ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወላይታ ድቻ

በነገው ዕለት የሚካሄደው ቀጣይ የ13ኛ ሳምንት ብቸኛ መርሐግብር የሆነውና ሜዳው በመቀጣቱ ሳቢያ ከሜዳው ውጭ የሚጫወተው ሀዲያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን በሀዋሳ ስታዲየም የሚያስተናግድበትን ጨዋታ በተከታዩ መልኩ ዳሰነዋል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ11ኛው ሳምንት በሜዳቸው በወልቂጤ ከተማ 2-1 ከተረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ በሜዳቸው በተስተዋለው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ድርጊት በፕሪምየር ሊጉ አወዳዳሪ አካል ሁለት ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወቱ ባስተላለፈባቸው ብይን መሠረት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጭ በሀዋሳ ስታዲየም ወላይታ ድቻን በማስተናገድ ይጀምራሉ።

የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ አሸነፈ

ባሳለፍነው ሳምንት ከአሰልጣኛቸው ግርማ ታደሰ ጋር ተለያይተው በሳምንቱ መጨረሻ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ዋና አሰልጣኝ አድርገው የቀጠሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በአዲሱ አሰልጣኛቸው እየተመሩ በሚያደርጉት በዚሁ ጨዋታ የቡድኑ ተጫዋቾች በአዲስ አሰለጣጠንና በተሻለ የመነሳሳት ደረጃ ሆነው ጨዋታውን ያደርጋሉ ተብለው ይጠበቃሉ። በአንፃሩ በተመሳሳይ በቅርቡ ዋና አሰልጣኛቸውን አሰናብተው በጊዜያዊ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ እየተመሩ ጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙት ድቻዎች ካሉበት ወቅታዊ ብቃት አንፃር ለሆሳዕናዎቹ ጨዋታውን ሊያከብዱባቸው እንደሚችሉ ይገመታል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በግርማ ታደሰ በሚመሩበት ወቅት በተለይ ቡድኑ በመከላከል አጨዋወት ላይ በማተኮሩ የተከፉት የቡድኑ ደጋፊዎችን ለመካስ አዲሱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ለጥቂት ቀናት በዘለቀው የሆሳዕና ቆይታቸው የተጋነነ ለውጥ ባይጠብቅም በግርማ ታደሰ የኃላፊነት ወቅት በሁለቱ ቢስማርኮች ፍጥነት ላይ ከተመሠረተው የማጥቃት እንቅስቃሴ በዘለለ ሌሎች አማራጮችን ይዘው ሊቀርቡ እንደሚችል ይገመታል።

ከላይ እንደተገለፀው ቡድኑ በአሰልጣኝ ሽግግር ላይ እንደመሆኑ በነገው ጨዋታ እምብዛም ለውጥ ባይጠበቅም የወላይታ ድቻ ሁነኛ የጥቃት መሳርያ የሆኑ ተጫዋቾችን እንቅስቃሴ መገደብ ዋንኛ ትኩረታቸው እንደሚሆን ይጠበቃል። የማጥቃት ፍሰቱን የሚቆጣጠረው ኢድሪስ እና ሁለቱ የመስመር አጥቂዎችን መቆጣጠር ለሆሳዕና ከባድ የቤት ስራ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በሆሳዕና በኩል አማካዩ አብዱልሰመድ ዓሊ በጉዳት የቀድሞ ክለቡን የማይገጥም ሲሆን ይሁን እንደሻው ደግሞ ከቅጣት ይመለሳል።

የወላይታ ድቻ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

ባለፈው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን በማሸነፍ በጥሩ መነሳሳት ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ከወራጅ ቀጠናው በአስተማማኝ ሁኔታ ለመራቅ ማሸነፍን አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።

ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሜዳቸውም ሆነ ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በሁለቱ አጋማሾች ፍፁም የተለያየ ቡድን ሆነው ሲቀርቡ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ቡድኑ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከእድሪስ ሰዒድ በሚነሱና በቅርቡ ከጉዳት የተመለሱት ሁለቱ ተስፈኛ የመስመር አጥቂዎች እዮብ ዓለማየሁ እና ቸርነት ጉግሳን ማዕከል ባደረገ መልኩ በመስመሮች ጥቃትን ለመሰንዘርና ግቦችን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቢስተዋልም በሁለተኛው አጋማሽ ግን በተቻለ መጠን ውጤትን ለማስጠበቅ በጥንቃቄ የሚጫወት ቡድን እየሆነ መጥቷል። ይህን ተከትሎም በነገው ጨዋታም በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ የሚታትረው ወላይታ ድቻን ሊያስመለክተን ይችላል።

ወላይታ ድቻ ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች እንደተስተዋለው ዋንኛ የጎል ምንጮቹ የሆኑት መስመር አጥቂዎች እና ባዬ ገዛኸኝ ፍጥነት ላይ ተመስርቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በተለይ የሆሳዕና የኋላ ክፍል ቀልጣፋ አለመሆን ለድቻ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። በተቃራኒው የሆሳዕና የአማካይ ክፍል አንፃራዊ ጥንካሬ የጥቃት መነሻ የሆነው የመሐል ክፍሉን እንደልብ እንዳይቆጣጠሩ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል።

በነገው ጨዋታ ወላይታ ድቻ ያሬድ ዳዊትን ግልጋሎት አያገኝም።

የእርስበእርስ ግንኙነት

ሁለቱ በድኖች ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ (በ2008) ተገናኝተው ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና 5-1፣ ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ 2-0 አሸንፈዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-2-3-1)

አቤር ኦቮኖ

ፀጋሰው ዲለሞ – አዩብ በቀታ – ደስታ ጊቻሞ – ሄኖክ አርፊጮ

ይሁን እንደሻው – አፈወርቅ ኃይሉ

ሱራፌል ዳንኤል – ሱራፌል ጌታቸው – ቢስማርክ አፒያ

ቢስማርክ ኦፖንግ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ፀጋዬ አበራ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – ውብሸት ዓለማየሁ

በረከት ወልዴ – ተስፋዬ አለባቸው

እድሪስ ሰዒድ

ቸርነት ጉግሳ – ባዬ ገዛኸኝ – እዮብ ዓለማየሁ

© ሶከር ኢትዮጵያ