ምስራቅ አፍሪካ| ኤርትራ ነገ በምታደርገው ጨዋታ ወደ ዓለምአቀፍ ውድድር ትመለሳለች

ከአንድ ዓመት በላይ ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ ተገልላ የቆየችው ኤርትራ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ነገ ናሚቢያን በመግጠም ወደ ውድድር ትመለሳለች።

ኤርትራ በ2018 መጀመርያ ወር በዓለም ዋንጫ ከቦትስዋና ጋር ተደልድላ ጨዋታ ካካሄደች በኋላ አስር የሚደርሱ ተጫዋቾች በዛው በጋቦሮኒ ጥገኝነት መጠየቃቸውን ተከትሎ የኤርትራ መንግስት ሃገሪቷን በማንኛውም የእግርኳስ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ መወሰኑ ይታወሳል። ከቦትስዋናው ክስተት እና ብዙዎች ካነጋገረው የ2009 የኬንያ ሴካፋ ውድድር ተጫዋቾች መጥፋት ታሪክ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ የተጫዋቾች መጥፋት ታሪክ ያላት ኤርትራ ከ18 ወራት በኋላ በድጋሚ ወደ ዓለም አቀፍ እግር ኳስ የምትመለስ ይሆናል።

አሰልጣኝ ዓለምሰገድ ኤፍሬም ለትውልደ ኤርትራውያን ተጫዋቾች ባደረጉት ጥሪ መሰረት ከዚህ በፊት በአንድ ጨዋታ ኤርትራን ወክሎ የተጫወተው አምበሉ ኄኖክ ጎይትኦምን ጨምሮ ሶማዮማ አሌክሳንደር እና ሌሎች በርካታ ተጫዋቾች በትናንትናው ዕለት ኤርትራ ገብቷል።

ኤርትራ ባለፉት አስር ዓመታት ደካማ የእግር ኳስ ደረጃ ብትይዝም ከእግር ኳስ ደረጃዋ አንፃር በርካታ የማዘውተርያ ስፍራዎች ያላት ሃገር ስትሆን በአስመራ ከተማ ሁለት ደረጃቸው የጠበቁ ስታድሞች እንዲሁም ከዋና ከተማው ሃምሳ ኪሎሜትር ርቀት የሚገኝ የከረን ስታዲየም አሏት። በ2000 እና 2008 የተሻለ ወደ አህጉሪቱ የማለፍ ዕድል የነበራት ይቺ ሃገር በዚ ሰዓት በአሰልጣኝ ዓለምሰገድ ኤፍሬም እየተመራች ወደ ውድድር የምትመለስ ሲሆን ከዚ በፊት በነጋሽ ተክሊት ፣ ሬኒ ፌለር ፣ ዶርያን ማሪን ፣ ይልማዝ ዩስታርክ እና ተክኤ አብርሃ መሰልጠን ችላለች።

ሀገሪቱ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የተከናወነው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ውድድርን በጥሩ ሁኔታ ማስተናገዷ የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ