የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በባህር ዳር ስታዲየም ቀለል ያለ ልምምድ ሰርቷል

ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሁለተኛ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ነገ ከኮርዲቯር ጋር የሚጫወቱት ዋሊያዎቹ ዛሬ አመሻሽ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሰርተዋል።

7:00 ሰዓት ባህር ዳር የደረሰው ብሄራዊ ቡድኑ በቀጥታ ወደ ዩኒሰን ሆቴል በማምራት ለጥቂት ሰዓታት ካረፈ በኋላ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የ70 ደቂቃ ልምምድ ሰርቷል።

11:20 በጀመረው የቡድኑ ልምምድ ተጨዋቾችን የሚያነቃቃ የቡድን ስራዎች ተሰርተዋል። ፈገግታን ከሚያጭሩ እና የተጨዋቾችን ፍላጎት ሊያነቃቁ ከሚችሉ ቀለል ያሉ ልምምዶች በተጨማሪ ቡድኑ ዘለግ ላለ ደቂቃ የቡድን ውይይት ሲያደርግ ተስተውሏል። በዚህም የውይይት ጊዜ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቡድኑ እንዴት መከላከል እንዳለበት በተግባር ገለፃ ሲያደርጉ ታይቷል።

ብሄራዊ ቡድኑ ለ60 ደቂቃዎች ያክል ቀለል ያሉ ልምምዶችን ከሰራ በኋላ ተጨዋቾቹ በጋራ በመሆን ዜማ ሲያዜሙ ታይቷል። በዚህ ጊዜ ተጨዋቾቹ አንድነታቸውን የሚያጠናክር ዜማዎችን በጋራ በማዜም የዕለቱን ልምምድ ቋጭተዋል።

በተያያዘ ዜና የስታዲየም የመግቢያ ዋጋዎች ታውቀዋል። በዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ያዘጋጃቸው ትኬቶች ባለ 25፣ 50 እና 100 ብር እንደሆነ ተገልጿል።


© ሶከር ኢትዮጵያ