብቀዋል።

በቀጣይ ቀናት በአቋም መለኪያ ጨዋታ ከአልጀርያ እና ቱኒዝያ ጋር ጨዋታቸው የሚያካሂዱት በኦሊቨር ንያንጌኮ የሚመሩት ብሩንዲዎች ትልቋ ናይጀርያን በመግጠም የምድብ ጨዋታቸው ይጀምራሉ።

ሌላኛው ሀገሩን የሚወክለው የአዳማ ከተማው ግዙፍ ግብጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ሲሆን እሱም በተመሳሳይ ለቋሚ ተሰላፊነት ከኮከቡ ዴኒስ ኦኔያንጎ ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል። በግል ጉዳይ ምክንያት ወደ አቡዳቢ ዘግይቶ ያመራው ይህ ግብጠባቂ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅቱ ዘግይቶ ቢገባም የሴባስትያን ደሳብርን ስብስብ ሰብሮ ለመግባት ግን አልተቸገረም።

ሌላው ሀገሩን ይወክላል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ክሪዚስቶም ንታንቢ በመጨረሻው ስብስብ ሳይካተት ቀርቷል።

በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫው የምትሳተፈው ብሩንዲ እና ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ወደ ውድድሩ ያመራችው ዩጋንዳ ከኬንያ እና ታንዛንያ ጋር በመሆን ከምስራቅ አፍሪካ የሚሳተፉ ሀገራት ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: