ሶከር መጻሕፍት | የመሐል ሜዳ መሪዎች

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በሶከር መጻሕፍት መሰናዷችን እ.ኤ.አ. በ2006 ለህትመት የበቃው የጆን ፉት <ካልቺዮ> የተሰኘ መጽሐፍን እያቀረብን እንገኛለን። በጣልያን እግርኳስ ታሪክ ላይ ካተኮረው ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሶከር ኢትዮጵያ ለአንባቢዎቿ ይመጥናሉ ያለቻቸውን ምዕራፎች መራርጣ በትርጉም መልክ ማቅረቧን ቀጥላለች። የዛሬው ፅሁፍም ከመፅሐፉ ምዕራፍ ስድስት ላይ የተቀነጨበ ነው – መልካም ንባብ!

ጣልያኖች በእግርኳስ ጨዋታ የሜዳውን መሐል ክፍል በቁጥጥሩ ሥር የሚያደርገውን ተጫዋች “ሬጂስታ” ይሉታል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በጣልያን ሁሉም ቡድኖች መሐል ክፍላቸውን በአግባቡ በሚያደራጅ ተጫዋች ማዋቀር ጀመሩ፡፡ ይህ አማካይ ለፊት መስመር ተሰላፊዎች እና የመስመር አማካዮች ቅብብሎችን የሚያሰራጭ ባለ ክህሎት መሆን ይኖርበታል፡፡ ያም ሆኖ ሬጂስታ ብዙ እንዲሮጥና ኳስ እንዲያስጥል አይጠበቅበትም፡፡ በ1980ዎቹ የዚህ ተጫዋች ቀደምትና ወጥ ሚናው እየከሰመ፥ ተፈላጊነቱም እየወረደ መጣ፡፡ በጨዋታ ወቅት ሜዳ ላይ የሚሰለፉ ሁሉም ተጫዋቾች ወደኋላ እያፈገፈጉ ከተጋጣሚዎቻቸው እግር ሥር ኳስ የመንጠቅና ተጭነው የመጫወት ግዴታ ተጣለባቸው፡፡ ስለዚህም አንጻራዊ በሆነ ውስን የመንቀሳቀሻ ክልል የሚጫወቱት የመሃል ሜዳ አማካዮች ቀስበቀስ ደብዛቸው ይጠፋ ጀመር፡፡ ቡድኖች መሐል ክፍላቸው ላይ ባለ ተሰጥዖዎቹን አማካዮች ማካተታቸውን ቢቀጥሉም የተጫዋቾቹ እንቅስቃሴያዊ አቋቋም የሚዋልል ከመሆኑ በተጨማሪ የጨዋታው አጠቃላይ ሒደት በአንድ ተጫዋች አማካኝነት ብቻ መወሰኑ ቀረ፡፡ የዘመናዊው እግርኳስ አጨዋወት ጥድፈት መጨመርም ባለ ክህሎቶቹ አማካዮች እንደፈለጉ ጨዋታ የሚቆጣጠሩበትን ቦታ ነፈጋቸው፡፡ በጨዋታ ወቅት የመሐል ሜዳ ክፍሉን እንዳሻቸው የሚመሩት ተጫዋቾች ወርቃማ ዘመናቸው 1950ዎቹና 1960ዎቹ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላም በሀገሪቱ  እግርኳስ ታላላቅ “ሬጂስታ” አማካዮች ታይተዋል፡፡ ከሮማ ጋር ድንቅ ጊዜያትን ያሳለፈው ብራዚላዊው ሮቤርቶ ፋልካዎ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡

ጣልያን የእነዚህ ተጫዋቾች መፍለቂያ ሃገር ናት፡፡ ብዙዎች በዚህ ሚና ስኬታማ መሆን ቢችሉም የጂያኒ ሪቬራን ያህል የመሃል ሜዳ መሪነትን የተካነበት ተጫዋች አልታየም፡፡ እርሱ የምንግዜውም ምርጡ የጨዋታ ተቆጣጣሪ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ሪቬራ በሴሪአው ከሃያ አንድ ዓመታት በላይ በላቀ የብቃት ከፍታ በመጫወት ለሊጉ ልዩ ድምቀት መሆን ችሏል፡፡ ከእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሃያውን የውድድር ዘመን በሚላን አሳልፏል፡፡ ሪቬራ የ”10-ቁጥር ተጫዋቾች” ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ፣ ለቡድኑ የጨዋታ የበላይነትን የሚያስገኝ፣ የሚላን አማካይ ክፍል መዘውር አና በመሐል ሜዳ ላይ በአጨዋወት ንግስናው የገነነ የክለቡ ውድ ልጅ ነበር፡፡ በ1998 በተዘጋጀ ዓለምአቀፍ ውይይት የሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጣልያን ምርጡ ተጫዋች በመባል ተሰይሟል፡፡ በ1970 እንግሊዛዊው አሰልጣኝ አልፍ ራምሴይ “የጣልያን አራቱን ታላላቅ ተጫዋቾች ጥቀስ!” ተብሎ ሲጠየቅ “ሪቬራ-ሪቬራ-ሪቬራ-ሪቬራ” ሲል ዘርዝሯል፡፡

ብዙዎቹ ጣልያናውያን አማካዮች የመሐል ሜዳውን መቆጣጠርና የማጥቃት ሒደቱን መምራት ይሆንላቸዋል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች ኳሱን ፍለጋ ሜዳ ሙሉ ሲባዝኑ አይታዩም፡፡ ሪቬራም እንዲሁ ነው፡፡ ግንቦት 28-1969 በተካሄደው የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ፍጻሜ ላይ ሚላኖች በጊዜው ወደ ዓለምዓቀፉ እግርኳስ የኃያልነት ማማ በመንደርደር ላይ የነበረውን የክራይፍ እና የኒክሰንስ አያክስ በማድሪዱ-ሳንቲያጎ ቤርናቢው መፋለም ነበረባቸው፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች እስሲቀሩ ድረስ ሚላኖች የሆላንዱን ክለብ 3-1 ይመሩ ነበር፡፡ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ጂያኒ ሪቬራ መሃል ሜዳ ላይ ኳስ ደረሰው፤ ኳሷን እግሩ ሥር አድርጎ ወደ አያክሶች የግብ ክልል አፈተለከ፤ በከፍተኛ ጥድፈት ኳሱን ሊንጥቅ ወደ እርሱ የሚንደረደረውን የአያክስ ግብ ጠባቂ በአስደናቂ ክህሎት አለፈው፤ ኳሷ ግን ወደ ግብ ክልሉ አላመራችም- ይልቁንም ከግቡ ቋሚ ርቃ ወደ ማዕዘን መምቻው አቅጣጫ ሄደች፡፡ ኳሷ መስመሩን አልፋ ለተጋጣሚ ቡድን የመልስ ምት እንዳትሆን ሪቬራ ሮጦ ደረሰባት፡፡ ጨዋታው ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ስለነበረ ሁሉም ተመልካች ሪቬራም ልክ እንደ ማራዶና፣ ፕላቲኒ፣ ዚዳን እና መሰሎቹ ታላላቅ አማካዮች ጀርባውን ለተከላካዮች ሰጥቶ የሚጫወት መሰላቸው፡፡ እርሱ ግን ያን አላደረገም፡፡ ይልቁንም ኳሷን እግሩ ሥር ይዞ ወደኋላ ተመለከተ፤ ማድረግ የሚገባውን አሰላሰለ፤ ግራ እግሩ ሥር የነበረችውን ኳስ ወደ ቀኝ እግሩ አዞራት፡፡ ወዲያው ከቆመበት አካባቢ ወደ ራቀው የግቡ ቋሚ ቃኘ፤ ጥቂት ሰከንዶች ቀደም ብሎ ቦታው ላይ ክፍተት መኖሩን አስተውሏል፡፡ ስለዚህም ኳሷን በተመጠነ ልኬት ወደ ክፍቱ ቦታ ሰደዳት፤ ኳሷም በራ ማንም የተጋጣሚ ተከላካይ ሳያየው ከኋላ ተስፈንጥሮ የመጣው የቡድን አጋሩ ግንባር ላይ አረፈች፡፡ ይህ ምናባዊ የሚመስል አዕምሯዊ መስተጋብር በእግርኳስ ታሪክ በተጫዋቾች መካከል አስደናቂ መናበብ የታየበት ቅጽበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ የሚላኑ የመሃል አጥቂ (9-ቁጥር ተጫዋች) ፕየሪኖ ፕራቲ ከኋላ-ሰላሳ አምስት ሜትር ያህል ከሚጠጋ ርቀት ወደፊት መሮጡን የጀመረው ከሰከንዶች በፊት ነበር፡፡ ይህን የሪቬራ እይታ በቃላት ማድነቅ እጅጉን ከባድ ነው፡፡ ፕራቲ ቦታው ላይ የሚደርስበትን ጊዜ አስልቶ ልከኛ ቅብብል መከወኑን ለምልዑነት ከቀረበ አዕምሯዊ ብቃት በላይ የትኛውም ገለጻ በቂው አይደለም፡፡ ምናልባት በ1970ው የአለም ዋንጫ ፍጻሜ ፔሌ ለካርሎስ አልቤርቶ ያቀበለው ኳስ ይስተካከለው ይሆናል፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሠራተኛው መደብ ቤተሰቦች የተወለደው ሪቬራ በሰፈር ቡድኖች ውስጥ እግርኳስን መጫወት ጀመረ፡፡ በጊዜው በሪቬራ ብቃት እጅጉን የተደመመው ታላቁ ሲልቪዮ ፒዮላ እንኳ ያለበት አካባቢ ድረስ በመምጣት ጨዋታውን ይከታተል ነበር፡፡ በመጨረሻም ደረጃው ከፍ ያለ ያካባቢው ክለብ ሲያስፈርመው የአማካዩ ዝና በመላው ሃገሪቱ ናኘ፡፡  በአስራ ሰባት ዓመቱ ሚላንን ሲቀላቀል ኮከብ ሆኖ ነበር፡፡ ሪቬራ ታላቅ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ተጫዋች እንደነበር ይነገራል፡፡ ኳሷን በተከላካዮች አናት እያሳለፈ እንዲሁም ግብ ጠባቂዎችን አታሎ የሚያስቆጥራቸው ጎሎች ቄንጠኞች ሲሆኑ ከሁሉ በላይ የጨዋታን ሒደት በቁጥጥሩ ሥር ማድረጉ እጅጉን የተካነበት ስጦታ ነበር፡፡ ለሁሉም የሚላን የወቅቱ ተጫዋቾች አንድ ያልተጻፈ ግን ዘወትር የሚተገበር ህግ ተላልፎላቸዋል፡፡ “ኳሱን ለሪቬራ ስጡት፤ በቃ! እግራችሁ ሥር የደረሰን ኳስ ለሪቬራ አቀብሉት!” የሚል፡፡ በክለቡ በቆየባቸው ሃያ ዓመታት በግልም በክለብም በርካታ ስኬቶችን አጣጥሟል፡፡ ሪቬራ ምንም ያህል ታላቅ ተጫዋች የነበረ ቢሆንም በሰላ ትችት የሚወቀስበት ድክመትም ነበረበት፡፡ በአንድ አጋጣሚ እንኳ አካላዊ ንክኪ ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለዓመታት ሲወቀስ ኖሯል፡፡ በጨዋታ ወቅት አካላዊ ጉሽሚያዎችን በመራቁ በታላላቅ ጋዜጠኞች ሳይቀር ብዙ ውርጅብኞች ቀርበውበታል፤ ቅጽል ስሞችም ተሰጥተውታል፡፡ ዝነኛው፣ ተጽዕኖ ፈጣሪውና በዘመኑ ምርጡ የእግርኳስ ጸሃፊ ጂያኒ ብሬራ ሳይቀር ሪቬራ በሜዳ ላይ ተጋጣሚን ለመጫን የሚያሳየውን ቸልተኝነት በሚመለከት አሉታዊ ሒስ ጽፎበታል፡፡ ከዚህም አልፎ ጋዜጠኛው ሪቬራን እና እርሱን መሰል ሌሎች ተጫዋቾችን የሚጠራበት ሥም እስከ ማውጣት ደርሷል፡፡ ብሬራ እነዚህን ተጫዋቾች “አልባቲኒ” ይላቸዋል፡፡ የጣልያንኛው ቃል ቀጥተኛ ፍቺ “ወጣት ቄስ” የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ በዝነኛው ጋዜጠኛ እንግዳ የሆነ የቋንቋ ዓለም ስያሜው ሌላ መልዕክት ኖሮታል፡፡ ሪቬራ ደካማ ነበር፡፡ ሜዳ ላይ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ አያደርግም፤ ኳስ የመቀማት ፍላጎት የለውም፤ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ላይ ጫና አያሳድርም፡፡ እንደ እርሱ አይነቶቹ እግርኳሰኞች “የቅንጦት ተጫዋቾች” ናቸው፡፡ አልባቲኒዎች በጨዋታ ወቅት አልፎአልፎ የሚሰሩት የ”እግርኳሳዊ ተዓምር” ቅጽበቶች በእነርሱ ቸልተኛ እንቅስቃሴ አማካኝነት በሜዳው መሃለኛ ክፍል ላይ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን አይደፍንም፡፡

ይቀጥላል…

የመጽሃፉ ደራሲ ጆን ማኪንቶሽ ፉት ይባላል፡፡ እንግሊዊው ጸሃፊ የጣልያንን ጓዳ-ጎድጓዳ አብጠርጥረው ከሚያውቁ የውጭ ምሁራን መካከል ይጠቀሳል፡፡ በበርካታ የጣልያን እና እንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎችም የጣልያንን ታሪክ አስተምሯል፡፡ በሃገሪቱ ፖለቲካ፣ ፍልስፍና እና ምጣኔ ኃብት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የታሪክ መጻሕፍትም አበርክቷል፡፡ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎችም ጥልቀት ያላቸው ጥናቶቹን ያቀርባል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ