የደጋፊዎች ገፅ | ቆይታ ከሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳዊት ጡምዳዶ ጋር

በፕሪምየር ሊጉ ብቅ ካሉበት ጊዜ ጀምሮ ስማቸው በአዎንታዊም በአሉታዊም መንገድ ከሚነሱ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ጡምዳዶ በደጋፊዎች ገፅ ይናገራል።
አቶ ዳዊት ጡምዳዶ ከ2006-07 ድረስ የሀዲያ ሆሳዕና ክለብ ፕሬዝዳንት በመሆን ለሁለት ዓመታት ሠርቷል። በዚህም ኃላፊነት ክለቡ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ አመራር በመስጠት የድርሻውን ተወጥቷል። በከተማ አስተዳደር ማስተርስ ድግሪ ያለው ዳዊት የከተማው አስተዳደር የመዘጋጃ ቤት መምርያ ኃላፊ በመሆንም በከፍተኛ ሹመት ሲራ ቆይቷል። ለእግርኳስ ካለው ከፍተኛ ፍቅር በተነሳም ከሁለት ዓመት በፊት የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆን ዳግም ባለው ሙያ እና ልምድ ክለቡን እያገለገለ ይገኛል። የዛሬ የደጋፊዎች ገፅ እንግዳ የሆነው ዳዊት ጡምዳዶ በክለቡ የደጋፊዎች እንቅስቃሴ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ላነሳንለት ጥያቄዎች ተከታዮቹን ምላሾች ሰጥቶናል። መልካም ቆይታ !

የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊነት አጀማመርህ እንዴት ነበር ?

ከልጅነቴ ጀምሮ ነው ሀዲያን መደገፍ የጀመርኩት። ሀዲያ ሆሳዕና ሳይባል በቀድሞ አጠራሩ ሆሳዕና ከተማ እየተባለ መጠራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው ጨዋታዎችን መመልከት የጀመርኩት። ለቀለም ትምህርቴ ትኩረት ስለሰጠሁኝ እንጂ በእግርኳሱም ተጫውቼ አልፌያለሁ። ሀዲያ ሆሳዕና ድሬደዋ ላይ በ2007 ወደ ፕሪሚየር ሊግ ከገባ በኃላ ነው ስያሜውን የቀየረው። በነገራችን ላይ የደጋፊ ማህበሩ ፕሬዝዳንት ሳልሆን በፊት ክለቡ በከተማው ሥራ አስኪያጅ ሥር በሚተዳደርበት ጊዜ ለሁለት ዓመት በትልቅ ኃላፊነት የክለቡ ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግያለው።



ይህ ብዙ ያልተለመደ ነው ፤ቀደም ሲል በክለቡ አመራር ሰጪነት የኃላፊነት ቦታ ውስጥ እንዴት ልትገባ ቻልክ ?

ከ2006-7 ድረስ የክለቡ በፕሬዝዳንት ነበርኩ፡፡ ይህ የሆነው ቀድሞ ሆሳዕና ከተማ ተብሎ ይጠራ ስለነበር የከተማው አስተዳደር ክለቡን ይመራው ስለነበር ነው። እኔ በአዲስ አባባ ሲቪል ሰርቪስ በማኔጅመት ማስተርስ ዲግሬዬን ጨርሼ በሆሳዕና ከተማ በተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ በኃላፊነት ህዝቤን አገልግዬ ለተሻለ ኃላፊነት ደግሞ የከተማው ሥራ አስኪያጅ ስለነበርኩ ክለቡን በበላይ ጠባቂነት በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ዕድሉን አግኝቻለው። በጊዜውም ክለቡ ይፈልገው ወደነበረው የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊነት ጉዞ ውስጥ አመራር በመስጠት ድርሻዬን ስወጣ ቆይቻለው።

ወደ ደጋፊ ማህበሩ ልመልስህና አደረጃጀቱ ምን እንደሚመስል ግለፅልኝ፡፡

በመጀመርያ እንደማንኛውም ማህበር ጠቅላላ ጉባዔ አለው። የራሱ መተዳደርያ ህገ-ደንብም አለው። ማህበሩ ከተቋቋመ ትንሽ የቆየ ቢሆንም በጣም በተጠናከረ ሁኔታ መንቀሳቀስ የጀመረው ከ2011 ጀምሮ ነው። የማህበሩ አጠቃላይ አባላት በሚገኙበት በሚካሄድ ምርጫ አስራ አንድ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ይመረጣሉ። በሥራ አስፈፃሚው አወቃቀር ውስጥ የተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ክፍፍል አለ
፡፡ ፕሬዝዳንት ፣ ም/ፕሬዝዳንት ፣ ፀኃፊ እና ኦዲተር አለው። ቀሪዎቹ ውስጥ ደግሞ የተለያ ንዑሳን ኮሚቴዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ህዝብ ግኑኝነት ፣ ገቢ አሰባሳቢ ፣ ፀጥታ እና ደንብ አስከባሪ እንዲሁም የደጋፊዎች ዲሲፒሊን ኮሚቴ የሚባሉ አሉን። በዚህ መልኩ ነው የደጋፊ ማህበር አወቃቀራችን።

ደጋፊው ከመደገፍ ባለፈ በክለቡ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ውስጥ ያለው ድርሻ እስከ ምን ድረስ ነው?

ደጋፊ ማህበሩ በክለቡ ውስጥ የቦርድ አባል ነው። በእያንዳንዱ የክለቡ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ አለው። እንዲሁም በውሳኔ አሰጣጥ ላይም አንድ ድምፅ አለው። ለምሳሌ የ2012 የክለቡ አፈፃፀም ግምገማ ላይ ፣ የቀጣይ ዓመት ዕቅድ አወጣጥ ላይ እና በተጫዋቾች ግዢ ውስጥ ደጋፊ ማህበሩ ድርሻ ነበረው። እንግዲህ ከደጋፊነት ባለፈ በክለቡ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የምንጫወተው እኛ ነን ማለት ይቻላል።

በሀዲያ ደጋፊነትህ ለአንተ የተለየ የምትለው ቀን መቼ ነው ?

ሀዲያ ሁሌም ሜዳ ካለ እንዲሁም በጨዋታው ካሸነፈ ለኔ የተለየ ቀን ነው። የሚገርም ስሜት ነው የሚሰማኝ። ሆኖም ግን በጣም የተለየ ቀን ካልከኝ 2011 ላይ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ልንገባ ከሺንሺቾ ከተ0ማ ጋር የነበረው ጨዋታ የተለየ ነበር። ምክንያቱም አንደኛ ጨዋታው ደርቢ ነው። ሺንሺቾ ለከተማችን ቅርብ ነው። ሁለተኛ ይህን ጨዋታ ካሸነፍን ወደ ሊጉ የምንገባበት የነበረ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። ስታድየሙ ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልቶ ጠጠር መጣያ እንኳን አልነበረም። የቀረው ደጋፊም በየፎቆቹ ቆሞ ነበር። እኔ በህይወቴ ታሪክ እንዲህ ያለ በርካታ ደጋፊ አይቼ አላውቅም ፣ የተለያዩ ከከተማው ዙርያ የሚገኙ ደጋፊዎች መጥተው የታደሙበት ነበር። የክለቡ አመራሮች ‘ምን ይፈጠር ይሆን ?’ ብለን ተጨንቀን ነበር፡፡ ሆኖም ምንም ነገር ሳይፈጠር ጨዋታው በሠላም ያለቀበት ቀን ነበር፡፡ ለኔ ያ ቀን የተለየ ነበር።

ክለባችሁ በመንግሥት ድጎማ ነው የሚተዳደረው ፤ ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ምን እየሰራችሁ ነው ?

በመጀመርያ የአባሉን ቁጥር ማብዛት እና መታወቂያ ወስዶ እንዲመዘገብ በማድረግ ከመለያ እና ከስካርፕ ሽያጭ የደጋፊ ማህበሩን ለማጠናከር እየሰራን ነው። ለደጋፊ ማህበሩ የራሱ የሆነ ቢሮ ከፍተን አንድ ሠራተኛ ቀጥረን ህጋዊ መሠረት እንዲይዝ እየሰራን ነው ፤ ኮሮና መጥቶ ትንሽ እንቅስቃሴያችንን ገደበው እንጂ። በተለያዩ ወረዳዎች እና ዞኖች እንዲሁም በአዲስበአበባ ፣ በድሬደዋ እና ሌሎች ከተማዎች ላይ የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎችን የማብዛት ፣ ፅህፈት ቤት በመክፈት ወደ ገንዘብ የመቀየርም ሥራዎች እየሠራን እንገኛለን። ክለቡን በተመለከተ ከመንግስት ድጎማ ወጥቶ ህዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ቦርዱ ብዙ ሥራዎች እየሰራ ነው። የተለያዩ ዕቅዶችን በማውጣት እየተንቀሳቀሰ ነው። እንዲሁም ክለቡን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርገውን የተጫዋቾች ግዢን ለማስቀረት እንዲረዳ የተሻለ የትምህርት ደረጃ ባላቸው ሦሰት የቴክኒክ ዳይሬክተሮች እንዲደራጅ ሆኗል። የታዳጊ ተስፋ ቡድንም አቋቁመናል። ከመንግስት በጀት ወጥቶ በባለሙያ የተሟላ እንዲሆን ፣ ባለሀብቶች ክለቡን እንዲረከቡ እየተነጋገርንም ነው። በከተማዋ ከሚገኙ ከተለያዩ ተቋማት ለምሳሌ የሆሳዕና ንግድ ባንክ እና ሌሎች ድርጅቶች ጋር ፕሮፖዛል አዘጋጅተን እየተንቀሳቀስን ነው።

ሀዲያ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት ክለብ ነው። ሆኖም ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ ብዙ ጊዜ የተለያዩ ችግሮች እየተፈጠሩ ክለቡን ለቅጣት ሲዳርጉት ይታያል፡፡ ይህን ለማስቀረት ምን እየሰራችሁ ነው? የችግሩስ መንስዔ ምንድን ነው ?

እኛ ጋር ሁለት ዓይነት ደጋፊ ነው ያለው። አንደኛው በማህበር ታቅፎ መዋጮ እየከፈለ የደጋፊ ማህበሩን ህገ-ደንብ አክብሮ የሚንቀሳቀስ አለ። ሌላው ኳስ ሲኖር ፣ ውጤት ሲመጣ ብቻ መጥቶ የሚያይ ፣ ውጤት ሲጠፋ ቅሬታ የሚያሰማ ‘ተመልካች’ የሚባል አለ። ይህ ማለት የተቀላቀለ ነገር አለ ማለት ነው። በነገራችን ላይ በዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ የስፖርታዊ ጨዋነት ሥልጠናዎችን ሠጥተናል። እግርኳስ የዓለም ቋንቋ ነው። ደጋፊው ከስሜት ወጥቶ ክለቡን ብቻ እንዲደግፍ ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ተመልካቹን ወደ ደጋፊነት አምጥቶ የአባልነት መታወቂያ አውጥቶ በደንብ እና በህግ እንዲመራ ለማድረግ እየሰራን ነው። በሌላ መልኩ በክለቡ አመራሮች በኩል መስተካከል ያለባቸው ነገሮችም አሉ፡፡ አንደኛ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የመጣ ተጫዋች የሚጠበቀውን ሆኖ ሳይገኝ ሲቀር ደጋፊው ያዝናል እንዲሁም ተጫዋቾች ከአቅም በታች ሲጫወቱ እና ክለቡን የሚመጥን ተጫዋች ሳይመጣ ሲቀር ደጋፊው ቅሬታ የሚያቀርብበት ሁኔታ ይፈጠራል። በተጨማሪም ክለቡ በተጫዋቾች ግዢ ብቻ በመጠመድ ከታች ታዳጊ አለማውጣቱ ደጋፊውን ወደ ተቃውሞ የሚገፋፋ ሌላው ጉዳይ ነው። ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መስራት አለብን።

ሀዲያ በየዓመቱ ብዛት ያላቸው ተጫዋችን በማስፈረም ቡድን የመገንባት እና የማፍረስ አዝማሚያ ይታይበታል። ይህን አስቀርቶ ከታች ለማሳደግ እንደሌሎቹ ክለቦች የታዳጊ ቡድን እንዲኖረው ምን እየተሰራ ነው?

ቅድም ገልጬልሀለው። በ2012 የ ‘B’ ቡድን አደራጅተን ወደ ሥራ ገብተናል ፤ ይሄ ትልቅ ጅምር ነው። በዚህ ብቻ አንቆምም ፤ ከ13 ዓመት በታች ጀምሮ በተለያዩ የዕድሜ ዕርከኖች በቀጣይ ተገቢው ስራ እንዲሰራ በቦርዱ አቅጣጫ ተቀምጧል። የሚመጡት የክለቡ አሰልጣኝ አባላት እና ቴክኒክ ኮሚቴዎች ይሄን እንዲሰሩ ይደረጋል። በቀጣይ ማክሰኞ በሚኖረው የቦርድ ስብሰባ ላይ ዋና አጀንዳ ሆኖ በታዳጊዎች ሥልጠና ዙርያ ውይይት ይደረጋል። በተጫዋቾች ግዢ ብቻ ክለቡ ማተኮር የለበትም፡፡ ህዝባዊ ክለብ እንዲሆን ከመንግሥት ድጎማ እንዲላቀቅ ከታች ጀምሮ መስራት ወሳኝ ነገር ነው።

የብዙዎች ጥያቄ ስለሆነ ነው ይሄን የማነሳው፡፡ ዘንድሮ ሀዲያ አዲስ አሰልጣኝ ከቀጠረ በኋላ ባልተለመደ ሁኔታ አስር ተጫዋቾችን ከአንድ ክለብ አምጥቷል። አንተ በቦርድ ውስጥ እንደለህ ድምፅ ይሄን እንዴት ነው የምታዩት ? ትክክል ነው ብላችሁስ ታመናለችሁ ?

የመጀመርያ ዕቅዳችን ይህን ክለብ ማሻገር የሚችል ጠንካራ አሰልጣኝ መቅጠር ነው ፤ እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጥነው። ‘ታዳጊ ማፍራት ፣ ወጣቶች ላይ በመስራት ልምድ ያለው ፣ ጥሩ ቡድን መገንባት የሚችለው ማነው ?’ ብሎ ቴክኒክ ኮሚቴው ስድስት አሰልጣኞችን አወዳድሮ አሰልጣኝ አሸናፊን በቀለን ቀጥሯል። አሰልጣኝ አሸናፊ ከክለቡ ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመነጋገር ክለቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራሉ ብሎ ያመነባቸውን ተጫዋቾች እንዲመጡ ቦርዱ ባዘዘው መሠረት አጋጣሚ ከአሰልጣኙ ፍልስፍና ጋር የሚሄዱ አዳማ ውስጥ ውል የጨረሱ አስር ተጫዋቾችን አምጥቷል። አሰልጣኙ ካመነበት ድርሻው የእርሱ ነው። አዳማን ለማፍረስ ማንም አይፈልግም። ክለቡን የሚመጥኑ ተጫዋቾች ሲፈልጉ ለእርሱ ፍልስፍና ስለሚሆኑ እና ጠንቅቆ ስለሚያቃቸው እነሱን መርጧል። የተጫዋቾቹም ፍላጎት ተጨምሮበት በአዳማ ውላቸውን ማጠናቀቃቸውን አጣርተን ቴክኒክ ኮሚቴው ተቀብሎት የመጡ ተጫዋቾች ናቸው። ስለዚህ ክለቡም አምኖበት የተቀበለው የአሰልጣኙ ሥራ ነው። ደጋፊ ማህበሩም አምኖበት የገባበት ጉደይ ነው።

እግርኳሱ መልኩን ቀይሮ የተለያዩ አላስፈላጊ ነገሮች በየስታድየሞቹ እየተንፀባረቁ ነው። አንተ አንደ አንድ ደጋፊ ማኅበር ይህ ለእግርኳሱ ስጋት የሆነውን ነገር እንዴት ታየዋለህ ?

ለክለቦቻችን ደጋፊዎች ሥልጠና ስንሰጥ መጀመርያ ስፖርት ሳይንስ መሆኑን ከዘር፣ ከኃይማኖት ፣ ከፖለቲካ ፣ ከቀለም እና ከብሔር ውጪ መሆኑን አስረደተናቸዋል። ስፖርት መዝናኛ ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ትስስር መፍጠርያ እንዲሁም ወዳጅነት እና ባህልን ማስተዋወቂያ መድረክ ነው ። ይህን በተደጋጋሚ በሰጠናቸው ሥልጠናዎች ደጋፊዎቻችንን አስገንዝበናል። ደጋፊያችንም እግርኳሱ ውስጥ እንዲህ ያሉ አላስፈላጊ ነገሮችን አይቀበልም። ለስም እንዲጠቅም ሀዲያ ብለን እንጥራ እንጂ ዋናው የክለቡ ዓላማ ለኢትዮጵያ እግርኳስ የሚጠቅም ትውልድ ማፍራት ነው። በክለቡ የበላይ ጠባቂ በነበርኩበት ጊዜ እና በከተማው አስተዳደር በነበረኝ ኃለፊነትም እግርኳሱ ጤናማ አየር እንዲኖረው እየሰራው ቆይቻለው። አሁንም እግርኳሱ ከማንኛውም ነገር ነፃ እንዲሆን እየሰራን እንገኛለን። ከዚህ ቀደም ከወራቤ እና ከወልቂጤ በደጋፊዎቻችን ላይ ለተፈጠረው ችግር ክለቦቹ ይቅርታ ሲያቀርቡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ነው የተቀበልነው። ምክንያቱም እግርኳሱን ከዘር እና ኃይማኖት ነፃ ለማድረግ ስለምንፈልግ ነው። እግርኳስ አንዱን ከአንዱ ፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያቀራር እንጂ የአንድ ከተማ ወይም የዘር ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ ሁላችንም ለኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት ልንጨነቅ ይገባል፡፡ በትንሽ ነገር ተቧድነን እግርኳሱን እንዳንጎዳ አደራ እላለው።

ሀዲያ ሜዳ መጥተው የሚጫወቱ ቡድኖች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በመጫወቻ ሜዳው ላይ በተደጋጋሚ ቅሬታ ያሰማሉ። ሜዳውን ለማስተካከል ምን እየተሰራ ነው ?

እውነት ነው፡፡ የሜዳ ችግር አለ፣ ይህ ችግር ደግሞ እንኳን ሀዲያን ለመግጠም የመጡ ቡድኖችን አይደለም ለእኛም አመቺ ያልነበረ ብዙ ውጤት ያሳጣን የተቸገርንበት ሜዳ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ በኮሮና ውድድር ሲቋረጥ ቦርዱ መጀመርያ ሊሰራው ያሰበው የሜዳውን ጉዳይ ነው። የባህል እና ቱሪዝም ፣ ደጋፊዎች እና የግብርና ባለሙያዎች ያሉበት ኮሚቴ አዘጋጅተን የሜዳው ሳር ተነቅሎ አዲስ ሌላ ሳር እንዲከል አድረገናል። እንዲሁም ችግር አለባቸው የተባሉ ቦታዎችን ለምሳሌ አጥር እና ሌሎችን ስራዎች እያስተካከልን ነው። በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሜዳዎች የተሻለ ሜዳ ሠርተናል ፤ መጥታችሁ ማየት ትችላላችሁ። ሜዳውን ማስተካከል ጥቅሙ ለኛ ነው። ምክንያቱም በሜዳችን ነጥብ የምንጥለው አንዱ በሜዳ ችግር በመሆኑ ነው።

🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!