ሶከር ሜዲካል | የአንጎል ጉዳት በእግርኳስ

ከእግር ኳስ የተያያዙ የህክምና ጉዳዮችን በምንዳስስበት የሶከር ሜዲካል ዓምዳችን የዛሬ ፅሁፍ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባውን እና እንደ እግርኳስ ባሉ የንክኪ ስፖርቶች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የአንጎል ጉዳት የምንመለከት ሲሆን ጉዳቱ ካጋጠመ በኋላ ተጫዋቾች በጥሩ ሁኔታ እንዲያገግሙ መደረግ የሚኖርባቸውን እርምጃዎች የምንመለከት ይሆናል።

እግር ኳስ በከፍተኛ ፍጥነት የሚከወን የንክኪ ስፖርት እንደመሆኑ በሜዳ ላይ ግጭቶች የተለመዱ ናቸው። ጭንቅላት ላይ የሚደርሱ ግጭቶች ደግሞ ለአንጎል ጉዳት ያጋልጣሉ። የሰውነታችን ሁሉም መስተጋብር በአንጎላችን መሪነት ከመደረጉ አንፃር ይህ አደጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በጨዋታ ወቅት ኳስን በግንባር መግጨት የተለመደ ነው፤ በዚህ መልኩ ኳስን ደጋግሞ መግጨት እንዲሁም በእንቅስቃሴ ሂደት የተጫዋቾች እርስ በእርስ መላተም እነዚህ የአንጎል ጉዳቶች እንዲፈጠሩ ሊያደርጉ ይችላሉ።

በቀደሙት ዓመታት በትልልቅ የአውሮፓ እግርኳስ ሃገራት እና ውድድሮች ጭምር በጭንቅላት ግጭት የሚደርሱ ጉዳቶች እንደሌላው እግር ኳስ ላይ እንደሚያጋጥም ማንኛውም አደጋ ነበር የሚታዩት። በአሁኑ ወቅት ግን  ጉዳቱ በአጭር እና ረጅም ሊያመጣቸው የሚችሉ ችግሮች እና መዘዞች ከግምት ውስጥ ስለሚገቡ ግልፅ የሚባል የህመም ስሜት በማያሳዩ ተጫዋቾች ላይ እንኳን በቂ ምርምራ ካልተደረገና ምንም ችግር እንደሌለ ካልተረጋገጠ ተጫዋቾቹ ወደ ሜዳ እንዲመለሱ አይፈቀድም።

አንድ ተጫዋች አንጎሉ ላይ ጉዳት ገጥሞታል ለማለት የግድ እራሱን መሳት የለበትም። የዚህ ጉዳት መገለጫዎች የተለያዩ ሲሆኑ ከታች የተገለፁትን የተለያዩ ምልክቶችም ሊያሳዩ ይችላሉ።

 1. የራስ ምታት
 2. ራስን ማዞር
 3. ማቅለሽለሽ
 4. የመርሳት ችግር
 5. ሚዛንን መጠበቅ አለመቻል
 6. የባህሪ ለውጥ

የጭንቅላት ግጨት ያጋጠመው አንድ ተጫዋች ወደ ሜዳ በቶሎ አይመለስም። ይልቁንስ ስሜቶቹ በጊዜ ሂደት በሚታዩበት መልኩ የሚቀጥል ሲሆን Graduated Return to Play (GRTP) የተሰኘውን መመሪያ በመጠቀም ወደ ሜዳ መመለስ እና አለመመለስ መቻሉ የሚወሰን ይሆናል። እንደ ቀድሞው የሀል ሲቲ ተጫዋች ራየን ሜሰን ከፍተኛ ግጭት ያጋጠማቸው ተጫዋቾች እስከመጨረሻው ከእግር ኳስ እንዲርቁ የሚወሰንበት አግባብም ሊኖር ይችላል። በአብዛኛው ጊዜ አንድ ተጫዋች ከአንጎል ጉዳት በኋላ ወደ ሜዳ የመመለሱ ጉዳይ እና የሚመለስበት የጊዜ ሠሌዳ የሚወሰነው ተጫዋቹ በድጋሚ ለተመሳሳይ ጉዳት ቢዳረግ በጤናው እና በህይወቱ ላይ ሊያመጣው የሚችለው አደጋ ምን ያህል እንደሆነ በመተንበይ ነው።

ከእዚህ በፊት በሶከር ሜዲካል አምዳችን ለማስፈር እንደሞከርነው በተደጋጋሚ ኳስን በግንባር መግጨት በራሱ ለጉዳት ሊዳርግበት የሚችል አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። በአጭር ጊዜ ከሚኖሩ ጉዳቶች በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ እና ተጫዋቾች ከሜዳ ከተገለሉ ረጅም ዓመታትን ቆይተው የሚከሰቱ ህመሞች አሉ። ከእነዚህም አንዱ እና ዋንኛው Chronic Traumatic Encephalopathy (CTE) ሲሆን የነርቭ ስርአት በመዛባቱ የሚመጣ እና በተደጋጋሚ የጭንቅላት ግጭቶች የሚከሰት ነው።

በዚህ ርዕስ ውስጥ አፅዕኖት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ውስጥ በሜዳ ላይ የጭንቅላት ጉዳት ሲያጋጥም መደረግ ያለባቸው አፋጣኝ እርምጃዎች በዋንኛነት የሚጠቀሱ ሲሆን እነርሱም እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል።

 • ምን ምልክቶች እንዳሉ መለየት
 • ተጫዋቹ እራሱን መሳቱን እና አለመሳቱን ማረጋገጥ፤ ራሱን ስቶም እንደሆነ የአየር መተላለፊያ ቱቦ እንዳይዘጋ ማድረግ
 • የአእምሮውን ሁኔታ ለማወቅ ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ
 • አንገቱ ላይ ስብራት መኖር እና አለመኖሩን ማረጋገጥ
 • በ72 ሰአታት ውስጥ ሙሉ ምርመራ አድርጎ ችግሩን ማወቅ

 

ምንም እንኳን የአንጎል ጉዳት አስከፊ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ትክክለኛው ህክምና እና ክትትል ከተደረገ በጥሩ ሁኔታ ማገገም ይችላሉ። ነገር ግን ሁሉም የጭንቅላት ጉዳቶች በሚታከሙበት ወቅት የባሰው ነገር ሊደርስ እንደሚችል  ታስቦ መሆን አለበት። ይህ ጉዳት ሲደርስ ተጫዋቾች ወዲያውኑ ከሜዳ እንዲወጡ መደረግ አለባቸው። ጉዳት የከፋ ሊሆን እንደሚችል እስከታሰበ እና ጥርጥሬ እስካለ ድረስ የተጎዳው ተጫዋች በቅፅበትወደ ሜዳ ተመልሶ እንዲጫወት መደረግ የለበትም።

የአንጎል ጉዳት በሚያጋጥምበት ወቅት ተያይዞ በጭንቅላት አቅራቢያ የሚገኙ የጀርባ አጥንቶች (cervical spine) ሊጎዱ ስለሚችሉ ለእነርሱ የሚደረገው ጥንቃቄ እና ህክምናም ተግባራዊነት ላይ መዋል አለበት። ተጫዋቹ ከደረሰበት የጭንቅላት ግጭት በሚያገግምበት ወቅት የሚሰራቸውን እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ በማስኬድ ሰውነቱ በሚፈቅደው የጊዜ ሠሌዳ መሰረት ወደ ሜዳ መመለስ ይኖርበታል።

error: