አምስት ተጫዋቾችን ያፈራው እና አራቱን ለስኬት ያበቃው የአሻሞ ቤተሰብ

አምስት ተጫዋቾችን እግርኳሰኛ አድርጎ አራቱን ስኬታማ ያደረገው ቤተሰብ ቅብብሎሽ።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ከአንድ ቤተሰብ ተገኝተው ስኬታማ የሆኑ ተጫዋቾችን ባለፉት ዓመታት ተመልክተናል፡፡ ዛሬ ይዘን የቀረብንላችሁ የአንድ ቤተሰብ አባላት ግን እጅግ በሚያስገርም መልኩ ቁጥራቸው ላቅ ያለ ነው። ይህም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የራሳቸውን ድርሻ ያበረከቱትን እና እያበረከቱም ያሉትን አምስት ተጫዋቾች አፍርቶ አራቱን ከፍ ባለ ደረጃ ያስመለከተን የአሻሞ ቤተሰብ ነው፡፡

ተወልደው ያደጉት ሀዋሳ ከተማ በተለምዶ ባህል አዳራሽ እየተባለ በሚጠራው ሠፈር ውስጥ ነው፡፡ ወንድማገኝ አሻሞ የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን እግር ኳስን ከቤተሰቡ ቀደም ብሎ በ1980ዎቹ መባቻ ላይ ቢጀምርም አባታቸው ‘አንተ ለትምህርት ያለህ አመለካከት ጥሩ ስለሆነ እግር ኳሱን ተው’ ይሉታል፡፡ የአባትን ምክር ሳያቅማማ የሰማሁ ወንድማገኝም በፕሮጀክት (ቤዛ ኮሌጅ) ይጫወት የነበረውን የእግር ኳስን አቁሞ ወደ ትምህርቱ ፊቱን ያዞራል። እሱም የሚናፍቀውን እግር ኳስ ትቶ አባቱ የሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ በትምህርቱ ራሱን ካጎለበተ በኃላ በኮንስትራክሽን ሙያ ውስጥ ገብቶ እግር ኳስን ለተከታይ ወንድሙ ያስተላልፋል።

1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በእግር ኳሱ ከታዩ ድንቅ የመስመር አጥቂዎች መሀል ይጠቀሳል ፤ የቤተሰቡ ፈር ቀዳጅ ጌታሁን አሻሞ (ጠገራ)። ይህ ተጫዋች ለሌሎች ወንድሞቹም መንገድ ከፋች ብቻም ሳይሆን በግሉ በስኬታማ ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ ላይ ሲያንፀባርቅ በብዙዎች ዓይን ውስጥ የማይረሳ ትዝታን አስቀርቷል፡፡ ሀዋሳ በተለምዶ አሮጌው ሜዳ እየተባለ በሚጠራበት እግር ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ ሲጫወት ነበር። 1993 የአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ አሰልጣኝ ተመልክተውት ወደ ክለቡ እንዲቀላቀል አደረጉት። በአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅም ባሳየው ጥሩ አቋም መነሻነት በትውልድ ከተማው የመጫወት ፍላጎት ስለነበረው 1994 ግማሽ ዓመት ላይ በወቅቱ የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ታመነ ይርዳው አማካኝነት ወደ ሀዋሳ የመጣው ጌታሁን በሀዋሳ ረዘም ያሉ ዓመታትን ያሳለፈ ሲሆን 1996 ክለቡ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ የቡድን አባል ነበር። በቀጣዩ ዓመትም ሀዋሳ ከተማ በድጋሚ ሁለተኛ ዋንጫውን በጥሎ ማለፍ ሲያስመዘግብ አሁንም የዚህ ቤተሰብ አንድ አካል የሆነው ጌታሁን ድርሻ ላቅ ያለ ነበር፡፡ ተጫዋቹ በወቅቱ ባሳየው አቋም መነሻነት ከሀዋሳ ከተማ እነሙሉጌታ ምህረት ፣ አዳነ ግርማ እና በኃይሉ ደመቀ ለሴካፋ ዋንጫ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲመረጡ ጌታሁንም ዕድሉን አግኝቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት የሴካፋ ዋንጫን መሳም ችሏል፡፡ ተጫዋቹ በዛው ሀዋሳን በመልቀቅ ለግማሽ ዓመት ብቻ ለመብራት ኃይል ተሰልፎ ጥቂት ጨዋታ ካደረገ በኃላ ዳግም ወደ ሀዋሳ ተመልሶ በ2002 ክለቡን ተቀላቀለ። ይሁን እና በዚሁ ዓመት ሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን በሜዳው ከደደቢት ጋር ሲያደርግ በነበረበት ወቅት በሁለተኛው አጋማሽ በደረሰበት የቁርጭምጭሚት ጉዳት ለአንድ ዓመት ከእግር ኳሱ በመራቅ በህክምና ላይ ካሳለፈ በኃላ በ2004 ዳግም ተመልሶ እስከ 2005 በንግድ ባንክ መጫወት ቢችልም ጉዳቱ ድጋሚ አገርሽቶበት ጫማውን እንዲሰቅል አስገድዶታል።

ሦስተኛው ሰለሞን አሻሞ (ጎማ) ይባላል። በእግር ኳስ ልዩ ችሎታ የነበረው ይህ አማካይ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የታዳጊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ኳስን በመጫወት የጀመረ ሲሆን በክለብ ቆይታው ደግሞ ለሻሸመኔ ከተማ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ደግሞ ለአዳማ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ 1990ዎቹ እግር ኳስን የጀመረው ይህ ተጫዋች ብዙ የመዝለቅ ዕድል የነበረው ቢሆንም ጉዳት መሰናክል ሆኖበታል። 1997 ወደ ሲዳማ ቡና አምርቶ ክለቡን ወደ ብሔራዊ ሊግ ማሳደግ ቢችልም ከተረከዙ በታች ያስተናገደው ጉዳት ልክ እንደ ወንድሙ ጌታሁን ሁሉ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑን አገባዶበታል፡፡ ጉዳቱ እግር ኳስን መጫወት ቢከለክለውም በአሁኑ ሰዓት በወሰደው የአሰልጣኝነት ስልጠና ታዳጊዎችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል።

ከቤተሰቡ ቀደም ብለን ከላይ የጠራናቸው ከእግርኳስ ተጫዋችነታቸው ቢገለሉም ሁለቱ ወንድማማቾች ግን አሁንም በፕሪምየር ሊጉ እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ የመስመር አጥቂው ኤፍሬም አሻሞ እና የተከላካይ አማካዩ ብርሀኑ አሻሞ። ኤፍሬም አሻሞ 1997 ላይ ነበር ወደ ሙገር ሲሚንቶ አምርቶ ከተስፋ ቡድን እስከ ዋናው ድረስ በመጫወት ከክለብ እግር ኳስ ጋር ትውውቅ የጀመረው። በሙገር ሲሚንቶ ቆይታውም አቅሙ እየጎለበተ በመምጣቱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ወደ ሀረር ቢራ ወስደውት በክለቡ መጫወት የቻለ ሲሆን ከሀረር ቢራ በኃላም በኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ደደቢት እና ወልዋሎ ዘንድሮ ደግሞ በመቐለ 70 እንደርታ እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተጠርቶ መጫወት የቻለው ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች በደደቢት እንዲሁም ባለፈው ዓመት የወልዋሎ ቆይታው ከታናሽ ወንድሙ ጋር በአንድ ክለብ ውስጥ የመጫወት ዕድል አግኝቷል፡፡

ብርሀኑ አሻሞ የመጨረሻ እና አምስተኛው ተጫዋች ነው፡፡ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ስር ለሀዋሳ ተስፋ ቡድን በመጫወት ወደ ክለብ ህይወት የገባሁ ይህ ወጣት የተከላካይ አማካይ በ2009 ወደ ዋናው ሀዋሳ ቡድን በማደግ ተጫውቷል፡፡ ሆኖም በክለቡ የመሰለፍ ዕድልን ማግኘት ባለመቻሉ ታላቅ ወንድሙ ኤፍሬም አሻሞ በደደቢት ይጫወት ስለነበረ በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ አማካኝነት ወደ ወንድምዬው ክለብ ሊያመራ ችሏል፡፡ በደደቢት የግማሽ ዓመት ብቻ ቆይታ አድርጎም እስካለፈው ዓመት ድረስ በወልዋሎ ዘንድሮ ደግሞ በሲዳማ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

ከአንድ ቤተሰብ ወጥቶ በእግር ኳሱ የማንፀባረቅ ሚስጥራቸው ምን እንደሆነ ኤፍሬም አሻሞ ሲናገር ” አብዛኛዎቻችን ሠፈር ውስጥ ነው ያደግነው። በሠፈራችን ኳስን የሚወዱ ብዙ ሰዎች ነበሩ ፤ መጫወትም የሚችሉ። የዕድል እና የጊዜ ጉዳይ ሆኖ እኛ ተሳክቶልናል ፤ እንደ ቤተሰብም ኳስ ተጫዋች የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ነበረን። ይህ ይመስለኛል እግር ኳስ ላይ እንድናተኩር ያደረገን ፤ ከእግር ኳሱ ሌላ ሙያ የለንም ነበር። በጣም አስበልጠን የምንወደው ኳስን ብቻ ስለሆነ ከእኛ የሚበላልጡትን እያየን አካባቢያችን ታቦር ትምህርት ቤት ስላለ እዛ ሜዳ እየሄድን እንጫወታለን። ከትምህርት ቤት ሁላችንም ስንወጣ የምንጫወተው ኳስን ብቻ ነበር። ትምህርት እያቋረጥን እንኳን ለኳስ ነበር ትኩረታችን። ቤተሰቦቻችን የሚፈጥሩብንም ጫና የለም ፤ እንደውም አባታችን ጫና የፈጠረው ታላቅ ወንድማችን ላይ ነበር። እሱ ትምህርትን በመቀበል አዕምሮው ፈጣን ነበር። ‘ከኳስ አንፃር የተሻለው ትምህርት ላይ ነው’ ብሎ እሱን ብቻ ነው ወደ ሌላ ሙያ ያስገባው። እንጂ እኛን ኳስን አይከለክለንም ነበር። እናታችን ደግሞ ከልምምድ ስንመጣ በጣም ትንከባከበን ነበር። ይህ ይህ ተደምሮ ስኬታማ አድርጎናል” በማለት ሀሳቡን አጋርቶናል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: