ይህንን ያውቁ ኖሯል? (፫) | የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ክለቦች…

በተከታታይ ሁለት ሳምንታት በይህንን ያውቁ ኖራል? አምዳችን ስለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ክለቦች እውነታዎችን ስናቀርብ ቆይተናል። ዛሬም በሦስተኛ ክፍል 10 የሊጉ እና የክለቦችን እውነታዎች እናነሳለን።

1 – በሊጉ ታሪክ ሁለት ክለቦች ተመሳሳይ ነጥብ አምጥተው ዋንጫ ለመውሰድ የግብ ክፍያ የታየበት አጋጣሚ በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ተከስቷል። የመጀመሪያው አጋጣሚ የተከሰተው በ1990 ዓ/ም ነው። በዚህ የውድድር ዓመት መብራት ሃይል እና ኢትዮጵያ መድን እኩል 32 ነጥቦችን አስመዝግበው ነበር። ነገርግን በ14 የሊጉ ጨዋታዎች 37 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው መብራት ሃይል በ2 የላቀ የግብ ልዩነት(21) የሊጉን ዋንጫ አሸንፏል። ሁለተኛው አጋጣሚ ደግሞ የተፈጠረው በሊጉ የ20ኛ ዓመት(2010) በዓል ላይ ነው። በዚህ ዓመት ጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እኩል 55 ነጥቦችን ሰብስበው ጅማ ከጊዮርጊስ ያነሰ ግቦችን በማስተናገዱ ምክንያት የተሻለ የግብ ልዩነት በማምጣቱ ዋንጫውን ወስዷል።

2 – ከተከታዩ(2ኛ ካለው) ክለብ በብዙ ነጥቦች ርቆ ዋንጫ ያሸነፈው የሊጉ ብቸኛ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቡድኑ በ2002 ዓ/ም 9ኛ የሊግ ዋንጫውን ወደ ካዝናው ሲያስገባ ከተከታዩ ደደቢት በ24 ነጥቦች ርቆ ነው ዋንጫውን በ84 ነጥብ የወሰደው። ከ24 ነጥቦች በተጨማሪ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ2006 ከኢትዮጵያ ቡና በ20 ነጥቦች ልቀው ዋንጫውን ያሸነፉበት ዓመት ሁለተኛው ሪከርድ ሆኖ ተመዝግቧል።

3 – በ22 ዓመት የሊጉ ጉዞ 51 ክለቦች ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህ 51 ክለቦች 39ኙ በተለያዩ አጋጣሚ የመውረድ እጣ አጋጥሟቸዋል።

4 – በየውድድር ዓመቱ ከወረዱት ክለቦች መካከል በአንፃራዊነት ከፍተኛ ነጥብ አስመዝግቦ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የወረደው ክለብ ኢትዮጵያ መድን ነው። በ18 ክለቦች መካከል በተደረገው የ2002 ዓ/ም የሊጉ ውድድር 40 ነጥቦችን ሰብስቦ 15ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ሊጉን ያጠናቀቀው መድን በቀጣይ ዓመት የሊጉ ተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 16 በማነሱ ሊጉን ተሰናብቷል።

5 – በተቃራኒው በየውድድር ዓመቱ ከወረዱ ክለቦች መካከል በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ነጥብ አስመዝግቦ ሊጉን የተሰናበተው ክለብ ፐልፕ እና ወረቀት ነው። ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ መልክና መዋቅር በተጀመረው የ1990 ውድድር ላይ 5 ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ ከሊጉ ወርዷል። ነገርግን ከጨዋታ ቁጥር አንፃር ሊጉን በአነስተኛ ነጥብ የተሰናበተው ክለብ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ነው። አርባምንጭ በ1997 ባከናወናቸው 26 የሊጉ ጨዋታዎች 7 ነጥቦችን ብቻ ነበር የሰበሰበው።

6 – በአንድ የውድድር ዓመት ዝቅተኛ ነጥብ አስመዝግቦ ከሊጉ ያልወረደው ክለብ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ነው። ኮምቦልቻ በ1990 ዓ/ም በተደረገው የሊጉ ውድድር 10 ነጥቦችን ብቻ አግኝቶ ከሊጉ ሳይወርድ ቀርቷል። ኮምቦልቻ ያልወረደበት ምክንያት ደግሞ በ1991 ዓ/ም የሊጉን ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ከ8 ወደ 10 ለማሳደግ በመታሰቡ ነው።

7 – በሊጉ ታሪክ ብዙ ጊዜ የመውረድ እጣ ፈንታ የደረሳቸው ክለቦች ሦስት ናቸው። ኒያላ፣ ጉና ንግድ እና ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ሦስት ሦስት ጊዜ በመውረድ ቀዳሚዎቹ ክለቦች ሆነዋል።

8 – በሊጉ ታሪክ ዋንጫ አሸንፎ የወረዱ ክለቦች ሁለት ናቸው። እሱም መብራት ኃይል (ኢትዮ ኤሌክትሪክ) እና ደደቢት ናቸው። ኤሌክትሪክ በ1990 እና በ1993 ዓ/ም የሊጉን ዋንጫ ሁለት ጊዜ ወስዶ በ2010 ዓ/ም ወደታችኛው የሃገሪቱ የሊግ እርከን ወርዷል። ደደቢት ደግሞ በ2005 አሸንፎ በ2011 ወርዷል።

9 – በአንድ የውድድር ዓመት አነስተኛ የሊግ ጨዋታዎች የተደረጉበት ዓመት በ1990 ዓ/ም የተደረገ ነው። በዚህ ዓመት የተሳተፉት 8 ክለቦች እያንዳንዳቸው 14 ጨዋታዎችን በአንድ ዓመት ውስጥ አድርገዋል። በአጠቃላይ ደግሞ 56 ጨዋታዎች በውድድር ዓመቱ ተከውነዋል።

10 – በአንድ የውድድር ዓመት በርካታ የሊግ ጨዋታዎች በክለቦች መካከል የተደረገበት ዓመት ደግሞ በ2002 ዓ/ም ነው። በዚህ ዓመት በተደረገው የሊግ ውድድር 18 ክለቦች ተሳትፈው እያንዳንዳቸው 34 ጨዋታዎች በዓመቱ አከናውነዋል። በአጠቃላይ ደግሞ በሊጉ 306 ጨዋታዎች ተደርገዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: