ሶከር መጻሕፍት | ተከላካዮች እና የመከላከል እግርኳስ በጣልያን   

በዛሬው የሶከር መጻሕፍት መሰናዶአችን እ.ኤ.አ. በ2006 ለህትመት የበቃውን የጆን ፉት <ካልቺዮ> የተሰኘ መጽሃፍ ይዘን ቀርበናል፡፡ ካልቺዮ በጣልያን እግርኳስ ታሪክ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ለአንባቢዎቿ ይመጥናሉ ያለቻቸውን ምዕራፎች መራርጣ በትርጉም መልክ ለማቅረብ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡ ይህኛ ክፍል የመጀመሪያ ሲሆን ከመፅሐፉ ምዕራፍ አምስት ላይ የተቀነጨበ ነው – መልካም ንባብ!

በትምህርት ቤት ቆይታዬ አቶ ካምቤል የተባለ የስፖርት መምህር ነበረኝ፡፡ ሰውየው ትጉህ፣ ጉጉ እና ባተሌ አስተማሪ ነበር፡፡ ገና በዘጠኝ ዓመት ዕድሜዬ በግቡ የምሰሶ ቋሚዎች መካከል እንድቆም በመወሰኑን መቼም ይቅር ልለው የማልችለው ከመሆኑ በተጨማሪ ካምቤል በዘመናዊ የእግርኳስ ታክቲክ ልሂቅ የሚባል አሰልጣኝ አልነበረም፡፡ በልምምድ ወቅት አዘወትሮ የሚነግረን ዋነኛ መልዕክቱ የሚከተለውን አባባል በአዕምሯችን እንድናመላልስ ነበር፡፡ ” ኳስ መያዝህ ምቾት ካልሰጠህ አርቀህ ምታው!” እንግዲህ ይህ የካምቤል አስተምህሮ ተከላካይ ክፍላችን ለብዙ ጊዜ የሚመራበት መርህ ሆኖ ቆየ፡፡ ኳሱን መጠለዝ-ኳሱን ማራቅ! በሚቻለው ከፍታ እና ርቀት ከራስ የግብ ክልል ኳሱን ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በፍጥነት መላክ ተልዕኳችን ሆነ፡፡ በተቻለን አቅም ኳሱን ከግብ ክልላችን ውጪ ካደረግን ሌላ ብዙም አይጠበቅብንም – የሚፈለግብንን ከወንን ማለት ነው፡፡ አሁን-አሁን ከ1950ዎቹ ጀምሮ የጣልያን ቡድኖች በመከላከል አጨዋወታቸው የተነሳ የሰላ ትችት ሲቀርብባቸውና ውግዘቱ ሲያይልባቸው እገረማለሁ፤ የወቀሳው መነሻ ወይም የክሱ አስረጅ ትርክቶች ሐሰተኛ አመክንዮ የያዙ መሆናቸውን እረዳለሁና፡፡ ሲጀመር የጣልያን ቡድኖች እግርኳሳቸውን በመከላከል አጨዋወት ላይ ጥገኛ አላደረጉም፡፡ ይልቁንም ጣልያኖች ከሌሎች የአውሮፓ ቡድኖች አንጻር ከጨዋታ ሒደቶች መካከል አንዱ በሆነው የመከላከል ሥልት የተሻለ ብቃት አሳይተዋል፡፡ ብዙዎቻችን ሒደቱን የተረዳንበት መንገድ ለሥህተት ዳርጎናል፡፡

የጣልያን ተከላካዮች ኳስ መጫወት ይችላሉ፡፡ ኳስ እግራቸው ሥር ማቆየት አይፈሩም፤ ኳሷን እግራቸው ሥር አድርገው ወደፊት መሮጥንም ተክነውታል፤ የቅብብል ልኬታቸውና ልከኝነታቸውም ከፍ ያለ ነው፤ የቅብብሎችን መዳረሻ ቀድመው በመገመትና በማወቅ ረገድ ብቁዎች ስለሆኑም ጥሩ ውሳኔ ለመወሰን አይቸገሩም፡፡ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ደህንነት እርግጠኛ ስላልሆኑ ብቻ ኳሱን ስለማራቅ አያስቡም፤ ያን ለማድረግም አይቸኩሉም፡፡ እንደ ሌሎቹ ሀገራት ተከላካዮች ኳሱን ማራቅ የመጨረሻ እንጂ የመጀመሪያ ምርጫቸው አይደለም፡፡ ለዕይታ በማይስብ መልኩ ኳሱን ወደ ተጋጣሚ ክልል መጠለዝ አልያም ኳስን እግር ሥር ላለማቆየት ሲባል ያለ አላማ ወደፊት መምታት በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ የተቃውሞ ጩኸት ያስከትላል፡፡ ወደ ሰማይ የሚጎኑ ቅብብሎችን “ማማዎች ላይ የሚገኙ ደወሎችን ለማስነሳት የሚደረጉ ቅብብሎች” ወይም በራሳቸው ቋንቋ “ካምፓኒሊ” ብለው የፌዝ መጠሪያ አውጥተውላቸዋል፡፡ በጣልያን ያሉ ተከላካዮች በሌሎች ሃገራት ከሚገኙት አንጻር ጥሩ የታክቲክ ግንዛቤና አረዳድ እንዲሁም ፍጥነት አላቸው፡፡ ስለ ዕውነት ለመናገር በጣልያን ዝቅተኛ ሊጎች የሚጫወቱ የመሐል ተከላካዮች በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የመሰለፍ ዕድል የሚያገኙ ናቸው፡፡ ከተጠቀሱት የተከላካዮቹ አይነተኛ ብቃት በተጨማሪ ጣልያናውያን ግብ ጠባቂዎች የላቀ ቴክኒካዊ ክህሎት አላቸው፡፡ በ1990ዎቹ የጣልያን እግርኳስ በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያልነበራቸውን በርካታ ግብ ጠባቂዎች ማፍራት መቻሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች በዚያ ዘመን በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ይጫወቱ ቢባል እንኳ ከመጀመሪያ ተሰላፊነት ያነሰ ቦታ አይሰጣቸውም፡፡

የጣልያን ቡድኖች ለኳስ ቁጥጥር ዋጋ ይሰጣሉ፤ ከኋላ መሥርተው ለመጫወትም አያቅማሙም፡፡ በጨዋታው የበላይነታቸውን ካረጋገጡ ተጠንቅቀውና ኳሱን ተቆጣጥረው ይጫወታሉ፡፡ ግብ የማስቆጠር ግዴታ ውስጥ ሲወድቁ ደግሞ በከፍተኛ ፍጥነት እና ስልነት ወደ ተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል በተደጋጋሚ ይከንፋሉ፡፡ በቴክኒካዊ ሥልጠና እጅጉን በዘመነው የሀገሪቱ ታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት ሰልጣኝ-ግብ ጠባቂዎች በዘፈቀደ ኳስ እንዳይጠልዙ በአሰልጣኞቻቸው ጥብቅ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል፡፡ ኳስን ዝም ብሎ መምታት ወይም በረጅሙ ማራቅ ክልክል ነው፡፡ ጨዋታውን ከኋላ ለማስጀመር ግብ ጠባቂዎች በቅርባቸው ለሚገኝ ተጫዋች በእጃቸው መወርወር አልያም በእግራቸው በአጭሩ ማቀበል ይጠበቅባቸዋል፡፡

የኳስ ቁጥጥር ላይ ያመዘነ አቀራረብ የግድ ለመከላከል አጨዋወት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ታላላቆቹ የብራዚል ቡድኖች በተጋጣሚዎቻቸው ላይ ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ይወስዱ ነበር፡፡ ግብ ለማስቆጠር የሚረዳው ፈጣኑ መንገድ ምናልባት ወደ ተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል የሚደረስበት የረጅም ኳስ ቅብብል ዘዴ ላይሆን ይችላል፡፡ የጣልያን ቡድኖች የረጅም ኳስ አጨዋወት ሥልትን ይተገብራሉ፤ ለዚህም ወደ መስመሮች የሚደረጉ ቅብብሎችን ያዘወትራሉ፤ አልፎ አልፎም በሜዳው ቁመት በመሐለኛው ክፍል ቅብብሎችን ይከውናሉ፡፡ በጣልያን ኳስን ሳይቆጣጠሩ እጅግ ፈጣንና በሁለት-ሦስት ምቶች የተጋጣሚ የግብ ክልል ጋር ለመድረስ የሚደረግ አጨዋወት እንደ ዋነኛ የማጥቃት ሥልት አይታይም፡፡ በቀደሙት ዘመናት ጣልያኖች በጨዋታ ወቅት አነስተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ሒደቱን በቁጥር በርከት ባሉ ተጫዋቾች ስለሚመሩ እጅግ ፍሬያማ ሆነዋል፡፡ በእግርኳስ ከተቀያያሪ፣ ስኬታማና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ዘይቤ በላይ ማራኪ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ በማጥቃት አጨዋወቱ ትልቅ ከበሬታን ያተረፈው የ1990ዎቹ የአርሰን ቬንገር አርሰናል የመልሶ-ማጥቃት ተግባሪ ቡድን ነበር፡፡ የክለቡ ተጫዋቾቹ በተጋጣሚዎቻቸው አማካኝነት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በመጠቀም ረገድ ስል ነበሩ፡፡

የመከላከል አጨዋወት በቴክኒካዊ ክህሎት ወይም በታክቲክ ልህቀት ላይ ብቻ የሚመሰረት ሒደት አይደለም፤ ለጨዋታ በምንሰጠው ክብደት አልያም ግምት ብቻም አይለካም፡፡ ከዚያ በዘለለ መከላከል እግርኳስን በጥልቀት የምንረዳበት መንገድም ነው፡፡ እግርኳስ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተመልካቾች- ማራኪ የአጨዋወት ሥልትን የሚያስቀድሙ እና በማንኛውም ዘይቤ ማሸነፍን የሚመርጡ ተብለው በሁለት ጎራ ሲፈረጁ ኖረዋል፡፡ ዝነኛው ጋዜጠኛ ጂያኒ ብሬራ 0-0 የሚጠናቀቅ ጨዋታ በሁሉም መስፈርቶች ረገድ ወደ ምሉዕነት የተጠጋ እንደሆነ ብዙውን ጊዜ ይናገራል፡፡ ይህ አይነቱ የእግርኳስ አረዳድ ከብዙኃን የሙያ ባልደረቦቹ ምልከታ አንጻር እጅጉን በተራራቁ ጽንፎች እንዲቀመጥ ያደርገዋል፡፡ በእንግሊዝ ሊግ ለተጫወቱ አልያም የሃገሪቱን እግርኳስ በሚከታተሉ ወገኖች ዘንድ ደግሞ ከፍተኛ ውግዘት ያስከትላል፡፡ በእንግሊዝ ማንም ሰው ምሉዕ የሆነ ጨዋታ 0-0 ይጠናቀቃል ብሎ ሊሟገት አይችልም፡፡ በዓለም እግርኳስ ታሪክ ከዋነኞቹ የመከላከል ታክቲካዊ ዘዴዎች አንደኛው በ1940ዎቹ ከሌሎች ቀድሞ በጣልያን ምድር ተተገበረ፤ ከዚያ ሥያሜውንም ከሃገሪቱ ቋንቋ አገኘ፡፡ እናም ብዙዎች ጣልያንን መከላከል ላይ ባመዘነ የእግርኳስ አጨዋወት እየቃኙ ኖሩ፡፡ የጂያኒ ብሬራ ክርክር ከእሳቤው ታሪካዊ ዳራ አንጻር ሲታይ ላያስገርም ይችል ይሆናል፡፡

ይቀጥላል…

የመጽሃፉ ደራሲ ጆን ማኪንቶሽ ፉት ይባላል፡፡ እንግሊዊው ጸሃፊ የጣልያንን ጓዳ-ጎድጓዳ አብጠርጥረው ከሚያውቁ የውጭ ምሁራን መካከል ይጠቀሳል፡፡ በበርካታ የጣልያን እና እንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎችም የጣልያንን ታሪክ አስተምሯል፡፡ በሃገሪቱ ፖለቲካ፣ ፍልስፍና እና ምጣኔ ኃብት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የታሪክ መጻሕፍትም አበርክቷል፡፡ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎችም ጥልቀት ያላቸው ጥናቶቹን ያቀርባል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ