ስለ አንዋር ያሲን (ትልቁ) ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

አንድ አማካይ ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮች ሁሉ አሟልቶ እንደያዘ ብዙዎች የሚመሰክሩለትና ኢትዮጵያዊው ዚዳን ሲሉ የሚያሞካሹት የዘጠናዎቹ የመሐል ሜዳ ኮከብ አንዋር ያሲን “ትልቁ” ማነው?

በየመን እግርኳስ ቤተሰቦች ዘንድ “ካፒቴን” በሚል ቅፅል ሰም ይጠሩታል። አንዋር ትውልድ እና ዕድገቱ ኮልፌ 18 ማዞርያ ነው። በ1983 ከእርሻ ሰብል ሲ ቡድን እስከ በዋናው ቡድን ድረስ መጫወት የጀመረው የክለብ ህይወቱ ብዙም ሳይቆይ ከ1984–86 ድረሰ ለሁለት ዓመታት ለኦሜድላ መጫወት ችሏል። ኦሜድላ እያለ በኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለት ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ የተማረከው ኤሌትሪክን አንዋን በመውሰድ ለስድስት ዓመታት ክለቡን እንዲያገለግል አድርጎታል።

ኢትዮጵያዊው ዚዳን እየተባለ የሚጠራው የመሐል ሜዳው ሞተር አንዋር የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ መካሄድ በጀመረበት በ1990 የመጀመርያው ዋንጫን ከመብራት ኃይል (ኢትዮ ኤሌትሪክ) ጋር ከማንሳቱ በተጨማሪ የውድድሩን መጀመርያ የኮከብ ተጫዋች የመሆን ክብር አግኝቷል። በ1991 ከኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር ከተለያየ በኃላ ለአንድ ዓመት ያህል ኢትዮጵያ ቡና ቆይታ አድርጓል። በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ መቼም የማይዘነጋው የ1992ቱ የአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያ ቡና ከግብፁ ሀያል ክለብ ዛማሌክ ጋር ሲጫወት በሁለቱም የደርሶ መልስ ጨዋታ ላይ ያስቆጠራቸው ሁለት ግሩም ጎሎች የአንዋርን ድንቅ ብቃት አጉልተው የሚመሰክሩ ናቸው። በባህሪው ዝምተኛ እንደሆነ ቢነገርም ሜዳ ውስጥ ግን ኳስ ሲበላሽ አይወድም፣ ይቆጣል የሚባለው አንዋር በቡና አንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ወደ የመን ቢያመራም በ1995 አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡናን ለማሰልጠን በተረከበበት ወቅት ዳግም ለአንድ ዓመት ከየመን ተመልሶ ለኢትዮጵያ ቡና ተጫውቷል።

በሁለቱም እግሩ መጫወት የሚችለው እና በየትኛውም ቦታ እግሩ ኳስ ሲገባ የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል ብዙዎች የሚመሰክሩለት ይህ የመሐል ሜዳ ፈርጥ ዳግመኛ በክለብ ደረጃ በኢትዮጵያ ተመልሶ ላይጫወት እግርኳስን እስካቆመበት 2001 ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገሩ እየተመላለሰ በየመን በጥቅሉ ለአስር ዓመት ያህል እየተወደደ መጫወት ችሏል። “አንዋር አንድ ግለሰብ ቢሆንም ግን ቡድን ነው፤ የእግርኳስ ሒደቱን በሚገባ ያውቀዋል።” ይሉታል። በሁለት አጋጣሚ በጉልበት ጉዳት ክፉኛ በመቸገሩ የቀዶ ጥገና አድርጎ የነበረው አንዋር ወደ እግርኳስ ማብቂያ ዘመኑ አካባቢ ተጫዋች አሰልጣኝ በመሆን በየመን ቆይታ ማድረጉ ይነገራል።

አንድ ተመልካች (በተቃራኒ የሚጫወት ተጫዋች) አንድ ተጫዋች እግሩ ኳስ ሲገባ ይህን ሊያደርግ ነው ብሎ ቀድሞ የሚገምት ነገር አለ ፣ አንዋር ግን በተመልካችም ፣ በሌላም ተጫዋችም ከሚገምተው (ከሚታሰበው) ውጭ የሚያደርግ ትልቅ ተጫዋች ነው የሚባልለት አንዋር የመን በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ ወደ ሀገሩ በመምጣት ወደ አሰልጣኝነት ጎራው በመቀላቀል በኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ በም/አሰልጣኝነት ሲያገለግል ከ2002 በኋላ በድጋሚ ከ2011 ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በዋና አሰልጣኝነት ማገልገሉ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወጣት እና ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው ይህ ድንቅ አማካይ በዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከቦች አምዳችን ስለ አጠቃላይ የእግርኳስ ሕይወቱ የሚከተለውን ብሎናል።

“በግሌ በተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉ ስኬታማ ተጫዋች ነበርኩ። አንድ ተጫዋች ከሲ ቡድን ወደ ላይ ለመውጣት ብዙ ሂደት ይፈልጋል። እኔ ግን ከሲ ቡድኑ ጋር ዋንጫ አንስቼ ወድያውኑ ነበር ወደ ዋናው ቡድን ያደኩት። በወጣት ብሔራዊ ቡድን ተመረጥኩ ከዛም በሀገሬ በተለያዮ ክለቦች ተጫውቻለው፣ የመን ጥሩ የሚባል ቆይታ ነበረኝ። በአጠቃላይ በግሌ በሁሉም ነገር ደስተኛ ነኝ።

” በእግርኳስ ህይወቴ አላሳካሁትም ብዬ በማሰብ ሁሌም እንደተቆጨው ነው። ምንም እንኳን የሊጉን የመጀመርያ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ባነሳም ከዚህ በላይ የምፈልገውን ዋንጫ አላገኘሁም። በተለይ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ አንድ ነገር ባለማድረጌ ሁሌም ይሰማኛል። ማድረግ የምንችልበት አቅም ኖሮን ይህን አለማሳካቴ ለምሳሌ የአፍሪካ ዋንጫ ሀገሬን ባለማሳለፌ፣ የሴካፋ ዋንጫ አለማንሳቴ፣ በአጠቃላይ ሀገሬን ወክዬ ስሟን አለማስጠራቴ ይቆጨኛል።

“በአሰልጣኝነት ህይወቴ ደስተኛ ነኝ። ባሰለጠንኩባቸው ክለቦች ሁሉ ጥሩ ቆይታ አድርጌያለው። ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋርም ቢሆን ሦስት ነገሮችን እንዳሳካ ነበር የተነጋገርነው። የቀድሞ የክለቡን የአጨዋወት ባህል መመለስ፣ ከታች ለሚገኙ ታዳጊዎች በቂ እድል መስጠት እና አንደኛ ሆኖ መጨረስ ነው። በአጨዋወት ደረጃ ጥሩ እግርኳስ የሚጫወት ብቻ ሳይሆን የጎል ዕድል መፍጠር የሚችል ቡድን መስራት ተችሏል። ያው ዋናው ውጤት መለኪያው ስለሆነ እንጂ። ለታዳጊዎችም ከመቼውም ጊዜ በላይ አቅም ያላቸውን ልጆች ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ መጠቀም ተችሏል። ይህን ልጆቹ የሚመሰክሩት ይሆናል። ወደ ላይ ለመውጣት በከፍተኛ ሊጉ አንድ ቡድን ብቻ የሚያድግ በመሆኑ ትዕግስት ከማጣት እና ውጤት ከመፈለግ ጋር ተያይዞ በጊዜ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ተለያየሁ እንጂ በሁሉም መልኩ በአሰልጣኝነት ቆይታዬ ደስተኛ ነኝ። አሰልጣኝ አብርሐም መብራቱ አብሬው እንድሰራ ደውሎልኛል። (አሁን ላይ ይሄን ማለት ባልችልም።) ወደ ፊት ሀገሬን የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎቱ አለኝ።

“ብዙ ቅፅል ስም አውጥተው እንደሚጠሩኝ ብሰማም በተደጋጋሚ ዚዳን በሚለውን ስም ሲጠሩኝ እሰማለው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔ ለቅፅል ስም አልመችም (እየሳቀ)፣ ሆኖም አንዳንዶቹ በደብዳቤ፣ በአካልም ኢትዮጵያዊው ዚዳን እያሉ ይጠሩኛል። እኔም ስቀልድባቸው ዚዳን የምትሉኝ መላጣዬ ተመሳስሎባቹሁ ነው እላቸዋለው።

“በቤተሰብ ህይወቴ ከባለቤቴ የወለድኳቸው ሦስት ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ። ወንዶቹ በጠቅላላ እግርኳስን የሚወዱ ናቸው። የመጀመርያው ልጄ መሐመድ በባህሪው ዝምተኛ ነው። ነገር ግን በእግርኳስ የተከፈ ነው ማለት ይቻላል። ኳስ ሲያይ ስሜቱን መቆጣጠር አይችልም። እንዲያውም በአንድ አጋጣሚ ከሚማርበት ትምህርት ቤት ተጠርቼ ሄድኩኝ፤ መምህሯ አንተ የመሐመድ አባት አንዋር ነህ? አዎ አልኳት ልጅዎ ከፍተኛ የእግርኳስ ፍቅር፣ ስሜት አለው እያለች ትናገራለች። በዚህ አጋጣሚ አንድ ሌላ አስተማሪ ጓደኛዋ ይመጣና እንዴ ! በጣም የምወደው ሰው ብሎ ሠላም አለኝ። ‘አታቂውም እንዴ? ይሄ እኮ.. እንዲህ.. እንዲህ..’ ብሎ ስለ እኔ ያስረዳታል ከዛ ” እንዴ አቶ አንዋር ምነው መጀመርያውኑ እግርኳስ በደሙ እንዳለ አይነግሩኝም ነበር እንዴ? ያለችውን መቼም አልረሳውም። አሁን አስራ ሰባት ዓመቱ ነው። ኤልፓ ሲ ለሙከራ ሄዶ ብዙ ሰው ስለነበረ ሳይመለከቱት ተመልሶ መጥቷል። አሁን ቤተል ድሪም በሚባል ቡድን ውስጥ እየተጫወተ ይገኛል። ካለው የኳስ ፍቅር የተነሳ ወደ ፊት ተስፋ አደርጋለው ጥሩ ተጫዋች እንደሚሆን።

” እኔ ስለ እራሴ መመስከር አልችልም። በጣም ይከብደኛል ይሄን ያህልም የሚወራልኝ ተጫዋች አይደለሁም። ሁሌም ማድረግ የነበረብኝን አለማድረጌ ነው የማስበው። አሁን ላለው ትውልድ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ሙያቸውን እንዲያከብሩ እና ትዕግስት እንዲያደርጉ ነው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ