በድምፅ ብልጫ ከአሰልጣኙ ጋር ላለመቀጠል የወሰነው ፌዴሬሽን ዳግም በድምፅ ብልጫ የአሰልጣኝ ቅጥር ይፈፀም ይሆን?

በ2022 በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚደረጉበትን ጊዜ ካፍ ድንገት ማሳወቁን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ስለ ቀጣይ አሰልጣኝ ቅጥር ምን እያሰበ ነው?

በኮቪድ-19 ምክንያት የተራዘመው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ከስምንት ሳምንት በኃላ ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 8 ቀን 2013 ባሉት ቀናት ኢትዮጵያ የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዋን በሜዳዋ እና ከሜዳዋ ውጭ ከኒጀር ጋር እንድታደርግ መርሐግብር በቅርቡ መውጣቱ ይታወሳል። አስቀድሞ ቴክኒካል ለሆነ ጉዳይ ቴክኒክ ኮሚቴ መወሰን ይገባል በማለት የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው አቋም ይዘው በአፅንዖት ቢናገሩም የአሰልጣኙ ጉዳይ አስተዳደራዊ ውሳኔ ነው የሚያስፈልገው በማለት በድምፅ ብልጫ የአብርሀም መብራቱን ውል ያልተራዘመበት ሁኔታ መፈጠሩ ይታወቃል።

ፌዴሬሽኑ ይህ እጅግ ለእግርኳሱ የራቀ ውሳኔ በወሰነበት በአስራ አምስተኛው ቀን ካፍ የውድድር ፕሮግራም መላኩ የፌዴሬሽኑን ግብታዊነት እና የችኮላ ውሳኔን አመላካች ሆኗል። የማጣርያው ጨዋታ ሊካሄድ የአስር ሳምንት (የሁለት ወር) ዕድሜ በቀረው በዚህ ሰዓት ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ለቴክኒክ ኮሚቴው የቀረበ ምንም አይነት ነገር እንደሌለ ሰምተናል። አሁን ተጠባቂ የሚሆነው ጉዳይ የአሰልጣኙን ማንነት እና ሹመት በሥራ አስፈፃሚው በኩል በድምፅ ብልጫ ይወስናል ወይስ በአካሄዱ መሠረት ቴክኒክ ኮሚቴው በሚያቀርበው ምክረ ሀሳብ መሠረት የአሰልጣኙን ቅጥር ይፈፅማል የሚለው ጉዳይ በጣም አጓጊ ሆኗል።

ከቴክኒክ ኮሚቴ አባላት እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ እስካሁን ከፅህፈት ቤቱ የተመራ ጉዳይ ባይኖርም አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ውላቸውን አራዝመው ብሔራዊ ቡድኑን በማሰልጠን እንዲቀጥሉ ሙሉ ፍላጎት እንዳላቸው ለማወቅ ችለናል።

ፌዴሬሽኑም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎችን ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል የሚለውም ጉዳይ የሚጠበቅ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!