“ሁለት ወይም አንድ ጨዋታ እየቀረን የማረጋጋጥ እቅዳችንን አሳክተናል” ትዕግስቱ አበራ

ሀዲያ ሆሳዕና በውድድር ዓመቱ አንድ ጨዋታ ብቻ ተሸንፎ ሁለት ጨዋታ እየቀረው ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለሱን አረጋግጧል። የቀድሞ አሰልጣኙን በመመለስ ስብስቡን በአዳዲስ ተጫዋቾች አዋቅሮ ለውድድር የቀረበው ሆሳዕና ወደ ሊጉ እንዲያድግ ከረዱ ተጫዋቾች አንዱ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ትዕግስቱ አበራ ነው። ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ ቡድኑን በተቀላቀለበት ዓመት ቡድኑን በአምበልነት ለመምራት የበቃው ትዕግስቱ ከድላቸው በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።


ጉዞ

በአጠቃላይ ጓዞችን እጅግ በጣም ጥሩ ነበር። ከመጀመሪያው ጀምሮ እስካሁን ባለው ጉዞ ውስጥ አንዴ ብቻ ነው ሽንፈት ያስተናገድነው። ለዚህም ነው ትልቅ ደስታ የተሰማን። ቡድኑ በሁሉም ቦታ ብቁ ተጫዎቾችን መሰብሰቡ እና የአሰልጣኝ ስብስቡ እጅጉን ጠንካራ የነበረ መሆኑ ውጤታማ አድርጎታል።

ፈተናዎች

ይህን ድል ልዩ የሚደርገው በጣም አስቸጋሪ ውድድር አመት ነበር። ረዥም ጉዞ ነበር የምንጓዘው፤ የሜዳ አለመመቸትም አለ። እኒህ ነገር ሌሎች ምድብ ላይ ይኖራሉ፤ እዚኛው ምድብ ላይ ግኝ የተለየ ነገር የነበረው በበጋ ወቅት ዝናብ የሚጥልበት ቦታዎች ነበሩ። ይህ ደሞ ሜዳውን ጭቃማ ከማድረጉ በተጨማሪ ያሰብነውን የጨዋታ እቅድ እንዳንተገብር እና ውጤት እንዳናሳካ እንቅፋት ይሆንብን ነበር። እነዚህን ተቋቁመን ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ሁለት ወይም አንድ ጨዋታ እየቀረን የማረጋጋጥ እቅዳችንን ማሳካት ችለናል።

ደጋፊ

እናንተም እንዳያችሁት ቡድኑ ጥሩ ይንቀሳቀሳል። የማሸነፍ ስነልቦናው ሁሌም ጥሩ ነው። ይህን ድል በምትወደው እና በምታከብረው ደጋፊ ፊት ስታከብር እጅጉን በጣም ደስ ነው የሚለው። ደጋፊው አብሮን ነበር፤ እውነት ለመናገር የሆሳዕና ደጋፊ ይህ ድል ይገባቸዋል። ሁሌም ቀድሞ በመገኘት የስፖርተኛውን ፍላጎት በማሟላት የስራውን ነፃነት ለአሰልጣኙ በመተው አስተደራዊ አካሄዶች ላይ የተሳካ ጊዜ ያሰላፉት አመራሮች ሁላችንም ልናመስግናቸው እንወዳለን። በአጠቃላይ ሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጭ ለሚኖሩ የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች እንኳን ደስ ያላቹ ማለት እፈልጋለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡