ባህር ዳር ከተማ ወሳኙን ተጫዋች በጉዳት ሊያጣ ነው

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ባህር ዳር ከተማን በመቀላቀል መልካም የውድድር ጅማሮን እያደረገ የሚገኘው ፍፁም ዓለሙ በጉዳት ከሜዳ ሊርቅ ነው።

ትናንት በሊጉ 7ኛ ሳምንት ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ላይ ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ 3-2 በሆነ ውጤት በረታበት ጨዋታ ማጥቃት እንቅስቃሴ ከነበረው ከፍተኛ ሚና በተጨማሪ ሁለት ወሳኝ ጎሎችን ያስቆጠረው ፍፁም ዓለሙ ደረቱ ላይ ባጋጠመው የአጥንት መሰንጠቅ ጉዳት ምክንያት ለሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ሰምተናል።

ምንም እንኳን በትናንቱ ጨዋታ ደረቱ በፕላስተር ታሽጎ ከነጉዳቱ እስከ 84ኛው ደቂቃ ድረስ መጫወት ቢችልም የጉዳቱ መነሻ ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ እንደሆነ ተነግሯል። ዛሬ የህክምና ምርመራ ያደረገው ፍፁም የተወሰኑ ቀናት እረፍት እንዲያደርግ ሲነገረው ከዚህ በኃላ ለምን ያህል ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ባይታወቅም የፊታችን እሁድ ሀዋሳ ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር በሚኖረው ጨዋታ ከቡድኑ ጋር አብሮ እንደማይጓዝ ተረጋግጧል።

ፍፁም ዓለሙ በዘንድሮ የውድድር ዓመት እስካሁን በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ዝርዝር ከሙጂብ ቃሲም በመቀጠል በስድስት ጎሎች በሁለተኛ ደረጃነት እየተከተለ ይገኛል። በሶከር ኢትዮጵያ የሊጉ የመጀመርያ ወር ኮከብ ተጫዋች ሆኖ መመረጡም የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: