የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብስባ አደረገ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዛሬ ሰኔ 10/2012 ዓ.ም በዙም ቴክኖሎጂ በመታገዝ የቪዲዮ ኮንፍረንስ አካሂደዋል፡፡ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ተጠናቋል፡፡

ሙሉ መረጃው የፌዴሬሽኑ ነው

1ኛ. የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ ቀደም በየክልሎቹ በመጓዝ ባደረገው ክትትል እና ድጋፍ መሰረት የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ እና የተሻለ አደረጃጀት እንዲኖራቸው ለማድረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካለው በጀት በመቀነስ የ2ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺህ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ወሳኔ ተላልፏል፡፡ ድጋፉም ክልሎቹ ባላቸው የእግር ኳስ እንቅስቃሴ መሰረት የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ ኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፤ ደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን እያንዳዳቸው የ300 ሺህ ብር ድጋፍ፤ እንዲሁም ቤኒሻንጉል ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ አፋር ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ኢትዮ ሶማሌ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ የጋምቤላ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የሀረሬ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን እያንዳንዳቸው የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ተወስኗል፡፡

2ኛ. የኮሮና ቫይረስ ወርርሽኝ በ2012 ሲካሄዱ የነበሩ ውድድሮች እንዲሰረዙ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል፡፡በቀጣይ በ2013ዓ.ም የሚጀመሩ የሊግ ውድድሮችን በምን መልኩ ማካሄድ እደሚገባ የሚያጠና እና የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡

3ኛ. ለ2013 ጠቅላላ ጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ከወዲሁ እዲጀመሩ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

4ኛ. ክለቦች ያለባቸውን የተጫዋቾች ውዝፍ ደመወዝ ከፍለው እስከ ሐምሌ 5/2012ዓ.ም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሪፖርት እንዲያደርጉ ከዚህ ቀደም በተላከላቸው ድብዳቤ የተገለጸላቸው ሲሆን፤ የተጣለባቸውን ግዴታ እሰከ ተጠቀሰው ጊዜ ያልተወጡ ክለቦች የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ተጫዋቾችን እንዳያዛውሩ እና ውል እንዳያድሱ እንዲደረግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወስኗል፡፡

5ኛ. በጊዚያዊ ጽ/ቤት ኃላፊነት ፌዴሬሽኑን ሲመሩ የቆዩት አቶ ባህሩ ጥላሁን የፌዴሬሽኑ ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ የተወሰነ ሲሆን፤ የክለብ ላይሰንሲንግ ማኔጀር የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ በክለብ ላይሴንሲንግ ዳይሬክቶሬት ደረጃ እንዲሰሩ ተወስኗል፡፡

6ኛ. ለኢትዮጵያ መድን፤ ኢትዮጵያ ቡና፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ አዳማ ከነማ፤ ኒያላ፤ ጉና ንግድ፤ ወንጂ ስኳር፤ ሻሸመኔ ከነማ እንዲሁም ወደ የመን በመጓዝ ለ7ዓመታት ውሃደሰንአ ለተሰኘ ክለብ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተለያዩ ደረጃዎች ለታዳጊ፤ ወጣት፤ ለኦሎምፒክ እና ዋናው ብሄራዊ ቡድን የተጫወተው ጌታሁን መንግስቱ በአሁን ሰዓት ኑሮውን በጎዳና እየገፋ መሆኑን ለፌዴሬሽኑ በማሳወቁ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የ50 ሺህ ብር ድጋፍ እንዲደረግለት እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካፍ አካዳሚ ውስጥ በቋሚነት ስራ እንዲሰራ ጽ/ቤቱ በሙያው ሚሰራበት ስራ ዘርፍ እንዲፈልግለት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዛሬ ውሎው ወስኗል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ