“ከጅምሩ የሚሰራ ስራ ነው መጨረሻውን የሚያሳምረው” የሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ሀዲያ ሆሳዕና ባሳለፍነው እሁድ ካምባታ ሺንሺቾን 3-0 በማሸነፍ በ2008 ወደወረደበት ፕሪምየር ሊግ መመለሱን ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት ማረጋገጥ ችሏል። ቡድኑን ከሦስት ዓመት በፊት ለተመሳሳይ ድል ያበቁት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ዘንድሮም ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለሳቸውን ካረጋገጡ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

” እንግዳ ቡድኖችን በሜዳችን በጥሩ ሁኔታ መቀበላችን ከሜዳ ውጪ እንዳንቸገር አድርጎናል”

ውድድር ዓመቱን ከባለፈው ዓመት ጋር ሳነፃፅረው፤ የባለፈው ዓመት በጣም አሰልቺ ነበር። ምክንያቱም ብዙ ቡድኖችን በሁለት ምድብ ከፍሎ ማጫወት ድካምህን ይጨምራል። ዘንድሮ ምድቡ ወደ ሦስት በማደጉ ቶሎ እንዲጠናቀቅ ከመርዳቱ በተጨማሪ ውድድሩን ውበት እንዲኖረው አድርጓል። ወደ እኛ (ምድብ ሐ) ስመጣ እጅግ ጠንካራ ምድብ ነበር። በተለያየ ቦታ ሄደን ያሰብነውን ጨዋታ መተግበር እንዲሁም የደጋፊ ጫና ተቋቁመን መውጣት በጣም ከባድ ነው። በአንፃሩ ወደኛ የሚመጣ ቡድንን በከፍተኛ ሥነ ምግባር ነበር ተቀብለን የምንሸኘው። በዚህም ምክንያት ከሜዳ ውጭ ብዙ ችግር አልገጠመንም። ለዚህ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ደጋፊዎቹ ናቸው። አምና ደቡብ ፖሊስ ሳለው ቡድኑ በሜዳው ችግር ባይፈጠረበትም ከሜዳው ውጭ ብዙ ችግር አጋጥሞት ነበር። በአጠቃላይ ዘንድሮ በሜዳችን ካደረግነው 10 ጨዋታ 9 አሸንፈን 1 አቻ ወጥተናል።

” ጅማሬው ካላማረ መጨረሻው አያምርም “

በ2008 የነበረው ቡድን ብዙ ስራ አልተሰራበትም። እውነቱን ለመንገር ያኔ ምንም ሳንዘጋጅ ነው ወደ ላይ ያደግነው። የቡድኑ ባለቤት የሆነው አካልም ምንም አልተዘጋጀም ነበር። ብሔራዊ ሊግ የነበሩትን ነው ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደግነው። በዛም ምክንያት ሊጉን የመቋቋም አቅማችን በጣም አነስተኛ ነበር። ከዛ በኋላ ደቡብ ፖሊስ ላይ የተሻለ ነገር ሰርቻለሁ። በተለይም ከጅምሩ የሚሰራ ስራ ነው መጨረሻውን የሚያሳምረው። በእርግጠኝነት ጅማሬው ካላማረ መጨረሻው አያምርም። በዚህ ዓመት በትክክልኛ የሰራነው ስራ በተጫዋቾች ምልመላ የኔን የግብ እቅድ ይስካ ዘንድ ያገዙኝ ሰዎች አሉ። ከዚህ በተጨማሪ የአሰልጣኝ ስብስብ የተሻለ ይሆን ዘንድ በራሴ መንገድ ሰርቻለሁ። ያ ስራችን ነው ለዛሬ የስኬት ቀን ያደረሰን። መጀመሪያ ጥሩ ነገር መስራታችን ነው ለዚህ ያደረሰን፤ ፈጣሪ ይመስገን ለዚህም በቅተናል።

” ህዝቡ ፕሪምየር ሊግን አይቶ ነው የተነጠቀው…”

በዚህ ውጤት በጣም ደስተኛ ነኝ። ይህም የሆነበት ምክንያት ህዝቡ ፕሪምየር ሊግን አይቶ ነው የተነጠቀው። ይህ በመሆኑ እኔ በግሌ በጣም ተሰምቶኝ ነበር። ደቡብ ፖሊስ የመቀጠሉን እድል ወደ ጎን ብዬ ይህን ህዝብ ማስደሰት አለብኝ የሚል ሙሉ እምነት ይዤ ነው የመጣሁት። ከፕሪምየር ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚወርድ አሰልጣኝ ያለ አይመስለኝም። እኔ ይህን ማሳካት አለብኝ ብዬ ነው የመጣሁት። ፈጣሪ ይመስገን ይህ ይሳካ ዘንድ በጣም ያገዙኝ ሰዎች አሉ። ደጋፊው ምስጋና ይገባዋል። ይህ ሁሉ የሆሳዕና ደጋፊ ደስታውን ሲገልፅ የኔ ደስታ ደግሞ ከመጠን ያለፈ ነው። ይህን የደስታ ቀን በደጋፊው ላይ ማየት ነበር የናፈቅኹት። ሁለት ጨዋታ እየቀረን ማደጋችንን በማረጋገጣችን እጅግ የላቀ ደስታ ነው የተሰማን።

ካስፈለገዎ: ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡