በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች መልስ የ27 ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ በቀኑ ሁለተኛ ጨዋታ መርሐግብር የመውረድ ስጋት የተደቀነባቸውን አዳማ ከተማን ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ አገናኝቷል። አዳማ ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት በመቻል ከተሸነፉበት አሰላለፍ ሬደዋን ሸረፋ እና ቢንያም አይተንን በማሳረፍ በምትካቸው ሃይለሚካኤል አደፍርስን እና ዳንኤል ደምሴን ሲያስገቡ በተመሳሳይ ወልዋሎ ዓ.ዩ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፉበት አሰላለፍ ግብጠባቂውን በረከት አማረ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ ፉዓድ አዚዝን በማስወጣት ኦሎሩንለኬ ኦሉዋሴጎን፣ ናሆም ሃይለማርያም እና ሳምሶን ጥላሁንን አስገብተው ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተቀዛቀዘ ጨዋታን ያስመለከተን አጋማሽ ነበር። አዳማ ከተማዎች አብዛኛውን ጊዜ ከተከላካዮች ከሚነሱ ረጃጅም የአየር ላይ ኳሶች የማጥቃት ዒላማቸው በማድረግ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ በተቃራኒው ወልዋሎዎች ኳስን መስርተው በመግባት ከመሀል ከሚሰነጠቁ ኳሶች ግቦችን ለማግኘት ሙከራ ቢያደርጉም ነገርግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳያስመለክተን ረጅም ደቂቃዎችን አስቆጥሯል።
ያለሙከራዎች ተቀዛቅዞ የቆየው ጨዋታ 42ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስመልክቶናል። ወልዋሎዎች ከቀኝ መስመር ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ ሳሙኤል ዮሐንስ ቀጥታ ወደ ግብ የመታው ሲሆን ግብጠባቂው ዳግም ተፈራ መቆጣጠር ባለመቻሉ የመለሰውን ኳስ ያገኘው ዳዋ ሆቴሳ የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ በማስቆጠር ክለቡን መሪ አድርጓል።
ሆኖም ይሄ ደስታቸው የቆየው ለ3 ደቂቃ ነበር 45ኛው ደቂቃ ላይ መላኩ ኤሊያስ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ስንታየሁ መንግስቱ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ነቢል ኑር ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ወደ ግብ በመድረስ እና ሙከራዎችን መሞከር የቻሉ ሲሆን ይበልጥ አጥቅተው መጫወት የቻሉት ወልዋሎዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በጥሩ ሁኔታ ወደ ውጭ አውጥቶበታል። ብዙም ሳይቆይ ከ2 ደቂቃ በኋላ ቡልቻ ሹራ ከሳጥን ውጭ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው ሲመልሰው ያንኑ የተመለሰ ኳስ ያገኘው ስምዖን ማሩ በድጋሚ ቢሞክርም አሁንም ግብጠባቂውን ዳግም ተፈራን ግን ማለፍ አልቻለም።
በተለዋዋጭነት የጨዋታውን ብልጫ ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ የወሰዱ ሲሆን አዳማ ከተማዎች በስንታየሁ መንግስቱ እና ተቀይሮ በገባው አሜ መሐመድ አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ኳሶችን ወደ ግብነት በመቀየሩ ረገድ ግን የሁለቱም ቡድኖች ደካማ ጎን ሁኖ የተስተዋለበት ነበር። 90 ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ኤልያስ ለገሰ ያቀበለውን ኳስ ስንታየሁ መንግስቱ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂውን እንደምንም ጨርፎ ወደ ውጭ አስወጥቷታል። ይህም ለአዳማዎች እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ተጨማሪ ግቦችን ሳያስመለክተን ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።