ቢኒያም በላይ ወደ ሌላው የስዊድን ክለብ አምርቷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ አማካይ ቢኒያም በላይ ለስዊድኑ ክለብ ኡሚያ ኤፍሲ ፊርማውን አኑሯል።

ከሌላኛው የስዊድን ክለብ ስሪያንስካ ለቆ ይህን የሰፐርታን ሊግ ክለብ የተቀላቀለው ቢኒያም በክለቡ ይህን የውድድር ዓመት የሚያጫውተውን ኮንትራት ተፈራርሟል። 

ከዝውውሩ በኋላ ቢኒያም ወደ ክለቡ በመምጣቱ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ ከሌሎች ክለቦች የዝውውር ጥያቄ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም ዩሚያን ምርጫው እንዳደረገ ጠቁሟል። በተጨማሪም የቡድኑን ጨዋታዎችን እንደተመለከተና ከቡድኑ አመራሮች ጋር ያደረገው ንግግር ዝውውሩን ቀላል እንዳደረገለት ለክለቡ ድረ-ገፅ ተናግሯል። 

ቢንያም አክሎም ” ወጣት ነኝ፤ እንደተጫዋች መማር እና ማደግ አለብኝ። ክለብ ደግሞ ሁሌም ቀዳሚ ነው፤ ከቡድን ጓደኞቼ ጋር በጋራ ያለኝን በመስጠት ጥሩ ለመስራት ተዘጋጅቻለሁ።” ሲልም ሀሳቡን አጠቃሏል።

የቡድኑ አሰልጣኝ ዳኒ ፔርሰን በበኩላቸው ” ቢንያም አስደሳች የማጥቃት ባህርይ ያለው፤ በመሐል ወይም በመስመር መጫወት የሚችል ተጫዋች ነው። በሱፐርታ ሊግ ጥሩ ዓመት አሳልፏል። ከኛ ደግሞ ከሱ የበለጠውን ለማግኘት እናስባለን።” ብለዋል። 

ቢኒያም የተቀላቀለው ክለቡ ኡሚያ ኤፍሲ በስዊድን ሁለተኛ የሊግ እርከን (ሰፐርታን) የሚገኝ ክለብ ነው። 

©ሶከር ኢትዮጵያ

error: