አስተያየት | ጥቂት ነጥቦች በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የኮከቦች ምርጫ ዙርያ

የ2011 የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የኮከቦች ምርጫ ባሳለፍነው ቅዳሜ በካፒታል ሆቴልና ስፓ ተካሂዷል። መርሐ ግብሩን ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም አሁንም በቀጣይ መደገም የሌለባቸው መሠረታዊ ስህተቶችን አስመልክቶን አሳልፏል።
በቀጣይ ይህን ምርጫ በተሻለ መልኩ ለማካሄድ ይረዳ ዘንድ የተወሰኑ ዐበይት ጉድለቶች ብለን የታዘብናቸውን በቀጣዩ መልክ አቅርበነዋል።

1. ሽልማት ለተጫዋቾች የሚኖረው ትርጉም ላይ ያለው ደካማ አረዳድ

የእግርኳስ ተጫዋቾች በጥቅሉ በከፍተኛ ደረጃ የሚጫወቱበት ዘመን እጅግ የተገደበ ነው፤ በነዚሁ ውስን ዘመናት እንደቡድንም ሆነ በግል የሚያሳኳቸው ክብሮች የሚኖራቸው ትርጉም ከጊዜያዊ ደስታም የበለጠ ነው። ተጫዋቹ በእግርኳስ ዘመኑ ያሳካቸው እነዚህ ክብሮች በቀጣይ በእግርኳሱ የታሪክ ማህደር ውስጥ ጎልተው የሚሰፍሩ የህይወት ዘመን ስኬት ናቸው።

በዚህ ረገድ በእኛ ሀገር ያለው አረዳድ ግን ከዚህ ተፃራሪ ነው። ባሳለፍነው ቅዳሜ ከተካሄደው የኮከቦች ምርጫ ጋር ተያይዞም በርካታ ግድፈቶች ተመልክተናል። ለማሳያነትም ከሽልማቱ ከአንድ ቀን በፊት ይፋ በተደረገው የእጩዎች ዝርዝር ውስጥ በከፍተኛ ሊግ ኮከብ ግብጠባቂ ዐምና ከሰበታ ከተማ ጋር ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈው ሰለሞን ደምሴ እና የኢትዮጵያ መድኑ ጆርጅ ደስታ በመጨረሻ እጩነት የቀረቡ ቢሆንም አስቀድሞ በተለቀቀው ዝርዝር ውስጥ ግን ዐምና በሰበታ ከተማ ቡድን ስብስብ ውስጥ ከመካተት ውጪ እጅግ ጥቂት ጨዋታ ያደረገው አሰግድ አክሊሉ በእጩነት መገለፁ ከመርሐ ግብሩ ጀርባ የነበረውን ደካማ ቅድመ ዝግጅትና የድረስ ድረስ ጥድፊያ ጠቋሚ ነው።

በተመሳሳይ በዕለቱ በአንደኛ ሊግ፣ በከፍተኛ ሊግ እንዲሁም በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሽልማቶች ወቅት አስቀድሞ በተሰጠው የአሸናፊዎች ዝርዝር እንዲሁም በመድረክ አስተዋዋቂዎች ሲጠቀሱ የነበሩ የአሸናፊዎች ስም ስህተት ይስተዋልባቸው ነበር። በተለይም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት የአርባምንጭ ከተማው ስንታየው መንግሥቱ በ15 ግቦች ማጠናቀቅ ቢችልም በመርሃግብሩ በመድረክ አስተዋዋቂዎቹ ሲነገር የነበረው ግን በ2010 የተሸለመው ብዙዓየሁ እንደሻው ከጅማ አባቡና የውድድሩ ኮከብ አስቆጣሪ ስለመሆኑ ነው። በተመሳሳይ በሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን ሴናፍ ዋቁማ ኮከብ ተጫዋች ተብላ ብትመረጥም በመድረኩ ላይ የተጠቀሰችው አሸናፊ ግን ሌላኛዋ የቡድን አጋሯ ሰናይት ቦጋለ ነበረች።

ይህ አይነት ቀላል የሚመስሉ ግን በጊዜ ሂደት የታሪክ ሂደትን የማዛባት አቅም ያላቸው ግዙፍ ስህተቶች በቀጣይ ሊታረሙ ይገባል።

2. የሽልማት ቁስ ወጥ አለመሆን

በመሰል የሽልማት መርሃግብሮች ላይ የሚበረከቱ ሽልማቶች ከዓመት አመት ተመሳሳይ ይዘት ኖሯቸው በሂደት የሽልማቱ ማንነት መገለጫ ሲሆኑ ይስተዋላል።

በቅድሚያ የሽልማቶቹ ቅርፅና ይወት ከመወሰኑ በፊት በጥልቀት ሁኔታዎችን አማራጮችን በመመርመር መመረጥ ይገባቸዋል። ታድያ አንዴ ይህ ሽልማት ላይ መግባባት ተደርሶ ከተመረጠ በኋላ በወጥነት ከዓመት ዓመት ማገልገል ይኖርበታል።

በዚህ የኮከቦች ሽልማት ላይ እየሆነ የሚገኘው ግን ሌላ ነው፤ መርሐ ግብሩ ደረጃውን በጠበቀ ቦታ በአንድ ቦታ መሰጠት ከጀመረበት የቅዳሜው ለሦስተኛ ጊዜ የተካሄደ ነበር። ነገርግን በሦስቱም አጋጣሚዎች ለአሸናፊዎች የተበረከቱት ሽልማቶች ፈፅሞ የተለያዩ ናቸው። በቀጣይ በሚኖሩት መርሐ ግብሮች ላይም ተመሳሳይ ድክመቶች እንዳይኖሩ ሂደቱን መመርመር ይገባል።

3. የቀን አመራረጥ እና ጊዜ አጠቃቀም

ሽልማቶች በጊዜ የተገደቡ እና በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አመልካቾች እንደመሆናቸው ወቅቱን ጠብቀው መደረግ ይኖርባቸዋል። ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን በሐምሌ መጨረሻ ቢያገባድድም ሽልማቱን በ4 ወራት አጓትቶ ሌላ አዲስ የውድድር ዘመን ከተጀመረ በኋላ አከናውኗል። በሌሎች ሀገራት እንደሚደረገው ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ እና ሁለት ጨዋታ ሲቀር ማከናወኑ ባይቻል እንኳ ከውድድሮች መባቻ አንድ እና ሁለት ሳምንት በኋላ ቢከናወን ግለቱን በጠበቀ መልኩ ስለሚሆን ትኩረት ሳቢ እና ደማቅ ያደርገዋል። ከአራት ወራት በኋላ ለማድረግ ያህል ብቻ የሚከወን ሽልማት ቀዝቃዛ ድባብ ከመፍጠሩ በተጨማሪ እንዲመርጡ ለሚሰየሙ አካላትም ፈታኝ ይሆናል። ምክንያቱም ውድድር ከተጠናቀቀ ከወራት በኋላ የተጫዋቹን ትክክለኛ አቋም አስታውሶ መመዘን አዳጋች ስለሚሆን።

ከላይ ከተጠቀሰው ወቅት ተኮር ድክመት ባሻገር ፌዴሬሽኑ ሌላ ስህተት አክሎበታል። የሊግ ውድድር (የወንዶች እና ሴቶች ፕሪምየር ሊግ) ጨዋታ የሚደረግበትን ዕለት መርጦ ይህን ሽልማት ደንቅሮታል። ተሸላሚዎቹ ጨዋታ እያደረጉ አልያም በቀጣይ ቀን ለሚደረግ ጨዋታ እየተዘጋጁ ፌዴሬሽኑ ግን ሽልማቱን እያከናወነ ነበር። በዚህም 12፡00 የተጠራው የሽልማት ሥነ-ስርዓት ለአንድ ሰዓት ከሃምሳ ደቂቃ ዘግይቶ ሊጀመር በቅቷል። የሽልማቱ አሸናፊዎች በሥፍራው እስኪደርሱ ታስቦ በርካታ አሰልቺ የነበሩ ሂደቶችን አልፎ በስተመጨረሻም ከምሽቱ 4 ሰአት የመርሐግብሩ ማሳረጊያ ሆኗል።

በእርግጥ በዘንድሮው የኮከቦች ሽልማትን በተለየ መልኩ ከ11ኛው የፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ጋር ተሳስሮ እንዲካሄድ በማሰብ ብዙ ጥረቶች ተደርጓል፤ ለዚህም ሲባል ከጠቅላላ ጉባዔው አንድ ቀን ቀድሞ በተካሄደው በዚሁ መርሐ-ግብር በርከት ያሉ ለጉባዔው የተሰባሰቡ ተሳታፊዎች ሥነ-ስርዓቱ ላይ መታደም ችለዋል። ሆኖም ያለ ተሸላሚ የሚኖር ሽልማት የሽልማትነት ጣዕሙን የሚያሳጣ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል።

4. ግራ የተጋባው የሽልማት ሂደት

በመርሐ-ግብሩ ከአንድ ቀን በፊት ይፋ በተደረገው የእጩዎች ዝርዝር በተወሰኑ መስኮች ሦስት በአንዳንድ ዘርፎች ደግሞ ሁለት የመጨረሻ እጩዎች ቀርበዋል። ነገርግን በተባለው መሠረት እጩዎቹ የተለዩት በግልፅ በተቀመጡ መስፈርቶች ከሆነ እውን ሁለት እጩዎች በቀረቡባቸው ዘርፎች ሶስተኛ ሌላ እጩ ጠፍቶ ነውን?

ሌላው አሸናፊዎች አስቀድመው በታወቁበትና ለስፖርት ቤተሰቡ መረጃው በተለያዩ መንገዶች አፈትልኮ ወጥቶ በታወቀበት ሁኔታ መድረክ ላይ የክብር እንግዶችን ጠርቶ አሸናፊዎችን ለማስተዋወቅ የተኬደበት ሂደት እንደው ለደንቡ እንጂ አስፈላጊነቱ እዚህ ግብ የሚባል አይደለም።

5. የግልፀኝነት ችግር

በምርጫው ላይ በኢትዮጵያ ወንዶችና ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ በተደረገው የምርጫ ሂደት የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበርን ለማሳተፍ የተደረገው ጥረት የሚመሰገን ቢሆንም ሌሎች በምርጫው ሂደት ስለተሳተፉ አካላት እንዲሁም በሌሎች የውድድር ዓይነቶች ላይ ስለተካፈሉ አካላት በግልፅ የተገለፀ ነገር አለመኖሩ በቀጣይ መታረም ይገባዋል።

በሽልማት ሥነ-ስርዓቱ ላይ በዓመቱ ውድድር ከ1-3 ያጠናቀቁ ክለቦች የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፤ በተጨማሪም የገንዘብ ሽልማት ለሁሉም አሸናፊዎች መበርከቱን ለማስተዋል ችለናል። ነገር ግን የገንዘብ መጠኑ ይብዛም ይነስ መገለፅ ሲገባው በምስጢር ለመያዝ ተሞክሯል።

6. ደካማ የመድረክ ዝግጅት

አንድ የሽልማት መርሐ ግብር ግዝፈት እና ትኩረት እንዲያገኝ ከተዓማኒነቱ ባሻገር ሁሌም ሊታወስ በሚችል መልኩ ደማቅ በሆነ እና ባልተዝረከረከ መልኩ ሊዘጋጅ ይገባዋል። የቅዳሜው ሁነት ግን ከዚህ አጅግ ተቃራኒውን አስመልክቶን አልፏል። ዝግጅቱ ይጀመራል ከተባለበት ሰዓት እንዲሁም ታዳሚያን ቦታ ቦታ ከያዙ በኋላ በተለይ መድረኩን ለማስዋብ እጅግ በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ ተስተውሏል። ይህም ለመርሐ ግብሩ የተሰጠውን ዝቅተኛ ትኩረት በግልፅ የሚያሳይ ነበር።

በተመሳሳይ ፌደሬሽኑ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በመተባበር በተወሰኑ ዘርፎች በእጩነት የቀረቡ ተጫዋቾች ለታዳሚያን የተላለፉበት ሂደት እጅግ ደካማና በግብር ይውጣ የተሰራ ስለመሆኑ ያሳብቃል።

ከመድረክ ግንባታ፣ መብራት እንዲሁም ሌሎች ሂደቶች ጋር የነበሩት ክፍተቶች ምንም እንኳን ከዐምናው የተሻለ ቢሆንም በቀጣይ መታረም ይኖርባቸዋል። በተለይ ይህን ሥራ መስራት የሚችሉ የሙሉ ሰዓት ሁነት አዘጋጅ ተቋማት በሞሉበት ከተማ ፌዴሬሽኑ ሁሉንም ነገር በራሱ ለመስራት ማሰቡ ዘመኑን ያልዋጀ ኃላቀር አሰራር ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ