የትግል ፍሬ ትዝታዬ – በኤርሚያስ ብርሀነ

ይሄ ፅሁፍ ረጅም ነው – ምናልባት ለአንዳንዱ አሰልቺም ሊሆን ይችላል። እኔ ትዝታዬን ጽፌያለሁ፤ ስለፃፍኩትም ደስ ብሎኛል። ከቻላችሁ ሁሉንም አንብቡት፤ ካልቻላችሁ – የቻላችሁትን ያህል አንብቡት፤ ከከበዳችሁ ግን የምትወዱትን አድርጉ-ማለፍም ይቻላል፡፡ ይህን ሁሉ ትዝታ የሚጋራኝ ወንድሜና አብሮ አደግ ጓደኛዬ ኢሳያስ ብርሃኑ በዚያን ዘመን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አብሮኝ ስለኖረ እርሱ ደግሞ የድርሻውን ቢያክልበት ደስ ይለኛል። በዚህ የትውስታ ተረክ ውስጥ ገልህ ስህተት ያለ ከመሰላችሁ፣ የሚታረም ህጸጽ ካገኛችሁ እና ጊዜው ነጉዶ እንዲያው ነገረ-ታሪክ አምታትቼም ከሆነ ቅሬታችሁን ግለጹልኝ፤ ጉድለቴን ሙሉበት፤ ስህተቴን አርሙኝ። ጥያቄ ካላችሁም ደስ ብሎኝ የምችለውን አልያም የማስታውሰውን ያህል እመልሳለሁ።

አክባሪ ወንድማችሁ፦ ኤርምያስ ብርሃነ

” እንደው መቼ ይሆን በቂ ጊዜ አግኝቼ ስለ ትግል ፍሬ ትዝታዬ በፌስቡክ ገጼ ላይ በሰፊው የምጽፈው?” እያልኩ ረዘም ላለ ጊዜ ራሴን ጠይቄያለሁ፤ ብዙ አውጥቼ – አውርጃለሁ፡፡ አሁን ጊዜ አገኘሁ መሰለኝ – የምችለውንና የማስታውሰውን ያህል ይኸው ሞክሬያለሁ። የረሳሁትን በጊዜው አብሮኝ የነበረው አብሮ አደግ ጓደኛዬ “ኢሳያስ ብርሃኑ ያስታውሰኛል!” ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

የትግል ፍሬን – የቡድኑንም ሆነ የተጫዋቾቹን ትጥቅ የምንይዘው ሦስት ታዳጊዎች ነበርን። እኔ (ኤርምያስ ብርሃነ)፣ ኢሳይያስ ብርሃኑ እና የኢሳይያስ ታላቅ ወንድም አበበ ብርሃኑ ነበርን -ጊዜው ደግሞ 1972 ዓም። ትግል ፍሬ የተቋቋመው በ1971 ዓም ቢሆንም በይበልጥ የተጠናከረውና በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ቡድን የሆነው በ1972 ዓም የመኢሠማ (የመላው ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር) ቡድኖች በዘጠኙ ኢንዱስትሪዎች ስር እንዲዋቀሩ ከተደረገ በኋላ ነበር። በወቅቱ ለ<ትግል ፍሬ> የሚጫወቱት በፋብሪካዎች፣ በመንገድ ሥራ፣ በአውራ-ጎዳና እና ህንፃ ኮንስትራክሽን መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩት ተጫዋቾች ነበሩ። የ<እርምጃችን> ተጫዋቾች ደግሞ በመብራት ኃይል፣ በአስመጪና ላኪ እንዲሁም በሆቴሎች የሚሰሩት ሆኑ። በ<ወደፊት> ቡድን ውስጥ ደግሞ በትራንስፖርት፣ መድንና ባንክ የሚሰሩት ተጫዋቾች ተካተቱ። ይህ የድርጅቶችን መዋቅራዊ አደረጃጀት ተመርኩዞ የተፈጠረ አሰራር ሦስቱ ቡድኖች እንዲጠናከሩ- በተለይም ትግል ፍሬ በጣም ተወዳጅ እንዲሆን አደረገ፡፡ የትግል ፍሬ ተወዳጅነት ከዚያም አልፎ በቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን መፍረስ ምክንያት ከስታዲዮም የሸሸውን ተመልካች ለመመለስም አስችሎ ነበር። ይህ የሆነው ያለ ምክንያት አልነበረም። “በተሻሻለው” የክለቦች አወቃቀር መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1971 ዓም ከመፍረሱ በፊት በቡድኑ ይጫወቱ የነበሩት ታላላቆቹ አስራት ኃይሌ (ጎራዴው)፣ ሥዩም አባተ፣ ተስፋዬ ጥላሁን እና ፀጋዬ ገልጠው ወደ ትግል ፍሬ መቀላቀላቸው አንደኛው ምክንያት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የቡድኑ (ትግል ፍሬ) መለያ ደረቱ ላይ “V” ቅርፅ ባይኖረውም ብርቱካንማ ቀለም የነበረው መሆኑ – ከቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ጋር በጣም እንዲመሳሰል አድርጎታል።

እነዚህ ሁለት መሰረታዊ ግጥምጥሞች እንዳሉ ሆነው ከአስራአንዱ የትግል ፍሬ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች – አራቱ ከቀድሞው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን መፍረስ ሳቢያ ከስታዲዮም ርቀው የሰነበቱት ደጋፊዎች በብዛት ወደ ስታዲዮም መመለስ ቻሉ፡፡ ስታዲዮሙም በፍጥነት መሙላት ጀመረ፤ ትግል ፍሬም በጣም በርካታ ደጋፊዎች ኖሩት። በእርግጥም ትግል ፍሬ በጣም ጠንካራ ቡድን ነበር። አብዛኞቹን ጨዋታዎች በከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ያሸንፋል። ግብ ጠባቂው-ተስፋዬ ጎል አያስቀምስም፤ ፀጋዬ በቀኝ በኩል በቀላሉ የማይታለፍ ተከላካይ ሆነ፤ በጥሩ የአካል ብቃቱና በጠንካራ ምቶቹ የሚታወቀው አብዶ ከደር ከመለከላከል አልፎ በማጥቃት ሒደቱም እየተሳተፈ የተጋጣሚን ክልል መድፈር ጀመረ፤  ሸዋንግዛው ተረፈ- ዛሬም ድረስ በእርሱ ቦታ የርሱን ያህል ብቃት ያለው ተጫዋች አላየሁም- እንደ ላስቲክ እየተሳበ፣ በአየር ላይ ተንሳፎ በግንባርም ሆነ በመቀስ-ምት የሚመታቸው ኳሶች ዛሬም አይኔ ላይ አሉ። ሸዋ ከኋላ እየሄደ ለትግል ፍሬ ብዙ ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ ከሸዋ አጠገብ የሚሰለፈው አስራት ኃይሌ(ጎራዴ) ትግል ፍሬ እንደ ብረት የጠነከረ የተከላካይ መስመር እንዲኖረው አደረገ፤ መንግስቱ ቦጋለ የመሃል ሜዳው ሞተር ነበር- በኳስ ችሎታው ዛሬም ድረስ የሚወራለት ይህ አማካይ ለአጥቂዎች የሚሰጣቸው ግብ የሚሆኑ ቅብብሎች  (Assists) ከጉርሻ ከጉርሻ የሚተናነሱ አልነበሩም፡፡ የቀኝ መስመር አጥቂው አቦነህ ማሞ የባላጋራ ቡድን አራትና አምስት ተከላካዮችን አልፎ ግብ ማስቆጠር ልማዱ አደረገው- አይ ጸባይ! አይ የኳስ ችሎታ! በፊት መስመር ኳስን እንደፈለገ ያዛት የነበረውና ተመልካችን የሚያዝናናው ጥበበኛው በርሄ መኩሪያ የትግል ፍሬ አጥቂዎች ያገቡ ለነበሩ ብዙ ጎሎች መነሻ ነበር፡፡ ያን ቡድን በአምበልነት የመራው ተስፋዬ ጥላሁን በግንባር እየገጨ የሚያገባቸው ግቦች እንዲሁም የአየር ላይ ኳሶችን በደረቱ አብርዶ የሚከውናቸው ቅብብሎች ለቡደኑ ጨዋታ ማማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የፊት መስመር አጥቂው ዘውዱ ታከለ በጉልበቱ፣ በፍጥነቱና በኳስ ክህሎቱ ሁሌም የማይረሳ አሻራ አሳርፎብናል፥  ዘውዱ በቀላሉ የተጋጣሚ ግብ ክልል የመድረስ ችሎታውንና ግቦች የማስቆጠር ብቃቱንን ከብዙ ሺህ ተመልካቾች ጋር ሆነን አይተናልና በደስታ እንመሰክራለን። በግራ ክንፍ በኩል በማጥቃቱ ረገድ አስገራሚ ፍጥነትና ምርጥ የኳስ ችሎታ የነበረው ንጉሴ አስፋው ትግል ፍሬ ለዋንጫ በተፋለመበት የውድድር ዘመንም ሆነ በሌሎች ጨዋታዎች ግብ ባስፈለገው ጊዜ ሁሉ ለቡድኑ የሚደርስ፣ አከታትሎ ጎሎችን የሚያስቆጥርና የኮከብ ግብ አግቢዎች ፉክክርን ያሸነፈ ድንቅ አጥቂ ነበር። ታላቁ ሥዩም አባተም የዚህ ታሪካዊ ቡድን ደጀን ነበር፡፡ በተፈጥሯዊ የኳስ ችሎታው፣ ቅብብሎችን የሚቆጣጠርበት መንገድ ፣ በእግርኳስ አረዳዱ ሥዩም የተለየ ነበረ፡፡ በሁሉም ቦታ በመጫወት ብቃቱና በመልካም ባህርዩ የሚታወቀው ግርማ አብርሃም የትግል ፍሬ ምርጥ ቡድን አባል ነበር፡፡ ፈጣኑና የተከላካይ ቦታን ማራኪ በሆነ ሁኔታ ይጫወተው የነበረው ጌቱ ገብረማሪያም በትግል ፍሬ ውስጥ ካለፉት ድንቅ ተጫዋቾች መሃከል ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ በአጠቃላይ በ1972 ዓ.ም ትግል ፍሬ የመጀመሪያ  ተሰላፊዎቹም ሆኑ ተጠባባቂዎቹ ድንቆች ነበሩ። ስለዚያም ነበር ኃያላኑን-ምድር ጦርን፣ ፖሊስን፣ እርምጃችንንና ወደፊትን እያሸነፈ ለሁለት ዓመታት በወታደራዊ ቡድኖች ተወስዶ የነበረውን ዋንጫ ለማስመለስ ወደ መሪነቱ እስከመጠጋት የደረሰው።

በነገራችን ላይ የ1970 ዓም የሻምፒዮናው አሸናፊ ኦሜድላ (ፖሊስ) የነበረ ሲሆን በ1971 ዓ.ም ደግሞ ምድር ጦር ድሉን ተቀዳጅቷል። በ1972 ዓ.ም የሸዋ ሻምፒዮናን ዋንጫ ትግል ፍሬ ለመውሰድ ተቃርቦ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ከፖሊስ ጋር በነበረው የመጨረሻ ጨዋታ ህዝቡ በከፍተኛ ጉጉት ጠብቆት ውጥረት በበዛበት ፍልሚያ ፀጋዬ ገልጠው የፖሊሱ ንጉሴ ገብሬ ላይ በሰራው ጥፋት ፖሊሶች ፍፁም ቅጣት ምት ያገኛሉ፡፡ ኃይሉ ጎሹ ፍጹም ቅጣት ምቷን አግብቶ ፖሊስ አሸንፎ የሸዋ ሻምፒዮና ዋንጫውን ወሰደ። ትግል ፍሬም ሁለተኛ ሆኖ ጨረሰ። ምንም እንኳን ትግል ፍሬ የሸዋን ዋንጫ ቢያጣም ፖሊስን ተከትሎ ለኢትዮጵያ ሻምፒዮና አለፈ።

የ1972 ዓም የኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮን ከሸዋ- ፖሊስና ትግል ፍሬ፣ ከኤርትራ- ቀይ ባህርና ሰላም፣ ከሐረር ደግሞ ባቡርና ኢትዮ ሲሚንት አለፉ። ጨዋታዎቹ አዲስ አበባ ላይ ተካሄዱ። ትግል ፍሬ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከቀይ ባህር ጋር አደረገ። ቀይ ባህር ሳይጠበቅ በጣም ጠንካራ ቡድን ይዞ ቀረበ። የዚያን ዕለት ሃዲሽ፣ ተስፋ ሚካኤል፣ ተፈራ፣ ሚኪኤሌ እና ሌሎቹ የቀይ ባህር ተጫዋቾች ያሳዩት የጨዋታ በፍፁም አይረሳም። በመጨረሻ 0-0 ቢጠናቀቅም ቀይ ባህር ካሳዩት ብልጫ አንጻር ማሸነፍ ይገባቸው ነበር። ሁለተኛው የትግል ፍሬ ጨዋታ ማክሰኞ አመሻሹ ላይ እንደጀመረ ትዝ ይለኛል-ከኢትዮ ሲሜንት ጋር። በዚህ ጨዋታ ትግል ፍሬ ኢትዮ ሲሜንትን 7-0 ረምርሞ ለዋንጫ አለፈ። ከዛኛው ምድብ ደግሞ ፖሊስ የሐረሩ ሰላምን 3-0 አሸንፎ ከትግል ፍሬ ጋር በድጋሚ ለዋንጫ ተገናኙ። ትግል ፍሬም በሸዋ ሻምፒዮና ያጣውን ዋንጫ በኢትዮጵያ ክለቦች ዋንጫ ለመመለስ ተዘጋጅቶ ቀረበ።

በዚያ ዕለት የትግል ፍሬ አሰላለፍ የሚከተለውን ይመስላል:-

1.ተስፋዬ ዘለቀ 2.ፀጋዬ ገልጠው 3.አብዶ ከድር 4.ሸዋንግዛው ተረፈ 5.አስራት ሃይሌ (ጎራዴው) 6.መንግስቱ ቦጋለ 7.አቦነህ ማሞ 8.በረሄ መኩሪያ 9.ተስፋዬ ጥላሁን (አምበል) 10.ዘውዱ ታከለ 11.ንጉሴ አስፋው ነበሩ።

ጨዋታው እንደተጀመረ በጣም ከባድ ፉክክር ታየ። ሁለቱም በየተራ ጥሩ ሲያጠቁ ቆይተው ትግል ፍሬ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ንጉሴ አስፋው ባስቆጠረው ግሩም ግብ ማሸነፍ ቻለ፡፡ የትግል ፍሬ ደጋፊዎች ደስታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ገለጹ። ወዲያውኑ በካታንጋ እና በሌሎች ቦታዎች የነበሩ የፖሊስ ደጋፊዎች ህዝቡን ደበደቡት። ያው በመሸነፋቸው ተናደው ነበር። ይሁን እንጂ በጣም በርካታ ሰዎች ድብደባ ደረሰባቸው። እኔና ጓደኞቼ (ኢሳይያስና አበበ) ሳንመታ ቶሎ ወጥተን ትግል ፍሬ አርፎበት ወደ ነበረውና አሁን ቤተዛታ ሆስፒታል በሚባለው የዚያን ጊዜው ብሉ ናይል ሆቴል ገባን። ተጫዋቾቹ ዋንጫውን ይዘው እየጨፈሩ መጡ። እስከ ሰዓት እላፊ ድረስ ስንጨፍር አምሽተን ወደ ቤታችን ሄድን። ይህ የሆነው በ1972 ዓም ነው፡፡  ያኔ እኔ የአስራ ሁለት ዓመት ታዳጊና የሰባተኛ ክፍል የበየነ መርዕድ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ነበርሁ። ጠዋት ነግቶልኝ፥ ወደ ትምህርት ቤት ሄጄ ስለ ድሉ እሰካወራ ምንያህል እንደቸኮልኩ አልረሳውም። አይነጋ የለ! ደርሶልኝ በደንብ አወራሁት! በተለይ ዳንኤል ጉታ የሚባል አባቱ ፖሊስ የሆኑና ቡድኑን በጣም ይወድና ይደግፍ የነበረውን ጓደኛዬና የክፍሌ ልጅ እሲበቃኝ አበሸቅሁት፡፡ ሁሌም በምንደግፋቸው ቡድኖች ሰበብ የምንበሻሸቅ ጓደኛሞች ነበርን- አይ ጊዜ! ዳኒ ግን አሁን የት ይሆን ያለው?

ከላይ እንደገለጽሁት እኔ፣ ኢሳይያስና አበበ የትግል ፍሬ ቡድን ህልውናውን ጠብቆ በውድድር  በቆየባቸው ሥስት ዓመታት ውስጥ አብረናቸው የማንሄድበት ቦታ አልነበም። ለልምምድ-ቫርኔሮ ሜዳ፣ ለጨዋታ-ስታዲየም፣ ለወዳጅነት ግጥሚያዎች- ናዝሬት። ኧረ ስንቱ ቦታና ሰፈር ተጠቅሶ ያልቃል! ከርቸሌ መግባት ከባድ በነበረበት ጊዜ እንኳ በ1973 ዓ.ም ትግል ፍሬ ከከርቸሌ እሰረኞች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ሲያደርግ የትግል ፍሬ ቡድን መሪ የነበሩት ጋሽ ታደሰ አብደላ በኃላፊነት ፈርመውልን ገብተን ጨዋታውን ለማየት በቅተናል። በዚያ ጨዋታ ትግል ፍሬ በሸዋንግዛው ተረፈ ጎል ጠንካራውን የከርቸሌ እስረኞች ምርጥ ቡድን 1-0 አሸንፏል።

ትግል ፍሬ የ1972 ዓ.ም የውድድር ዘመንን በከፍተኛ ጥንካሬ አገባዶ በ1973 የበለጠ ተጠናክሮ ከተፍ አለ። የጥንካሬውም ምንጭ አዲስ የተጨመሩት ተጫዋቾች ነበሩ። ዳዊት ኃይለአብን፣ ሰለሞን (እንትዬን)፣ጋሻው ቅባቅዱስንና ጀማነህን-ከካራማራ፣ ደምስ ለማ (አራዊትን) ደግሞ ከጥቁር አንበሳ በማካተት ጠንካራውን ቡድን የበለጠ አጠናከረው። የእንትዬ እና አራዊት መጨመር በአስራት ኃይሌ (ጎራዴው) ወደ አሰልጣኝነት ማምራትና በፀጋዬ ከሃገር መውጣት ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት እንዲሸፈን አስቻለ። በችሎታም ሆን በጉልበት የተዋጣለቸው የነበሩት እነዚህ ሁለት የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች ትግል ፍሬን የማይደፈር ቡድን አደረጉት። ከእነርሱ ጋር አብሮ የመጣው የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ ዳዊት ኃይለአብ ደግሞ በሚገርም የእግርኳስ ችሎታው የትግል ፍሬን አጨዋወት አሳመረው፡፡ ፈጣኑ አጥቂ ቅብዓ-ቅዱስ የቡድኑን የፊት መስመር አስፈሪ አደረገው፡፡ 

በዚያን ጊዜ እግርኳሳችንን ለተከታተላችሁና ለምታስታውሱ 1973 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ እጅግ በጣም ጠንካራ የነበረበት ጊዜ እንደነበር አይዘነጋም። እኔ ያንን ዘመን የኢትዮጵያ እግርኳስ ሕዳሴ (Renaissance) ብዬ እጠራዋለሁ። በዚህም ብዙዎች የሚስማሙ ይመስለኛል፡፡ ሁሉም ቡድኖች ጠንካራ ተወዳዳሪዎች ነበሩ። ማንም ከማንም አይተናነስም ነበር። በቡድኖቹ መሃከል እምብዛም የደረጃ ልዩነት አይስተዋልም፡፡ በዚህም ምክንያት ትግል ፍሬ እነዚህንና ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ በማምጣቱ የበለጠ ተጠቃሚ ሆነ። የ1973 ዓ.ም የውድድር ዘመን ማራኪ፣ ፉክክሩም የሚገርም ነበር። ለእያንዳንዱ ቡድን ሁሉም ጨዋታዎች ፈታኞች ነበሩ። ጠንካራው ትግል ፍሬም-በተለይም በሁለተኛው ዙር-ሁሉንም ጨዋታዎች ቢያሸንፍም በእርምጃችን በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ  ዋንጫውን አጣ። በዚህ ዓመት ከፍተኛ የኳስ ችሎታ የነበረውንና ምርጡ አጥቂ  ሰሎሞን ወንድሙ፣ በግብ ማግባት ችሎታው፣ በጉልበቱና በፍጥነቱ ታዋቂ የነበረው ከበደ ሃይሌ እንዲሁም በተከላካይ ቦታ በጣም ምርጥ የነበረው ታሪኩ ሃይሌም ለትግል ፍሬ ታዋቂና ተወዳጅ መሆን ከፍተኛ አስተዋፆ አበርክተዋል፡፡

ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የ1973 ዓ.ም የሻምፒዮናው አሸናፊ እርምጃችን ሆነ። ትግል ፍሬ በዚሁ ዓመት መጨረሻ ለሸዋ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ከእርምጃችን ጋር ፍጻሜ ደረሰ፡፡ ነገርግን ወድድሩ በክረምቱ መግባት ምክንያት በ1974 መጀመሪያ ገደማ ተካሂዶ እርምጃችን ከአምስት-አምስት የፍፁም ቅጣት ምት ግቦች አስቆጥሮ በድጋሚ ዋንጫውን ከትግል ፍሬ ወሰደ። በ1973 መጨረሻ ላይ ሸዋንግዛው፣ አቦነህ፣ ንጉሴ እና ዳዊት ኃይለአብ ለብሄራዊ ቡድን ተመርጠው ጊኒ ከሄዱ በኋላ በዛው ቀሩ ። ዘውዱ ታከለም ከሃገር ወጣ፡፡ ስለዚህም በ1974 ትግል ፍሬ ተዳከመ፤ የቀደመ ጥንካሬውን ይዞ መቀጠልም ተሳነው። አዳዲስ ተጫዋቾች ከሁለተኛው ቡድን ቢያሳድግም ገና በመጀመሪያው ጨዋታ በአብዮት ፍሬ በሰፊ የጎል ልዩነት ተሸንፎ የውድድር አመቱን ጀመረ። እንደዛም ሆኖ እንደቀደሙት ዓመታት ኃያልነቱን ባያሳይም ትግል ፍሬ አመቱን በመልካም ውጤት አጠናቀቀ፡፡ ፌዴሬሽኑ የሃምሳ ቡድኖች ውድድር ሲጀምር የትግል ፍሬ ህልውና በ1974 የውድድር ዘመን ማብቂያ ላይ አከተመ።

ትግል ፍሬ በ1972 ዓ.ም እና በ1973 ዓ.ም ምርጥ ቡድን ነበር። ዋናው ብቻ ሳይሆን ሁለተኛውም ቡድን ጠንካራ ስለመሆኑ ብዙ ተብሎለታል። የትግል ፍሬ ሁለተኛው ቡድን በሁለተኛ ዲቪዥን ይወዳደር ነበር። ጨዋታቸውንም አባሲዮን እና ቫርኔሮ ሜዳዎች ላይ አካሂደዋል። የእነርሱም ጨዋታ አንድም ቀን  አምልጦን አያውቅም። ተወዳጅና ደስ የሚል ስብስብ ነበራቸው። ይህም ቡድን በ1972 ዓ.ም በፍጻሜ ጨዋታ በተቀናቃኙ የሸዋ ፖሊስ በፍጹም ቅጣት ምት ተሸንፎ ነበር ዋንጫ ያጣው። ግብ ጠባቂው-ባይሳ፣ መላኩ፣ እንዳልካቸው፣ ተሻገር፣ ሃይሌ፣ ዳዊት፣ ታዱ፣ መሰፍኔ፣ ዋሴ፣ ሳህሉ፣ መኮንን፣ ብርሃኑ፣ሃይሉ፣ ኦኬሎ፣ ጌታቸው አቲሞ፣ እና ሌሎችም የዚህ ቡድን አባላት ነበሩ።
የዚህ ቡድን ትውስታዬ አርባ ዓመታት ያስቆጠረ ረዥም ዘመን ያለፈው መስሎ አይሰማኝም፥ የትናንት ያህል በአእምሮዬ ይመላለሳል፡፡ ታዲያ እንዴት ነው በቀላሉ ከአእምሮዬ ጓዳ ወጥቶ  ልረሳው የምችለው? ያን ሁሉ ደስታ የሰጥኝን ቡድን እና ደስ የሚለው የልጅነትጊዜዬን መርሳት የማይታሰብ ነው፡፡

ቤታችን ከትግል ፍሬ ክለብ ፊት ለፊት ስለነበር ከተጫዋቾቹ እና ከቡድን መሪዎቹ ጋር ተግባብተን የትኛውም ቦታ መሄዱ ብዙም አልከበደንም። አብሮ አደግ ጓኞቼ ኢሳያስና አበበ ዘወተር አብረን ስለምንሆን ሁሌም ደስ ብሎን ከቡድኑ ጋር እናሳልፋለን። የቡድኑንም ሆነ የተጫዋቾቹን ዕቃዎች በታማኝነት ጠብቀን እንይዛለን፤ “አድርሱ!” የተባልንበት ቦታም በተገቢው ሰዓት እናደርሳለን። እነርሱም ለዚያ ውለታችን እንደ ወንድሞቻቸው ያዩናል፤ ስታዲዮምም ያለ ምንም ችግር ያስገቡናል። በዚያ እድሜ ከእነዚያ አይረሴ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ጋር በስታዲዮም- መልበሻ ክፍል ውስጥና የተቀያሪ ወንበር ላይ አብሮ መቀመጥ፣ ቡድኑ በሄደበት ሁሉ አብሮ መጓዝ ምን ያህል ደስተኛ ያደርገን እንደነበር እኛ ነን የምናውቀው። ተጫዋቾቹ በኳስ ችሎታቸው ብቻ ሳይሆን መልካም ስብዕና የተላበሱም ነበሩ።
ተስፋዬ ዘለቀ፣ ሰሎሞን እንትዬና ዳዊት ኃይለአብ የአካባቢያችን ልጆች ስለነበሩ በሚገባ ያውቁናል፤ ስለዚህም ሁሌ ይንከባከቡን ነበር። ፀጋዬ፣ አብዶ፣ ሸዋ፣ ጎራዴው፣ መንግስቱ ቦጋለ፣ አቦነህ፣ ዘውዱ፣ በረሄ፣ ተስፋዬ ጥላሁን፣ ንጉሴ አስፋው፣ ሳምሶን ሳላ፣ ስዩም አባተ፣ ወንድ ወሰን ስለሺ፣ ብርሃኑ ዋቅጅራ፣ ደምስ ለማ (አራዊት)፣ ሰሎሞን ወንድሙ፣ ከበደ ታሪኩ፣ ሽመክት በቀለ፣ መላኩ ፣ ኦኬሎ አቡላ፣ ምሳህሉ ብስራት፣ መኮንን ሮባ፣ ሃይሌ ኪዳኔ፣ ባይሳ በቀለ፣ ዋሴ ተስፉ፣ መስፍን ተረፈ፣ ታዱ ይልማ፣ ዳዊት ሽፈራው፣ ሃይሉ ወልደመድህን፣….. ሁሉም ወንድማዊ ፍቅር ሰጥተውናል። ለዛም ሁሌም ባለዕዳ ነበርን፤ነን፤ ሆነንም እንኖራለን። ሁሌም እናመሰግናቸዋለን። ሁሌም እንወዳቸዋለን። ከዚያ በተጨማሪ የቡድኑ መሪዎች እና ባለስጣናት የነበሩት ጋሽ ታደሰ አብደላ፣ ጋሽ ልዑል ሰገድ፣ ጋሽ ካሳሁን፣ ጋሽ ባልቻ፥ አሰልጣኞቹ ጋሽ ታደሰ (ጋሽ ታዴ)፣ ጋሽ ጌታቸው በኋላ ደግሞ ጋሽ አስራት ኃይሌ (ጎራዴው) ሁሌም እንደ ቤተሰብ እያዩን በእንብካቤ ይዘውን፣ ንፁህ ፍቅር እየሰጡን፣ በሥነ ምግባር አንጸውን ከቡድኑ ጋር ሁሉም ሥፍራ እየወሰዱን ደስታችንን እጥፍ ድርብ ላደረጉት ሰዎች የሚበቃ ምስጋና ያለኝ እይመስለኝም፡፡ ውለታቸውን በልጆቻቸውና በልጅ-ልጆቻቸው ያግኙት። 

በመጨረሻም-ትንሽ ወደፊት እንሂድ። ጊዜው በፈረንጆች አቆጣጠር 1989 ቦታው ዳላስ-ቴክሳስ ነው፡፡ እኔ ለሜሪላንድ ቡድን ስጫወት ተጋጣሚያችን የአትላንታ ቡድን ነበር፡፡ በአትላንታ ቡድን ውስጥ እንደ ነፍሴ እወዳቸው የነበሩት የቀድሞ የትግል ፍሬ ተጫዋቾች ሽዋንግዛው ተረፈ፣ አቦነህ ማሞ እና ንጉሴ አስፋው አሉበት። እነዚህን የልጅነት ጀግኖቼን ሜዳው ውስጥ ሳያቸው አይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ በጣም ከምወዳቸውና ከማከብራቸው ተጫዋቾች ጋር በአንድ ሜዳ መጫወቱ ለኔ ትልቅ ክብር፥ትልቅም ደስታ ሆነልኝ። መልሼ ሳስበው እውነት ሁሉ አይመስለኝም። ለፍጻሜ ለመድረስ የሚካሄድ ጨዋታ ነበረ። እኛ (ሜሪላንዶች) እስከመጨረሻው ታግለን ተጨማሪ ሰዓት ላይ ደረስን። የተጨመረው ሰዓት ሊያልቅ ሲል ንጉሴ አስፋው አስገራሚ ችሎታውንና ልምዱን ተጠቅሞ ባስቆጠራት ግብ አትላንታ አሸንፎን ለፍጻሜ በቃ።በጨዋታው ብንሸነፍም በጣም ከምወዳቸውና ከማከብራቸው፣ በፍቅር እደግፋቸውም ከነበሩት ወንድሞቼ ጋር በአንድ ሜዳ ላይ መጫወቴን እንደ ትልቅ ክብር እና ሞገስ አየሁት፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ለኔ እንደ ትልቅ የህይወት ስኬት እቆጥረዋለሁ፡፡

ስለ ፀሃፊው

ጸሃፊው በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ ያደገና ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የተደረጉ የዚያን ዘመን የሃገራችን እግርኳስ ጨዋታዎችን በአካል ተገኝቶ የተመለከተ፣ የጨዋታዎቹን አጠቃላይ ገጽታዎች በጥልቀትና በስፋት የሚያስታውስ እግርኳስ አፍቃሪ ነው፡፡ ከ1981 ዓ.ም በኋላ ነዋሪነቱን በአሜሪካ አገር ቢያደርግም አሁንም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሃገሩን እግር ኳስ ከመከታተል ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: